መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የትንሣኤው ብርሃን

የትምህርቱ ርዕስ | የትንሣኤው ብርሃን

እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ !

ብዙ እሑዶች አልፈዋል ። ጌታችን ሞትን አሸንፎ የተነሣባት እሑድ ግን የሰው ልጆች ሁሉ የሥጋና የነፍስ ትንሣኤ የታወጀባት የተመረጠች ዕለት ናት ። የፀሐይ ብርሃን በእሑዶች ላይ ሲወጣ ኖሯል ። በዚህ ቀን የወጣው የትንሣኤው ብርሃን ቃላት የማይገልጠው ነው ። ፀሐይ እዚህ ስታበራ እዚያ ጨልማ ነው ። የትንሣኤው ብርሃን ግን ሁሉን ያፈካ ነው ። ፀሐይ ከፀሐይ በታች ላለው ፍጥረት ታበራለች ። ጥልቅ በሆኑት ዓለማት በሰው መንፈስ ፣ በመቃብር ፣ በሲኦል ግን አታበራም ። የትንሣኤው ብርሃን ግን ለራሳቸው ዋጋ መስጠት አቅቶአቸው ለሚሰቃዩ የመንፈስ ሕሙማን ይኸው በራ ። ነገሥታትንና ጠቢባንን ይዞ አልለቅም ባለው መቃብር ላይ ይኸው ፈካ ። የኦሎምፒክ ችቦ ዓለምን ይዞራል ። የትንሣኤው ብርሃን ግን አንድ ጊዜ ለሁሉ አበራ ። ሰዎችም ለሞት እንዳይተኙ ፣ በእሳት በተያያዘ ቤት ውስጥ ትራስ እንዳያስተካክሉ ትንሣኤ ሕይወትም ማስተዋልም ሆኖ በራ ። ሙትን የሚከተል ሙት ነው ፣ ሕያውን የሚከተል ሕያው ነው ። ክርስቶስን የሚከተሉ ከዚህ ቀን ጀምሮ ጨለማ አይገጥማቸውም ። መፈጠር የተጀመረው በዕለተ እሑድ ነው ። ፍጥረት እንደገና የታደሰውም በዚህ ቀን ነው ። የሠራው እጅ ሊያበጀው ፣ የአብ ክንዱ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ ።

ያቺ ማለዳ እንዳለፉት ሺህ ዘመኖች ማለዳ አይደለችም ። ለሥጋ ተስፋን ፣ ለነፍስ አለኝታን የፈነጠቀች ማለዳ ናት ። ሴቶች ሞትን በመስማት ቀዳሚ እንደ ነበሩ አሁን ሕይወትን በመስማት ቀዳሚ ይሆናሉ ። ብሥራት ቢነገር ለድንግል ማርያም ፣ ትንሣኤ ቢነገር ለማርያም መግደላዊት ነው ። የእሑድ ሌሊት ከጨለማው ኃይላት ጋር ፣ ከታላላቅ ሰንሰለቶች ጋር ትልቅ ትግል የተካሄደባት ሌሊት ነው ። በጠባብ ማኅፀን ያደረው ክርስቶስ በጠባብ መቃብር አደረ ። ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይለውጥ ከማርያም ቅድስት የተወለደው አሁን ደግሞ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ተነሣ ። እየቻለ የሞተው እየቻለ ተነሣ ። በፈቃዱ የሞተው ፣ በፈቃዱ ተነሣ ። የሮማው ሹም ጲላጦስና ሄሮድስ ፣ የአይሁድ ሊቃውንት ተባብረው የሰቀሉት ክርስቶስ የአይሁድና የሮም ወታደሮች እያዩት ተነሣ ። ከሕዝብና ከአሕዛብ የተወለደውን ሕዝብና አሕዛብ ተባብረው ሰቀሉት ፣ ሕዝብና አሕዛብ እያዩት ተነሣ ። የመቃብሩ ማኅተም ፣ የሮማው ሕጋዊ ቁልፍ ሳይነካ ፣ ላብ ቆዳን ሳይቀድድ እንዲወጣ ክርስቶስ እንዲሁ ከመቃብር ወጣ ። የተነሣው በመቃብር ጠባቂዎቹ ድክመት አይደለም ፣ እነርሱ በጣም በርትተው ሳሉ የኃይላት ጌታ ተነሣ ። ያንን የመቃብር ስፍራ የሚታዩ ወታደሮች የማይታዩ የጨለማ ኃይሎች አጋንንት ይጠብቁት ነበር ። እርሱ ግን እንዳይነሣ የሚጠብቁትን ትቶ ወደሚጠባበቁት ደቀ መዛሙርት ሄደ ።

ትንሣኤው ገዳዮችን ያሳፈረ ፣ የአማኞችን ልብ የሞላ ነው ። ሰይጣን በሮማው ማኅተም ብቻ አላረፈም ፣ የክህደት ዜናንም ፈጥሮ ነበር ። ፈቅደው ቢሰቅሉትም ሳይፈቅዱ ተነሣ ። ሞትን መንገድ ሊያደርገው በቀራንዮ ገብቶ በጎልጎታ ወጣ ። “ጎሽ ለልጅዋ ስትል ተወጋች” እንዲሉ ለእኛ ሲል ሞትን ቀመሰ ። ያለነው በመቃብር ስፍራ ነበርና መቃብር ወረደ ። የእኛን ሞት ወስዶ የእርሱን ትንሣኤ ሰጠን ። ትንሣኤው እንዳይወራ ሰይጣን ገንዘብ ተሰነሰ ፣ ዜና አዘጋጀ ፣ ሐሰት ፈበረከ ። ሲጠሉት የሚብስበት የወንጌል ዜና ምድረ እስራኤልን አካለለ ።

ክርስቶስ ተነሣ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 17 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ