መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕይወት ራስ » የሕይወት ራስ -3

የትምህርቱ ርዕስ | የሕይወት ራስ -3

“የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት”

የሐዋ. 3 ፡ 15 ።

የትውልድ አባት

በሁሉ አገርና ዘመን የትውልድ መነሻ ተደርጎ የሚታሰብ አባት አለ ። እኛ የእገሌ ዘሮች ነን ማለት ትልቅ ኩራት ይሰጣቸዋል ። አዳም የፍጥረት መነሻ እንደሆነ ሁሉ የተለያዩ አገሮችን የመሠረቱ አባቶች አርኬጎስ የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል ። ጌታችንም የዳነችው የአዲሲቷ ዓለም መሥራች ነው ። በዓለም ላይ ትልቅዋ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያን ናት ። ቤተ ክርስቲያን በመቀራረብዋ ቤተሰብ ፣ በማስተሳሰርዋ አገር ፣ በጥበብ ባሕርነትዋ ዓለም ፣ በመዳረሻዋ ሰማይ ፣ ለክርስቶስ በመቅናትዋ አካለ ወልድ ተብላ ትጠራለች ። የዚህች ትልቅ ትውልድ መነሻ አርኬጎስ ክርስቶስ ነው ። ደስ ይበላችሁ ። ብቸኛ ነኝ እንዴት ትላላችሁ ? እግዚአብሔርን በሚፈራ ሰው ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል ተብሏልና ፈሪሀ እግዚአብሔር ካላችሁ ብቸኝነት አይሰማችሁም ። አንድ ሠራዊት ያለው መልአክ ሲሰፍር ከአእላፋት ቅዱሳን መላእክት ጋር ነው። በምድር ላይ የምናዝነው ጥቂት ሰዎች ከዱን ብለን ነው ፣ ከዳተኛ የረከሰ ነው ፤ የተቀደሱ መላእክት ግን በዙሪያችን አሉ ። ያልተቀደሱት በመሄዳቸው ደስ ሊለን ሲገባን እናዝናለን ፤ ከእኛ ጋር ያሉት የተቀደሱ መላእክት ቢሆኑም ይህን ማሰብና መደሰት አልቻልንም ። ጠባቂ መላእክት ሳሉን ፣ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቤተሰብ ሁና ተሰጥታን ሳለ ብቸኛ ነኝ ማለት ተገቢ አይደለም ። ደግሞም ሞት ገደብ ፣ ሰማይ ሩቅ ሳይሆንብን በላይኛው መኖሪያ ብዙ ዘመዶች አሉን ። ሥላሴ አባት እናቱ ሆነው ሳለ አባት እናት ሞቱብኝ ብሎ የሚያዝን አማኒ ተብሎ አይጠራም ። ቅዱሳን መላእክት ዘመድ ወገኑ ሁነውለት ሳለ ዘመድ የለኝም ብሎ የሚያዝን አላዋቂ ነው ። የሞት መንገድ ሲጀመር የሚከተል አንድም ዘመድ የለም ፣ የሚቀበለን ያመነው ጌታና መላእክት ናቸው ። ዘመዶቹ ተቀበሉት ተብሎ አይዘመርም ፣ ወደ መቃብር ሲሄድ የሚዘመረው “ወተቀበልዎ መላእክት” እየተባለ ነው ። የሚገርመው በምድር ሲለቀስ ፣ በሰማይ በደስታና በመዝሙር ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ያስገቡታል ። ይህን ሁሉ ክብርና ዝምድና የሰጠን የትውልድ አባት ክርስቶስ ነው ።

ጌታችን የሕያዋንና የሙታን ጌታ ፣ በሕያዋንና በሙታን የሚፈርድ ተብሎ ይጠራል ። ሕያዋን የሚባሉት በምድር በተጋድሎ ያሉት ቅዱሳን ሲሆኑ ሙታን የተባሉት ከሥጋ የተለዩ በነፍስ ሕያዋን ሁነው በሰማይ ያደሩት ናቸው ። በሰማይና በምድር አንዲት ቤተ ክርስቲያን አለች ። የዚህች ቤተ ክርስቲያን የአንድነትዋ መሠረት አንድ ራስ የሆነው ክርስቶስ ነው ። አንድ ራስ አንድ አካል አለው ፣ አንድ አካልም አንድ ራስ አለውና አንዲት ቤተ ክርስቲያን አንድ ጌታ ክርስቶስ አለ ። የሰው ልጅ ታሪክ እንደ አንድ ቀን ጨለማና ብርሃን ነው ። የጨለማው ገጹ በአዳም የመጣ ሲሆን የብርሃን ገጹ በክርስቶስ የሆነለት ነው ። አዳም ጀማሪ ነውና የእርሱን ዕዳ ልጆቹ ተሸከሙ ፣ ክርስቶስም የጽድቃችን መሠረት ነውና ጽድቁን እንካፈላለን ። ከአዳም በመወለድ ብቻ ፍርዱን የተካፈሉ ፣ ከእግዚአብሔር በመወለድም ጽድቁን ይካፈላሉ ። እንዴት በመወለድ ብቻ ጽድቁን እካፈላለሁ ? ካሉ እንዴት በመወለድ ብቻ ፍርዱን ተካፈልኩ ? ብለው መጠየቅ አለባቸው ። ፍርድን የተቀበለ አእምሮ ድኅነትንም መቀበል አለበት ። የትውልድ አባት ነው ሲል ሐዋርያው ጴጥሮስ አርኬጎስ በማለት ክርስቶስን ጠርቶታል ።

ይቀጥላል

ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ