ውኃ ያነጻል
ከብሉይ ኪዳን የሥርዓት አገልግሎቶች አንዱ በውኃ የሚፈጸም የመንጻት አገልግሎት ነው። በዕለታዊ ኑሮ በሰርግ በድግስ ስፍራ ለመንጻት የሚያገለግሉ የውኃ ጋኖች ይቀመጡ ነበር። ከምግብ በፊት መታጠብ ይገባል። የራስንና የሌሎችን ጤና ለመጠበቅ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡ ፡ ካህኑ ወደ ቤተ መቅደስ ከመግባቱ በፊት በደጃፍ ላይ ባለው የመታጠቢያ ሰን አማካይነት ንጹሕ ይሆን ነበር። ንጽሕና ለጤና፣ ለውበትና ለነጻነት በጣም ይረዳል። በሽታ አምጪ ነገሮች ከአካባቢውና ከውስጣችን የሚወጡ ናቸው። መታጠቢያ ቤት ደርሰን ስንመለስ የምንታጠበው ራሳችንን በራሳችን እንዳንጎዳም ነው ። ውኃ ከበሽታ በፊት፣ በበሽታ ጊዜ፣ ከበሽታ በኋላ ጤናን መንከባከቢያ ነው:: ራሳችንን የወደድነው፣ ቤታችንን የተቀበልነው ውኃ ስላለ ነው።
ውኃ አጥተው የቆሸሹ አሉ፣ ውኃ እያለ በስንፍና የቆሸሹ አሉ። ውኃ እንታጠብበታለን እንጂ አያጥበንም። ውኃ ለውበት እጅግ አስፈላጊ ነው፣ ውበት ያለንን ነገር መቀበልና መጠበቅ ነው ። ውበት ድምዳሜ የተሰጠው ምንም መለኪያ የለውም። ሦስት ነገሮች ግን ውበትን ያደምቃሉ። ንጽሕና ፣ ፍቅርና ጨዋነት። ውበትን አናመጣውም፣ እግዚአብሔር ሁሉንም ፍጥረት በውበት ፈጥሯል። አጠራሩም “ሥነ ፍጥረት” የሚል ነው። ያማረ ፣ የተዋበ ፍጥረት፣ ባለቤቱ መልካም ነው ብሎ ማኅተም ያሳረፈበት ነው። የተደበቀው ውበት በንጽሕና ይወጣል። ንጹሕ ሰውን አለመውደድ አይቻልም። የሚያውከውን የሚወድድ የለም። ንጽሕናን አለመጠበቅ ሌሎችን ማወክ ነው፡፡ ሌሎች የሚወዱን በአካል፣ በልብስ፣ በቤት ንጽሕናችን ነው።
ንጽሕና ነጻነትን ያጎናጽፋል ። ሱስ ከሚጠላበት ነገር አንዱ አካላዊ ንጽሕናንም ስለሚጋፋ ነው ። አፋችን፣ ልብሳችን ጥሩ እንዳይሽት ያደርጋል። ንጹሕ ስንሆን ግን ሰዎችን ማግኘት እንፈልጋለን። እኛ የራሳችን ብቻ ሳይሆን የሌሎችም ደስታ እንደሆንን ይሰማናል።
ሰው ውኃ ነው፣ ያነጻል። ውኃ የሚያነጻው ሳይታዘብ ነው:: በልቡ ትዝብት፣ በአፉ ፍርድ የሌለበት ሰው የሳተውን የሚመልስ፣ የወደቀውን የሚያነሣ ነው። ውኃ ማንጻቱን ሲፈጽም ድብቅ ስፍራ ላይ ነው። በአደባባይ እናርም፣ ሰድበን እንመልስ የሚሉ ሰዎች ሰውን በኃጢአቱ እንዲጸና ያደርጉታል እንጂ ለንስሐ አያበቁትም። በሌላው መሳት ሃይማኖተኛ መሆናቸውን፣ በሌላው መውደቅ ጽድቃቸውን ማወጅ የሚፈልጉ ወዮላቸው! በታሪክ እንዳየነው ሌላውን ስሁት የሚሉ ፣ ያለ መራራት የሚወግሩ ራሳቸው ከሀዲያን ሆነዋል:: ዱላቸውን ምርኩዝ ሳይሆን በትር አደረጉት። ጨካኝ ስለ ነበሩ ረድኤተ እግዚአብሔር ተለያቸው። አትፍረድ ይፈረድብሃል ማለት ይህ ነው። ጥሪ ያለው ሰው በኃጢአት አይወድቅም እያሉ በወደቀ ወንድማቸው ሲሳለቁ የነበሩ በማይጠበቅ አዘቅት ውስጥ ወድቀዋል። እግዚአብሔር በውድቀታችን የሚፈርደው በወደቁት ላይ የፈረድነውን ነው ። ፍቅር ግን የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል ፣ ይቀንሳል። በፍቅር የሳተውን መመለስ ይቻላል። ለዚህ ዘመን ገላጭ የሆኑ ሁለት ግጥሞችን ሁለት ቁጭቶችን ላክል፦
እራመዳለሁ ሲል መሬት ተንዶበት፣
እመክታለሁ ሲል ዱላው ተሰብሮበት ፣
ንብርብር ንብርብር እስቲ አትበሉበት
ለሰው ወራት አለው ወድቆ የሚነሣበት።
አልሞና አቅዶ ስህተት የሚፈጽም አለ፣ ላልማ ብሎ የሚያጠፋ አለ። ሁለቱን መለየት አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛው ግጥም በገዢነት ዘመናቸው በድለው ኋላ መከራ እየተቀበሉ ያሉት ሹም የተናገሩት ነው።
ሰው በድዬ ነበር አድርጌ እንደ ዋዛ፣
ቁናው ቁናዬ ነው ዙሩ በእኔ በዛ ።
ደግሞም እንዲህ ተብሏል፦
አንተም ጨካኝ ነበርህ ጨካኝ አዘዘብህ ፣
እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ ::
ሰው ውኃ ነው፣ ያነጻል። ትዝብትና ፍርድን ከተወ የጠፋውን ይመልሳል፣ የወደቀውን ያነሣል።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 14 ቀን 2017 ዓ.ም.