የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -15

ቍጣን ለማብረድ

ማለፍንና መተውን መማር

አንድ ሰው ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ከደረሰ ጠብን መናቅ አለበት ። ይልቁንም የአገር መሪዎች ጠብን ካልናቁ ሁሉንም ለመቅጣት ካሰቡ ከሥራ ይልቅ በሴራ ዘመናቸውን ይፈጽማሉ ። “ንጉሥ በግንቡ ሳይቀር ሳይታማ አይውልም” ይባላል ። ሐሜትን ፣ ስድብን ካልታገሠ ያለበትን ስፍራ አላወቀም ማለት ነው ። ትዕግሥትና የልብ ስፋት ለአስተዳደር በጣም አስፈላጊ ነው ። ራሱን ያልገዛ ሰው ወደ ሥልጣን መምጣት የለበትም ። ገንዘብ ፣ ሥልጣንና ዝና ኃይል ናቸውና ራስን መግዛት ይፈልጋሉ ። መኪናም አውሮፕላንም ኃይል አላቸው ፣ መቆጣጠሪያም አላቸው ። ፈረስ ልጓም አለው ፣ መሪዎችና አስተዳዳሪዎችም የሚገታቸውና የሚገድባቸው ሕግ ከሌለ ተጎድተው ሕዝብንም ይጎዳሉ ። አንድ ንጉሥ የሰደበው ፣ ጦር የመዘዘበት ሲገጥመው መጀመሪያ ጠቡን ግላዊ አድርጎ ማሰብ አይገባውም ። ምክንያቱም የብዙኃን ድምፅ ሁኖ ተቀምጧልና ነገሮችን ከግሉ አንጻር ማየት የለበትም ። ሁለተኛው ወይ እኔ ወይም ከእኔ በታች ያለ በድሎት አሳዝኖት ይሆናልና እስቲ ልስማው ማለት አለበት ። ሚሊየን ሠራዊትና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች ባሉበት አገር ማንም አልበደለህም ብሎ መከራከር አይችልም ። የአገሩ ልማት የእርሱ ሁኖ እንደሚነገርለት ፣ በአንድ ወታደርና በአንድ ሥራ አስፈጻሚ ስህተትም ንጉሥ ይወቀሳል ። ምስጋናውም ወቀሳውም የእርሱ ነው ። የቀደሙት ነገሥታት እረኛ ምን አለ ( አዝማሪው ምን አለ ( በማለት ስህተታቸውን ይፈልጉ ነበር ። ሕዝቡ ዝም ሲልም መልካም አይደለም በማለት እንዲጮኽ ያደርጉት ነበር ።

ማለፍ ትልቅ ጸጋ ነው ። እግዚአብሔር አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ያልፈናል ። የሚያልፈን በስህታችን ተስማምቶ ሳይሆን ይለወጣሉ ብሎ ተስፋ አድርጎን ነው ። ማለፍ ተስፋ መቍረጥ ሳይሆን ተስፋ ማድረግ ነው ። ሰው ከዛሬው ምክራችን ባይማር ከነገው መከራና የኑሮ ግፊት መማሩ አይቀርም ። ሰውን ለቀኑ መተው ትልቅ ብስለት ነው ። የሰው ልጅ ከመምህራን ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ፣ ከመከራ ይማራል ። ታላላቅ መምህራን ወደፊት አሉና ምክሬን ለምን አልሰማም ብለን ተስፋ መቍረጥ አይገባንም ። እንደውም ምክርን ረግጦ ሲሄድ የሚቆየው መከራ በድርብ ነው ። ጸጸትም ይጎዳዋል ፣ ለካ የሚደርስብኝን መከራ ቀድመው አይተውልኝ ነበር በማለት የመከሩትን ሰዎች ማመስገን ይጀምራል ። ምክርን እንቢ ማለት ይቻላል ፣ መምህርን ገፍቶ መሄድ የግል ነጻነት ነው ። መከራ መምህር ሁኖ ሲመጣ ግን ጥሎ መሄድ አይቻልም ። የመምህሩ ምክር ነጻ የትምህርት ዕድል ነበረ ። መከራ ግን እያስከፈለ የሚያስተምር ነው ። መከራ የሚያስገፍለው ጥሬ ገንዘብ ሳይሆን አካልን ፣ ስሜትንና መንፈሳዊነትን ጭምር ነው ።

ሁሉን አይተን ፣ ሁሉን ሰምተው ከሰው ጋር መኖር ከባድ ነው ። ከራሳችን ጋር የምንኖረውም ራሳችንን እያለፍነው ነው ። ሰዎች እኛን የቻሉት ነገር እንዳለ ሁሉ እኛም ሰዎችን መቻልና መሸከም አለብን ። ይልቁንም ሊለውጡት የማይችሉት ነገር መታገል ሰዎቹን ለመስበር ነው ። መጸለይ ፣ ለእግዚአብሔር ዕድል መስጠትና ጊዜ ትልቅ መምህር መሆኑን ማመን ይገባል ። መተው ነገሬን ከተተው ይባላል ። የሚያውቁት ሁሉ አይወራም ፣ ባዩት ነገር ሁሉ ዱላ አይመዘዝም ። መተው ራሳችንንም ሌሎችንም ያድናል ። “የስሙኒ ዶሮ የብር ከሃምሳ ገመድ ይዛ ጠፋች” እንዲሉ ጉዳዩና ንዴታችን የማይመጣጠን መሆን የለበትም ። ሁሉም ነገር ከእኛ ቀጥሎ ነው ። ይዘነው ባልመጣነውና ይዘነው በማንሄደው ንብረት ብስጩና ራሳችንን የምንጎዳ መሆን የለብንም ። በመጦሪያ ስፍራ የምናገኛቸው እንዲሁ የኖሩ አይደሉም ፣ የሚያውቃቸው ሰው አልቆ እንጂ የትላንት ጌቶች ነበሩ ። በመንገድ ላይ የወደቁት ትላንት ያማረ ቤት የነበራቸው ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ይህንንም ተቀብለው በመኖራቸው ሊደነቁ ይገባል ። ዓለም ተለዋዋጭ መሆኑን ማመን ቶሎ ከመሞት ይጠብቃል ። የሰው ልጅ ሲወልድ አመል ያወጣል ። ዝምተኛው የነበረው ለፍላፊ ይሆናል ። እንዲሁም ከልግመኛና ከራስ ወዳዶች ጋር ሲኖርም ጠባዩን እየከሰረ ይመጣል ። ራስ ወዳድ ወዳጅን መክሮ መሸኘት ፣ ልግመኛ ሠራተኛን አስተምሮ ካልተመለሰ ሌላ ዕድል እንዲሞክር መንገር መልካም ነው ። ጠባያችንን እንዳንከስር ማለፍና መተውን መማር አለብን ። ከእኛ በዕድሜና በሀብት የሚያንሱ ሰዎች ቢሆኑም ከሰውነታቸው ጋር እየታገሉ የሚኖሩ ናቸውና መረዳትም አለብን ። ቍጣን ለማብረድ ማለፍ ወሳኝ ነው ። የምናልፈው ስለታለፈልን ነው ። የምንተወው ስለ ተተወልን ነው ። የተሻለ ነገር ካገኘን የተበደረንን ሰው መከታተልና ማስጨነቅ አላስፈላጊ ይሆናል ። ምናልባት ያልሰጠን በብልጠት ፣ በማታለል ሳይሆን አጥቶ ሊሆን ይችላል ብለንም የዕዳ ምሕረት ማድረግ አለብን ።

ይቀጥላል
መጋቢት 10 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ