የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -14

ቍጣን ለማብረድ

ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መጠቀም

ቍጣውን የሚቆጣጠር ሰው ዓለምን መቆጣጠር ይችላል ። የሚቆጣ ሰው በመጨረሻ ከራሱ ጋር ይጣላል ። በቍጣ የምናፈርሰው ግንብ ከጠፋው ጥፋት በላይ ይሆናል ። አንዳንድ ጊዜ እውነት ላይ የተመሠረተ ቍጣ ይኖራል ፣ ልጆችን ተማሪዎችን መቆጣት አስፈላጊ ነው ። ሁሉንም ነገር ፌዝ የሚያደርጉ ሰዎችን ቆጣ ብሎ ማስቆም ይገባል ። ይህ ቍጣ ግን ዕድሜው ፀሐይ እስክትጠልቅ ነው ። ዓላማው ሰዎቹን ማስደንገጥ ሳይሆን እንዲለወጡ መፈለግ ነው ። ብዙ ጊዜ አይተን ፣ ገምተን ፣ መክረን ፣ አስመክረን መመለስ የማይፈልጉትን ሰዎች ከኑሮአችን ማራቅ ተገቢ ውሳኔ ነው ። ይህ ቍጣ ተብሎ የሚጠቀስ አይደለም ። ቤተ ክርስቲያንም ለመለወጥ ፍላጎት የሌለውን ሰው ትለየዋለች ። ቍጣን መቆጣጠር አስፈላጊ ሲሆን ቍጠኛ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ማኅበራዊ ሚዲያ ነው ።

ማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎችን ቢዚ በማድረግ የምድር ገዥዎች ጥፋትን ሲያከናውኑ ትውልድ እንዳያያቸው ዓይኑን የሚያውሩበት ነው ። እያንዳንዱ ቅንብር የሥነ ልቡና አዋቂዎች አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ፣ የሰው መሻት ይህ ነውና በዚህ አደንዝዙት የሚል የክፋት ምክር ያለበትም ነው ። ሰዎችን ፋታ ማሳጣት አንዱ የዓለም ሥርዓት ነው ። ኳስ ሲጨርስ ፊልሙን ፣ ፊልሙን ሲጨርስ ዜናውን እያከታተሉ መወጠር የዚህ ዓለምና የሰይጣን አሠራር ነው ። ጦርነቶችም ሲፈበረኩ ከምናውቀው ምክንያት የተለየ ነገር ሊኖር ይችላል ። ነገሥታት እንዲወጣባቸው የማይፈልጉት ምሥጢር ዳር ላይ ሲዳረስ ትኩረትን የሚያስቀይር ትልቅ አደጋ ይፈጥራሉ ። ለአንዱ ሰው ክብር መጠበቂያ ሺህዎች ይሞታሉ ፣ ንብረቶች ከልክ በላይ ይወድማሉ ። ማኅበራዊ ሚዲያ ያልተጣሩ መረጃዎች ስላለበት ሰውን የሐሰት ሎሌ ያደርጋል ። እርጋታ ስለሌለው ትዕግሥት ያሳጣል ። የምንፈልገው ብቻ ሳይሆን የተመረጠልን ነገር ስለሞላበት ዓላማን ያስታል ። መነኮሳትን ከጸሎት ፣ ምእመናንን ከቤተ እግዚአብሔር ያርቃል ።

ማኅበራዊ ሚዲያ እየበዛ ሲመጣ ከፍተኛ ራስ ምታት ፣ ድባቴ ፣ ጭንቀት ፣ ለመኖር ፍላጎት ማጣት እየተከሰተ ይመጣል ። ይልቁንም ዓለምን በስልኩ ላይ በመሐል እጁ የሚያየው ሰው ኑሮው እንዲህ ቀላል አልሆን ሲለው ይበሳጫል ። በሥራው ውጤታማ እንዳይሆን ለአስፈላጊው ነገር ጊዜ እንዳይሰጥ ፣ ወዳጅነቱን እንዳያከብር ስለሚያደርገው ብዙ ኪሣራ ያመጣበታል ። የባልና የሚስት ፣ የወላጅና የልጆች ግንኙነት ይበላሻል ። በቅርብ ያሉት በእውነት የሚራራቁበት ፣ ከሩቆች ጋር ደግሞ ሐሰተኛ ወዳጅነት የምንመሠርትበት ነው ። ሰው ንግድ ከሌለው በቀር ማኅበራዊ መገናኛ ላይ ብዙ ጊዜውን ባያጠፋ መልካም ነው ። ገንዘብን ፣ ጊዜን ፣ ጤናን ፣ የዓይንን ብርሃን ፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን ያባክናል ። የውሸት አልቃሾችን እየተከተለ እውነተኛ ኪሣራ ውስጥ ይገባል ። ማኅበራዊ ሚዲያ ቍጡ ያደርጋል ። ውስጣችን ጭንቅ ጭንቅ ሲለው ፣ ብስጩነት ሲያጠቃን መንፈሳዊ ቀለብና ንባብ ቀርቷል ማለት ነው ። በየዕለቱ መጸለይ ፣ ማንበብ ፣ ኅብረት ማድረግ ለመረጋጋታችን አስፈላጊ ነው ። ብዙ ውጤታማ ሰዎች ከማኅበራዊ ሚዲያ የራቁ ናቸው ። ምንም ነገር በእጁ ያልጨበጠው ሰው የሰውን ስኬት ሲያዳንቅ ይውላል ። ሥራ እንኳ ስንፈታ የበጎ ፈቃድ እርዳታዎችን ማድረግ ተገቢ ነው ። ታማሚዎችን መርዳት ፣ የሙት ልጆችን ማጫወትና ማጽዳት አስፈላጊ ነው ። ሁልጊዜ መሥራት የለም ፣ ታዲያ ሥራ በማንሠራበት ወቅት ሌላ የነፍስ ተግባር እንዳለን ማወቅ ያስፈልጋል ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ