“ዝኆን ቢያንቀላፋ ዛፍ ተደግፎ ነው ።”
እምነት ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን ለሥጋዊ ኑሮአችንም አስፈላጊ ነው ። ያለ እምነት መኖር አይቻልም ። መሬቱን ለመርገጥ ፣ ምግቡን ለመብላት ፣ ሰዎችን ለማግኘት ፣ ሥራ ለመሥራት ፣ መድኃኒት ለመዋጥ ፣ ለአገር ለመዝመት እምነት ያስፈልጋል ። እምነት እያደገ እንደሚመጣ ሁሉ እምነት ማጣት ወይም ፍርሃትም በጊዜ ካልገሠጹት እያደገ ይመጣል ። ሥራ የመሥራት ፍርሃት እያደገ ይመጣና ከቤት መውጣትን መፍራት ይጀመራል ። ከቤት የመውጣት ፍርሃት እያደገ ይመጣና ከአልጋ የመውረድ ፍርሃት ያመጣል ። ፍርሃት በእምነት ፣ በመጋፈጥ ፣ በመለማመድ የሚወገድ የሰው ልጆች ትልቅ ጋሬጣ ነው ። ማንቀላፋት ትልቅ እምነትን ይጠይቃል ። ሰው ፍጹም ተሸንፎ እንቅልፍ ሊጥለው ይችላል ። ለማንቀላፋት ግን እምነት ይፈልጋል ። ይልቁንም በሰው መካከል ለማንቀላፋት ሰዎቹን ማመን ይፈልጋል ። ሰዎቹን ማመን ሲባልም አይታዘቡኝም ፣ አይቀየሙኝም ፣ የእኔ ነገር አይከብዳቸውም ብሎ ማመን ያስፈልጋል ።
ነቢዩ ዳዊት፡- በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁ ይላል ። አገርን የሚመራው ንጉሥ ዳዊት በሰላም ማንቀላፋቱ በእግዚአብሔር ላይ ባለው እምነት የመጣ እንጂ የሠራዊት ብዛት የሰጠው ልብ አይደለም ። እግዚአብሔር ለሚታመኑበት የቀን ሰላምን ፣ የሌሊት እንቅልፍን ይሰጣል ። በዚህ ምድር ላይ ራስን እንደ መጠበቅ ያለ አድካሚ ነገር የለም ። ስንዘናጋ ፣ ስንተኛ ራሳችንን ልንጠብቅ አንችልም ። ማመን ምርጫ ሳይሆን ግዳጅ ነው ። ማመንም የሚታመነውን እግዚአብሔር ነው ። ሰላም ያላቸውን ሰዎች ስናይ ደስ ይለናል ። ስለሚያረጋጉን ከእነርሱ ጋር መሆንን እንፈልጋለን ። የኑሮ ግብዐታቸው ከእኛ ያነሰ ቢሆንም ሰላማቸው ግን ከእኛ ሰላም የተሻለ ሲሆን ይደንቀናል ። የእግዚአብሔር ሰላም በምድራዊ እሴት ላይ አይመሠረትም ። እንደውም ምድራዊ ነገር ለሰላም ትልቅ እንቅፋት ነው ። ሰላም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እንጂ የሀብትና የዝና ፍሬ አይደለም ። የመንፈስ ቅዱስ ሰላም ደግሞ በመብልና በመጠጥ ፣ በልብስ ላይ የሚመሠረት አይደለም ። በመንፈስ ቅዱስ ሰላም የተረጋጉ ሰዎች ዓለም ያመለጠን መስሎን የምንቀዠቀዠውን እኛን በኑሮአቸው ይገሥጹናል ።
“በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም አቤቱ ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።” መዝ. 4 ፡ 8 ። በሰላም እተኛለሁ የዕለቱን እንቅልፍ ብቻ አይደለም ። ዕለተ ሞትን ፣ ይህችን ዓለም የመሰናበት ቀንን የሚያመለክት ነው ። ከእግዚአብሔር ጋር የኖረ ሰው ሞትን መንገድ ያደርገዋል እንጂ አይሸበርም ። ለእግዚአብሔር እንደ ሠራ የሚሰማው ክርስቲያን ባይኖርም ፣ እግዚአብሔር ግን እንደ ሠራበት የሚያምን ክርስቲያን በሰላም ለማረፍ ዝግጁ ነው ። መኖርን የምንመኘው እግዚአብሔር በእኛ ሊሠራ ያሰበውን ሥራ ካልፈጸመ ብቻ ነው ። እኛው ሰበብ ፣ እኛው አድራጊ የሆንበት የምድር ቆይታ ሰላምን የሚያሳጣ ነው ። ብዙዎች ሮጠዋል ፣ ያለ እግዚአብሔር ስለሮጡ እያለቀሱ ተመልሰዋል ። ብዙዎች ወደ ጣዖት አምልኮ ወደ ተሳሳተ እምነት በተለያየ ስሜት ሄደው እያዘኑ ተመልሰዋል ። የዓለም ኑሮ ክለሳው የሚያደክምበት ቢሆንም ወድቆ አለመቅረት ግን ክብር ነው ።
ዝኆን ቢያንቀላፋ ዛፍ ተደግፎ ነው ። ራሱን ቢጥል የሚሸከመው እንዳለ አረጋግጦ ነው ። እንኳን የሰማይ መንገድ የምድር ጉዞም በወንድነት አይዘለቅም ። ወንድነትም ይደክማል ፣ ኃያል ሰውም በደዌ ታስሮ እቤት ይቀራል ። አሸባሪዎችም የደሴት እስረኞች ሆነው ይኖራሉ ። ለኃያልም ኃያል አለው ። አቻ የሌለውን ጉልበታም የናዝሬቱ ኢየሱስን መደገፍ የአማኝ ወጉ ነው ። በሰው ይሁንታ ፣ ተወለድ ተብሎ ፊርማ ተሰባስቦ ወደ ምድር ያለ መጣ የሰው ልን በእምነት ከመኖር ውጭ ፣ ላመጣውና ለሚወስደው ጌታ ከመታመን በቀር ምንም ምርጫ የለውም ። በእግዚአብሔር ካልተማመንን እያንዳንዱ ቀን የእኛን አለመቻል በብርቱ እየነገረን ነው ። ሰው ልኩን እንዲያውቅ ታላላቅ ፈተናዎች ወደ ምድር መጥተዋል ። ያለ እግዚአብሔር መዝራት ይቻል ይሆናል መሰብሰብ ግን አይቻልም ።
ዝኆን ዛፍ ተደግፎ ያንቀላፋል ፣ እኛ ያንቀላፋነው ማንን ተደግፈን ነው ? ለዝኆን ዛፍ መደገፊያውና ልኩ ነው ፣ የሰውን እምነት ግን ሊሸከም የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ያለ ምሽግ የሚንጎማለል ወታደር ቀጥሎ የጥይት ሰለባ ነው ። ያለ ንስሐ ፣ ያለ ቅዱስ ቍርባን አለሁ አለሁ የሚል የሰው ልጅ ፍጻሜው አጉል ነው ። የተዘናጋነው ምን ይዘን ነው ? የእገሌ መውደቅ የእኔ መውደቅ ነው ፣ የእገሌ ሞት የራሴን ሞት በዓይኔ የማይበት መስተዋት ነው ማለት ያስፈልገናል ። ሰው መሆን ማለት ሲደርስብን ሳይሆን ከደረሰባቸው ሰዎች መማር መቻል ነው ። ውድ ወዳጆች የዚህ ዓለም ዘመኖች ሲታጠፉ የዘላለም በሮች እንዲከፈቱ ዛሬ በእግዚአብሔር ላይ ተደገፉ ! እርሱ የተደገፉትን የማይጥል በዘመናት የጸና ነው ።
በአቤቱ ሆይ ማመናችንን በአንተ ብቻ አድርግልን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም.