መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ጥጃ ቢፈነጭ በሜዳ ፣ ውኃ ቢሄድ በጎድጓዳ

የትምህርቱ ርዕስ | ጥጃ ቢፈነጭ በሜዳ ፣ ውኃ ቢሄድ በጎድጓዳ

አለመብሰል ፣ ለዓለምና ለሕይወት እንግዳ መሆን ገላጋይን ሲያደክሙ ፣ ያዥን ሲያዝሉ መኖር ነው ። ሁሉም ሰው ጀማሪነትን ያልፍበታል ። ጀማሪ አፍቃሪ ፣ ጀማሪ ተማሪ ፣ ጀማሪ አስተማሪ መሆን የተለመደ ነው ። በጀማሪነት በቃል ቢሳሳቱ ፣ በስሜት ቢስቱ ፣ በእግር ቢንሸራተቱ ወጉ ነው ። ሁልጊዜ ጀማሪ ሆኖ መቅረት ፣ በብስለት አለማደግ ፣ ባሉበት እየረገጡ መታየት አሳዛኝ ነው ። ጥጃነት በወቅቱ ደስታ ያለው እሰይ ተወለደልኝ የሚያሰኝ ነው ። ጥጃ ግን አድጋ በሬ ሆና ማረስ ፣ ላም ሁና መውለድ ፣ ማጥባት ይጠበቅባታል ። በሬም ላምም ተፈጥሮአዊ ሞትን አያዩም ፣ በመሥዋዕትነት ያልፋሉ ። ሞተውም አያበቁም ፣ በቆዳቸው ልብስ ፣ አልጋ ፣ ምንጣፍ ፣ የዜማ ዕቃ ይሆናሉ ። ማደግ ለመሥራት ፣ ለማብላት ፣ ለመሥዋዕትነት ነው ። በሬ እንኳ ቆዳውን ትቶ ይሞታል ፣ እኔ ምን ትቼ እሞታለሁ ( ማለት የራእይ መቆስቆሻ ነው ።

አድሮ ጥጃ መሆን ፣ የትላንቱ ድንጋይ ዛሬም እንዲያደናቅፈን መፍቀድ ፣ በጉዳት አለመማር ፣ የአዋቂዎችን ምክር አለመስማት ዋጋ እየከፈሉ መኖርን ያመጣል ። ጥጃ ሜዳ ሲያገኝ ይፈነጫል ። በሜዳ ሁሉ አይፈነጭም ። ጥጃ ሲፈነጭ ከእናት ተለይቶ ፣ ባልጠነከሩ እግሮች ሰማይ ተወርውሮ ፣ ገደሉን አላይ ብሎ ነው ። አደባባይ ስለ ተገኘ ማውራት ፣ መድረክ ስለ ተነጠፈ መለፍለፍ ፣ ሚዲያ በእጅ ስለሆነ እንዴት አደራችሁ ( ካላልኩ ማለት አለመብሰል ነው ። በሁሉ ነገር አስተያየት መስጠት ሁሉንም ነገር ያለ ማወቅ ውጤት ነው ። ለሁሉም ነገር መልስ አይሰጥም ፣ ዝምታም መልስ የሚሆንበት ጊዜ አለ ። ደግሞም የሚወራው ሰው ሲገኝ ነው ። “ይሁና ሰው ሲገኝ እናወራዋለና” እንዲሉ ። ሁሉም ነገር አይወራም ። የታየ ሁሉ እዩልኝ ፣ የተሰማ ሁሉ ስሙልኝ አይባልም ። የአስተዳደግ ጉድለት ፣ የጠባይ ቅለት ፣ የአስተሳሰብ ዝቅጠት ያለበት ያየሁትን ካላሳየሁ ፣ የሰማሁትን ካላሰማሁ ይላል ። በአደባባይ ልብሱን የሚያወልቅ ሳተ ከተባለ ፣ በአደባባይ ነፍሱን ፣ ገመናውን ፣ ትዳሩን ፣ ሃይማኖቱን የሚያራቁት እጅግ የሳተ ነው ።

ሁሉ አድናቂ ቢሆን ፣ ስናስነጥስ ይማራችሁ የሚለየን ሚሊዮን ቢደርስ ፣ በንግግር ማስከተል ብንችል ፣ ቃላችን እንደ ቃለ እግዚአብሔር አድማጭ ቢያገኝ እንኳ ሁልጊዜ መናገር አንድ ቀን ስብራት ያመጣል ። ዕድሜአቸውን በሙሉ ተወድደው የኖሩ ዘፋኞችና ዝነኞች በመጨረሻ በአንዲት መስመር ንግግር ጠላት ያተርፋሉ ፣ ቀባሪ ያጣሉ ፤ ሕዝብ ጠልቶ ሲወድ ድል ነው ፣ ወዶ ሲጠላ ልብ የሚያዝል ነው ። ሰው የሚወርደው የወጣውን ያህል ነው ። ሰባ ደረጃ ወጥቶ እንደሆነ ሰባ ደረጃ ይወርዳል ። ባመሰገነን ሰው ልክ ስድብ ይገጥመናል ። ጥጃ ቢፈነጭ በሜዳ እንዲሉ ሜዳው ተገኘ ተብሎ ሁሉ ጋ ተጋባዥ ፣ በሁሉ ነገር አስተያየት ሰጪ መሆን አለመብሰል ነው ። ሳይናገሩ እርስዎ ይናገሩ የሚሉን ብዙ ተንኮለኞች አሉ ። ሞኙ እንደ ነዱት ተነሥቶ አውጋዥ ይሆናል ። “እንደ ነደዳት ተነሥታ ልቅሶዋን አበላሸች” እንዲሉ ለመናገር ማሰብ ያስፈልጋል ። ዛሬ በቤት ውስጥ እንኳ ለመናገር የሚያሳፍር ወግ ሰዎች በአደባባይ ይናገሩታል ። ጥጃ በሜዳ ይፈነጫል ፣ በአደባባይ እዩኝ ስሙኝ የሚሉም ልጅነት ያጠቃቸው ፣ የማይሰነብቱ ናቸው ። መንገዱ ረጅም ነውና ረጋ ማለት ፣ እያዩ መጓዝ ግድ ይላል ። የአዋቂ ልኩ አላውቅም ማለቱ ነው ። አቅምን አለማወቅ ውርደትን ፣ ሽቅብ መትፋት መርከስን ያመጣል ።

ውኃ ቢሄድ በጎድጓዳ ይባላል ። ውኃ ጎድጎድ ያለ ፣ ሆድ ያለው መንገድ ይፈልጋል ። ባበጠ ነገር ላይ ውኃ አይጓዝም ። በምንም ተአምር ለትዕቢተኛ ጸጋ ይበዛለትም ። ትዕቢተኞች ጋ ሃይማኖታዊ ትርኢት ወይም ሰይጣናዊ ምትሐት ፣ አሊያም ጮሌነትና የድለላ ሥራ እንጂ ጸጋ የለም ። መሃይምናኑ ዲያብሎስ ተመታ በትዕቢቱ ይላሉ ። ትዕቢት መልአክን ሰይጣን ያደረገ ፣ ከአርያም እንጦሮጦስ ያወረደ ነው ። የጸጋ ቦይ ለመሆን ፣ ርሶ ለማረስረስ ትሕትና ያስፈልጋል ። በአንዱ ሬሳ ላይ ቆሞ አንበሳ ገዳይ ለመባል መፈለግ አለመብሰል ነው ። ሟች የሆነ ሰው እንዴት በወደቀ ላይ ይስቃል ( እንደውም ያኛው የሞት ዕዳውን ከፍሎ ዐረፈ ። ይብላኝ ሞት ተሸክመን ለምንዞረው ለእኛ እንጂ ። መሰወርን ጠልቶ አደባባዩን መሙላት ፣ እኔ ከተናገርኩ ማን ያርመኛል( ብሎ መደንፋት መጨረሻው አያምርም ። ይህች ዓለም ኃያል ተናጋሪዎችን ፣ ተናግረው የሚተኩሱ ጨካኞችን አስተናግዳለች ። ዛሬ ሁሉም የሉም ። መኖር ባለመኖር ፣ አንቱ መባል በመረሳት ሲደመደም ትልቁ ምክንያት ትዕቢት ነው ። ትዕቢተኛ ሲሞት በድንጋጤ ዕለቱን ይለቅሱለታል ፣ እየቆየ ግን እንባ ያደርቃል ፣ ሥራው ፍትው ብሎ ይወጣል ። በአምስት ላንድ ተደራጅቶ የሚያለቅስ ወገን መካከል ነንና ሳቀልኝም አለቀሰልኝም ብሎ መመሰጥ ተገቢ አይደለም ። እምነትን በአንድ አምላክ ላይ ማድረግ ብቻ ተገቢ ነው ።
ጥጃ በሜዳ ይፈነጫል ተቀምጠህ ተነጋገር ሲሉት አቅሙን ይፈራል !

ሩጫ ያልጠገበ ጥጃ እዘላለሁ ብሎ ይሰበራል ፣ ጉብታም እታያለሁ ብሎ በድማሚት ይፈነቀላል ። ከትልቅነቱ ይልቅ በማነሱ ቤትና መንገድ ይሠራበታል ። ጥጃ ጩኸት ታበዛለች ። “የምትጠባ ጥጃ አትጮህም” ይላሉ ፣ የሚማርም አይለፈልፍም ። ዛሬ የበላዩን ካልመራን የሚሉትን ስናይ “የማታድግ ጥጃ እናትዋን ትመራለች” የሚለው ትዝ ይለናል ። የጥጃ ስሙም አቅሙም በእናቱ የሚላስ ፣ ከእናቱ አጠገብ የማይለይ እንጂ የሚሮጥና የሚዘል አይደለም ። እስራኤል በወርቅ ለተሠራ የጥጃ ምስል ሰገዱ ፣ ትልቁ ካህን አሮንም ጥጃውን ሰበከው ፤ ዛሬም ላልበሰሉ የወርቅ ጥጆች ብርቅርቅታ ሙናዎች ወገን እየሰገደ ነው ፣ የሚሰብኩትም “ሕዝቡ እኛን አይንካን ፣ የሚፈልገውን እንስጠው” የሚሉት ትልልቅ አባቶች ናቸው !

በሜዳው እንዳይሰበሩ ለጥጆች ትዕግሥትን ፣ ውኃ እንዳያጡ ለጉብታዎች ትሕትናን እንለምናለን ። አማኑኤል ሆይ እኛው ነንና ይቅርታህን ደጅ እንጠናለን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ