መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » እንደ ራስ ነው ፍርድ

የትምህርቱ ርዕስ | እንደ ራስ ነው ፍርድ

“ፍረድ ለነፍስህ ብላ ለከርስህ”

“እንደ ራስ ነው ፍርድ” የሚለው ዘመን የተጠገበ አባባል ነው ። በእኛ የሚፈረደው በሰዎች የፈረድነውን ነው ። በፍትሕ ያላገጡ ፣ የሰው ትዳርና ኑሮ ሲደፈር የሳቁ ነገሥታት በመጨረሻ ያለ ቀባሪ ቀርተዋል ። ብዙ ቢሰሩም ፣ ድንበር ከማስከበር በላይ የውስጥ ፍትሕን ማርጋት እንደሚበልጥ ከታሪካቸው ተምረናል ። ጥንታዊው ዘፋኝ እንኳ እንዲህ ብሏል፡-

ኧረ ተው ሰዎች እንደ ራስ ነው ፍርድ ፣
ጭምት ያሳብዳል ዛርና መውደድ ፤

በሌሎች ጉዳት ተሳልቀን ከሆነ በእኛም የጉዳት ቀን ስላቅ ትርፋችን ሆኖ ይመጣል ። እንደ ራስ ነው ፍርድ ሲባል እኔ ሊሆንብኝ የማልፈልገውን በሌላው ላይ ማድረግ የለብኝም ማለት ነው ። “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንተ ፍትሕ እንደምትፈልግ ለሌላውም ፍትሕህን ስጥ ማለት ነው ። ፍትሕ ለጥቁር ለነጭ ፣ ለሀብታም ለድሀ ሳይሆን ፍትሕ ለተገፋ ሁሉ ይገባዋል ። እግዚአብሔር ከሚያቀርቡለት መሥዋዕት በላይ በዚህ ይረካል ። ፍርድ ለእግዚአብሔር ነው ብለን እንደ ዋዛ እንናገራለን ። ይህ ማለት ሰው በዚህ ዓለም ላይ የእግዚአብሔር የዳኝነቱ ወኪል ሆኖ ተቀምጧል ማለት ነው ። መጽሐፉ አትፍረድና ፍረድ የሚል ነው ።

ጌታችን ከተቀበለው መከራ የነፍስ መከራ የሚባለው ፍርድ ማጣቱ ነው ። ነፍስ ፍትሕንና ፍርድን ስታጣ በብርቱ ትሰቃያለች ። ፍትሕ ለእኔና ለእገሌ ሳይሆን ፍትሕ ለሁሉ ካልሆነ ያልረጋ ዓለም ይከሰታል ። ሰዎችን የሚያባላቸው የሃይማኖት ማጣት አይደለም ። በኢትዮጵያ ክርስትና ፣ በሱማሊያ እስልምና ፣ በእስራኤል ይሁዲነት አለ ። ግን የእርስ በርስ ግጭት በርዶ አያውቅም ። ሰዎችን የሚያከባብራቸው የፍትሕ መርጋት ነው ። ፍትሕ የሚጀምረው በቤት ውስጥ ከአባ ወራው ነው ። ልጆችን ሲዳኝ አንተ ጥፋተኛ ነህ ብሎ ሲቀጣ ፍትሕ መሠረት እየያዘ ይመጣል ። ያለ ምክንያት ልጆችን መቅጣት ፣ አንዱ ባጠፋ ሁሉንም መግረፍ ፍትሕ ከምድር እንድትወጣ መሥራት ነው ። አባትና እናት ልጆችን ተከፋፍለው አንዷ ወደ አባትዋ ፣ አንዱ ወደ እናቱ እንዲወግኑ ማድረግ ፍትሕን ያጠፋል ፣ በመጨረሻም ያ ትዳር ይፈርሳል ። “ተወልዶ ብልጫ አንክሶ ሩጫ የለም” ይባላል ። ልጆችን ማበላለጥ ያድግና የገዛ ሕዝቡን የሚያበላልጥ መንግሥት እንዲመጣ ያደርጋል ። ሁሉም ነገር የሚያልቀው በቤት ውስጥ ነው ። እንኳን በንግግር በአሳብም ሊጸየፉት የሚገባው ነገር ቢኖር ልጆችን ማበላለጥ ነው ። ሁሉም የእኛው ናቸውና ጸጋችንን መሸራረፍ ተገቢ አይደለም ።

አንዱን ልጃችንን የበለጠ ስንወደው እርሱም ይሳቀቃል ፣ ወንድም እኅቶቹም ይጠሉታል ። ዮሴፍ በወንድሞቹ ለመሸጥና ለመጋዝ የበቃው አባቱ በተለየ ይወደው ስለነበር ነው ። ያዕቆብ ይህን የተማረው ከወላጆቹ ነው ። አባቱ ይስሐቅ ዔሣውን በጣም ይወድ ነበር ፣ እናቱ ደግሞ ያዕቆብን ትወድ ነበር ። ልጆችን እኛ ከምንወዳቸው በላይ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ማድረግ መልካም ነው ። ምክንያቱም ዐረፍተ ዘመን ሲገታን እነርሱ በፍቅር ይቀጥላሉ ። ልጅን ሲያሳድጉ ነገን እያዩ ነው ። የይስሐቅና የርብቃ ትዳር በኀዘን ያለቀው ታላቁን አባት ፣ ታናሹን እናት በመከፋፈላቸው ነው ። እስከ ዛሬ የዘለቀ ጦርነትን በትውልድ መካከል የተከለ ጉዳይ ነው ።

ፍትሕ መስጠት ስብሐተ እግዚአብሔር እንደ ማድረስ ነው ። እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳል ። መስቀል ላይ የዋለው ጌታ ፍትሕን ያጣ ፣ የራሱንም ፍትሕ ያሟላ ነው ። መስቀል የፍትሕ መሟላትን የሚናፍቅ ዓርማ ነው ። ፍትሕ ለነፍስ ነው ። የልብ ሰላም ፣ የአእምሮ መፈታት ፣ የመንፈስ እርካታ ለማግኘት ፍትሕን መስጠት ይገባል ። ፍትሕ ሁሉንም ካሳቀች ፍትሕ አይደለችም ። ፍትሕ ምንድነው ?

1- ስህተቱ የእኔ ነው ማለት ነው ። ኃላፊነትን የሚወስድ ሰው የጥፋት ቀኖችን ይቀንሳል ። ክብርንም ያገኛል ። አለመበደል ቢያቅት እንኳ በበደል አለመግፋት ሰውነት ነው ።

2-በትክክል በድለሃል ብሎ በዳይን መውቀስ ። ሰውን በጥፋቱ ማባበል ጨለማ ዘመንን መጥራት ነው ። ፍቅር በእውነት ላይ እንጂ በሽንገላ ላይ መቆም አይገባትም ።

3- የሌላውን ሕመም መገንዘብ ። እግራችንን በሌሎች ጫማ ውስጥ አስገብቶ ማሰብና መናገር ፣ መፍረድ ይገባል ። እውነት መናገር ካልቻልን ዝም ማለት ተገቢ ነው ።

4- የጋራ ዓለምን በጋራ መጠቀም ። ትልቁ ፍትሕ ለእኔና ለእኔ ወገን ብቻ አለማለት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ የተቀመጠ እንስሳም ባለመብት ነው ።

5- ወንጀልን መቅጣት ። መንግሥት ይቅር ባይ ነው የሚል አባባል ይሰማል ። ይቅር የሚል የሞተበት ፣ የተገደለበት ነው ። የመንግሥት ሥራ ፍትሕን ማሟላት ነው ።

6- በክፉና በደግ መካከል ያለውን ድንበር ማስመር ። እውነተኛው የሞራል ሕግ ከአምላክ ለሰው የተገለጠ ነው ። እንደ ፈለግነው መኖር አንችልም ።

7- ሥልጣን ያለበትን ዓለም መፍጠር ። ሚሊየን ደግ ሕዝብ ከሚገዛ አንድ ክፉ ገዥ ቢገዛ ይሻላል ። ሥልጣን ያስፈልጋል ፣ ሥልጣንም መከበር አለበት ። ከሁሉም ስፍራ ሥልጣን እየጠፋ ነው ። ልጆች ወላጆቻቸውን እየተቆጡና እያስፈራሩ ነው ።

ትልቁ የነፍስ ጥያቄ ፍርድ ነው ። አንተ ትክክል ነህ ፣ አንተ ተሳስተሃል ማለት የነፍስ ግዳጅ ነው ። ፍትሕ የነፍስ ምግብ ነው ። ዛሬ ላይ “ሆ” ብሎ አንዱን ሰው ማጥቃት ተለምዷል ። ሚሊየን ለአንድ ሰው መነሣቱ የወንድነት ጉዞም አይደለም ። ማጥቃት እንደ ሰላምታ ቀላል ሆኗል ። ሌላውን እየሠዉ መራመድ ፣ የሚያስጥል መጥፋት ፣ ምን አገባኝ ማለት ፣ ይባሉ የሚል ጭካኔ ፣ በጉቦ ጨለማውን ብርሃን ማለት የምድራችን ጣር ሆኗል ።

የአገራችን አባባል ድንቅ ነው፡- “ፍረድ ለነፍስህ ፣ ብላ ለከርስህ !”
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ