ውርርድ የሚወድ ሰው አሸንፎ መግባት እንጂ አስተምሮ የመግባት ዓላማ የለውም። ውርርድ የራስን የበላይነት የሌላውን ትንሽነት በማሳየት መደሰት ነው፡፡ ትልቅ ሆኖ የተወለደ የለም፣ ራሱን በትልቅ ዓላማ ግን የወለደ አለ። አዋቂ ሆኖ የመጣ የለም፣ ላያውቅም የሚኖር የለም። አንድ ዘመን አዋቂው አላዋቂ ነበረ፣ እውቀቱም በእብደት ሊሻር ይችላል። ውርርድ ለራስም ለሌላውም ክብር የለሽ መሆን ነው። ሦስተኛው ነገር ቁም ነገሩን የሚያድፋፋ ነው። ቁም ነገሩ የሚጠቀሰው ለቁም ነገሩ ክብር ሳይሆን ሌላውን ለማሸነፍ ጥሩ በትር ስለሆነ ብቻ ነው። ውርርድ የፌዘኝነት ልጅ ነው። ብዬ ነበር በማለት የራሱን ነቢይነት፣ ጥሎ ማለፍን በመናገር የሚኮራ ነው።
መንፈሳዊ ነገር ለራስ ክብር ፣ ሌላውን ለማሳነስ አይጠቀስም። ለእግዚአብሔር ክብር መኖር ነው:: ቅዱሳን አባቶቻችን ስሑታንን ረትተው አላረፉም ፣ የማሰቢያ ጊዜ ሰጥተዋል። እዚያ ጋ ወንድሙ በኃጢአት ሲወድቅ በዓይኑ ያየ ዓይኔንም አላምንም ብሎ ያስባል። መንፈሳዊ ነገር በቆራጥነት፣ በጸሎትና በፍቅር ካልተያዘ አደጋ ያመጣል። አደጋው ያመኑትን ያስወጣል፣ እየመጡ ያሉቱን ይመልሳል ::
በቆሻሻ ውኃም እሳትን ማጥፋት ይቻላል። በዱላም የበላይ መሆን ይቻላል:: በመስቀለኛ ጥያቄም ረቶ መግባት ይቻላል። እኛ አሸንፈን ወንድማችን በደጅ ከቀረ ተሸንፈናል ማለት ነው። ጣቱ ተቆርጣ ለመበጠስ ጫፍ ላይ ተንጠልጥላ ሐኪም ቤት የሚሄደው በጥሳችሁ ጣሉልኝ ለማለት ሳይሆን እንደ ምንም ቀጥሉልኝ ብሎ ነው:: በአንድ ክርስቶስ የምናምን በአንድ ባንዲራ ሥር ያለን አካል ነን። አንዱን አንዱን ስለ ማዳን ማሰብ አለበት። ክብራችንም ውርደታችንም የጋራ ነው፡፡ ወንድሜ ይዳን የማይል ክርስቲያን አይደለም።
ሃይማኖትና አገር እንደ ካምቦሎጆ እንደ ኳስ ድጋፍ ከታየ ከባድ ነው:: በጨዋታው የበላይ ስለመሆን ማሰብ ለቁማር እንጂ ለቁምነገር ዋጋ የለውም። አስተማሪ ተማሪዎቹን በማርክ ጥሎ ቢገባ ደስታ አይሰማውም፣ የተማሪ ውድቀት ያስተማሪም ውድቀት ነውና። ከርቸሌ እንኳ የማረሚያ ቦታ እንጂ የበቀል ቦታ አይደለም ተብሎ ስሙ ተለውጧል። ሰዎችን ገደል አፋፍ አድርሶ የውድቀት ዜና ማንበብ፣ ወንድምን አታሎ መግባት ለጊዜው ቢያሟሙቅም በፍጻሜው ደስታ የለውም። በአገራችን ሃይማኖት ያለው ይበዛል፣ ረቶ ለመግባት እንጂ በፍቅር ለመተናነጽ የወጣ ጥቂት ነው ። ልብስ በመገላለጥ ማሸነፍን ከፈለግን ይህ በከሀዲዎችም ሰፈር የለም። ትልቅ ውስጣዊ ጉዳት ያለው ሰው ሌላውን ዝቅ ማድረግ ይፈልጋል። ከውርርድ መንፈስ ወጥተን ቁም ነገርን እናስተላልፍ ! የእኛን አገር ለመውድድ የሌላውን አገር መስደብ አያስፈልገንም።
ውርርድ ቁምነገር ይጋርድ!