ቍጣን ለማብረድ
ዘላቂውን ማሰብ
የሚያልፉ ጉዳዮች ጤናን እንዳይጎዱ ፣ ዘላለማዊ ሕይወትም በወቅታዊ እንዳይጠቀለል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። በዚህ ዓለም ላይ የምንኖረው ዘመን አጭር ነው ። በቂምና በበቀል ስሜት ሲሆን ግን በጣም ረጅም ነው ። ዝምድናዎች ሊሰረዙ የማይችሉ በሰው ፈቃድ ላይ ያልተመሠረቱ ናቸው ። የሥጋ ቋጠሮ ከላይ ነው ። ተለያይቶ የማይለያይ ቢኖር ዘመድ ነው ። ብዙ ወዳጅነቶች ይቅርታ እያጡ ይኖራሉ ። ዝምድና ግን አንድ ቀን ጉዞውን ይቀጥላል ። ዝምድናን መሻር የማይቻለው አንደኛ ሰማያዊ ቋጠሮ በመሆኑ ነው ። ሁለተኛው ማኅበረሰቡ የዘመድን ጠብ ስለማይቀበለውና እንደ ቀልድ ስለሚያየው ነው ። ነገር ግን በእኛ መካከል ያለው ዝምድና ሊነቃነቅ ባይችልም ፣ ጠብን ለልጆቻችን ካወረስን የበለጠ ያሳድጉታል ። ልጆች የሰጠናቸውን ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም ይጨምሩበታልና ዘላቂውን ነገር በማሰብ ቍጣንና ሰባሪ ንግግሮችን ማራቅ ያስፈልገናል ። ቀጣይ ጤናን ፣ ዘላቂ ግንኙነትን ማሰብ ያስፈልጋል ። ሁልጊዜ እኛ ያልነው አይሆንም ፣ ሁልጊዜ አሸናፊ መሆንም ይሰለቻል ፣ ለመቀበል መልቀቅ ያስፈልጋል ፣ የራስን ጥቅም ብቻ በማስከበር ዘላቂ ሰላም አይገኝም ፣ የሌሎችንም ጥቅም ማክበር ይገባል ። እኔ እኔ በማለት ጠላት እናበዛለን ፣ እኛ በማለት ሰብአዊ ግዴታን ማሟላት ይገባል ። ሕይወት ሁልጊዜ ስሌት ናት ። ከመልካምና ከክፉ ብቻ ሳይሆን ከክፉና ከክፉም የተሻለውን ክፉ መምረጥ ያስፈልጋል ። አጠገባችን ከሚኖሩ ጎረቤቶች ጋር መለያየት ስለማንችል ክፉ የሆኑ ጠቦችን ማራቅ ያስፈልገናል ። በቍጣ ሳይሆን በእርጋታ መነጋገር ፣ በግብታዊነት ሳይሆን ሕግ በሚፈቅደው ነገር መተማመን ይገባል ። አብሮ የሚኖር ጎረቤት ከሩቅ ዘመድ የተሻለ ነውና ። በልጆች ፣ በእንስሳት ፣ በድንበር የሚመጡ ችግሮችን በስምምነት መፍታት ያስፈልጋል ። ትንንሽ ጉዳዮች ትልልቅ ጠብ አላቸውና መጠንቀቅ ይገባናል ።
ያልፋል የሚለውን መርሕ መከተል
በዚህ ዓለም ላይ የማያልፍ ደስታና ችግር የለም ። እንኳን ትንንሽ ጉዳዮች ሰማይና ምድርም ያልፋሉ ። ሁልጊዜ ነዋሪና አስጨናቂ ማንም የለም ። እነዚያ በመንገድ የማናያቸውን ፣ በቅርብ ርቀት የማንደርስባቸውን ነገሥታት መቃብራቸውን እየነካን እናያቸዋለን ። አንድ ሳጥን አለ ፣ ሁሉንም የሚከት ። ቁልፉ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው ። ያ ሳጥን መቃብር ነው ። ደሴት የገዛ ፣ ሕንፃ የሠራ በሦስት ክንድ ከስንዝር ተወስኖ ይቀራል ። ከበሬታም በስድብ ይለወጣል ። የካባ ስጦታ ይገፈፋል ፣ የዓለም የኖቤል ሽልማትም ተሰጥቶ ይወሰዳል ። ቁመናም ገለል ይላል ፣ ውበትም ምልክት ሳያስቀር ይሄዳል ። ተሰብስበን የበላንበት ፣ እገሌ ከቤቴ ይውጣ ብለን የፈረድንበት ቤትም አውራ መንገድ ይወጣበታል ። የወዳጃችን ክፍት በር አንድ ቀን ይዘጋል ፣ ምክንያቱም በሕይወት የለምና ። ድምፁ ባለ ጣዕም የነበረውና ዜመኛው ከሕልም ይልቅ እየራቀን ይመጣል ። የለፋንለትና ብዙ ሰዎችን የገፋንበት ያ ንብረትም ተወርሶ ይቀራል ። የተጨነቅንለትና እንቅልፍ ያጣንለት ጉዳይም መና ይሆናል ። ካንተ በፊት ያስቀድመኝ ፣ ሞትህን ልሙትልህ ይሉን የነበሩ መሄዳቸውን ሳይነግሩን በዚያው ይቀራሉ ። የሰርግ ድምፅም በኑሮ ግብግብ ይለወጣል ። የትላንቱ ደፋር ወልዶ ፈሪ ይሆናል ። ፈሪም ሸለቆውን ወጥቶ አገር ያስጨንቃል ። ከቢሮዬ ውጣልኝ ብሎ የጮኸ ከመሥሪያ ቤቱ ደጃፍ ለማኝ ሁኖ ይታያል ። ድንበር ሲገፋ ፣ የሌላውን ሲመኝ የኖረ የራሱንም ጥሎ ይሄዳል ። ሀብቱንም ልጆቹ አይበሉትም ። መዋደድ እንዳለ መጣለት ይመጣል ። አንድ ጥሬ ለሁለት እንቆርጥም ያሉ ዓይኑን አያሳየኝ ይባባላሉ ። የጠላነው ይወርሰናል ፣ የፈራነውም ምንም ብንፈራው መሆኑ አይቀርም ። ሁሉም ያልፋልና ቍጣን መተው ይገባል ።
የሚያስቆጣን ነገር በርግጥ መኖሩን መገምገም
ከቀበሌው ሠራተኛ ጋር የምትከራከረው የመብራት ኃይል ማመልከቻ ይዘህ ነው ። የክፍያ ካርድህ ተዘግቷል ሲልህ ብልጭ የሚልብህ ቀኑ ያለፈበትን አሮጌ ካርድ ስለከተትህ ነው ። መነጽርህ በመጥፋቱ የምታዝነውና የምትናገረው ዓይንህ ላይ ሰክተኸው ነው ። እገሌን ስትጠራው ባለ መምጣቱ ብስጭት ያልከው ደጅ ልከኸው ነው ። ቀጥረሃቸው ባለመምጣታቸው ድሮስ እነርሱ ያልካቸው አደጋ ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተው ነው ። አንዳንድ ነገሮች የማይጎዱህ ከሆነ ለቀቅ አድርግ ። ወላጆችህ ሁሉም ነገር ላይ ችክ ሲሉ ይገርምህ ነበረ ፣ አንተም እንደ እነርሱ ለምን ተነካብኝ እያልህ ጉዳት ላይ ነህ ። የተሰማህ የበሽታ ስሜት የፈራኸው ሳይሆን በቶሎ የሚድነው ነው ። ቆዳህ ላይ የወጣ ከባድ የመሰለህ ነገር ምናልባት ብጉር ነው ። ለሁሉም ነገር መልስህ ራስህን የሚያስከፍልህ አይሁን ። ይውሰዱብህ እንጂ አይውሰዱህ ። የሰማኸውን ክፉ ወሬ መጀመሪያ ከባለቤቱ አጣራ ። ልራብ ነው ማለትን ትተህ ተርቤአለሁ ወይ ብለህ ራስህን ጠይቅ ። ዛሬን ሳትኖረው ለነገ አትጨነቅ ። አልረካሁም ብለህ ባገኘኸው ነገር አትበሳጭ ፣ የሚያረካ ነገር በዓለም ላይ የለም ። “አብን አሳየንና ይበቃናል” አለ እንጂ ዓለምን አሳየንና ይበቃናል ፣ ቤተ መንግሥትን አሳየንና ይበቃናል አልተባለም ። እስኪደርሱበት የዓለም ክብር ያሯሩጣል ፣ ከደረሱበት በኋላ ባዶነቱ ያስጨንቃል ። አለመርካትን ለማንም መንገር አይቻልም ፣ አያምነንምና ። የተራበውን ሁሉም ያዝንለታል ፣ በጥጋብ ውስጥ ያለውን ረሀብ ፣ በነጭ ልብስ የተሸፈነውን ጥቁር ልብስ ግን ማንም አያውቅም ። ከመቆጣት በፊት የምንቆጣበት ነገር በትክክል መኖሩን ማረጋገጥ ይገባል ።
ይቀጥላል
መጋቢት 3 ቀን 2018 ዓ.ም.