“ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው ? እኛ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነንና” (2ቆሮ. 6 ፡ 16)
የብሉይ ኪዳኑ መቅደስ በኢየሩሳሌም የተወሰነው ብቸኛ የአምልኮ ማዕከል ነበረ ። በአዲስ ኪዳን ግን የክርስቲያኖች ሰውነትና የአማንያን ኅብረት መቅደስ ተብሎ ተጠርቷል ። እግዚአብሔር በአማንያን ሰውነት ላይ ያድራል ፣ በመካከላችንም ይገኛል ። እርሱ በአማንያን ሰውነት እንዲያድር መቀደስ ፣ በምእመናን መካከል እንዲገኝ አንድ መሆን ይገባል ። እያንዳንዱ በግሉ ሲቀደስ ኅብረቱም እውነተኛ እየሆነ ይመጣል ። ኅብረቶች እውነተኛ እንዲሆኑ እንመኛለን ፣ የግል ቅድስና ሲደረግ ኅብረቱም ንጹሕ እየሆነ ይመጣል ። እያንዳንዱ ቤቱን ቢያጸዳ ከተማው ጽዱ እንደሚሆን ምእመንም በግሉ ሲቀደስ ኅብረቱ እየተቀደሰ ይመጣል ። ጽዳት ከራስ ነው የሚባለው ለዚህ ነው ። ቤተ መቅደስ የሆነው አማኝና ኅብረቱ ከጣዖታት ጋር ትብብር ሊኖረው አይገባም ። ጣዖታት የሰው እጅ ሥራ ናቸው ። ሰውም ራሱ ለሠራው ነገር መስገድ ራሱን ማዋረድ ነው ። ጣዖታት የሚታዩ ቅርጾች ብቻ ሳይሆኑ በልባችን ላይ የእግዚአብሔርን ቦታ የያዙ ነገሮች ሁሉ ጣዖታት ናቸው ።
የጣዖት አምልኮ ከጥንት እስከ ዛሬ ትውልድን ሲበክሉ ኖረዋል ። በአል የሚባል ጣዖት ነቢዩ ኤልያስ የተቃወመው የዝናብ አምላክ ተብሎ የሚጠራ ነበር ። ጣዖታት አንዳንድ ፍጥረት እንዳላቸውና አንድ ግዳጅን ብቻ እንደሚወጡ ይታሰብ ነበር ። የፀሐይ አምላክ ፣ የጦርነት አምላክ ፣ የባሕር አምላክ እየተባለ ይጠሩ ነበር ። እግዚአብሔርን አኃዜ ኵሉ ዓለም ብሎ መጥራት ፣ ሁሉን የያዘ እያሉ ማመስገን ከጣዖታት ልዩና መንፈስ መሆኑን መመስከር ነው ። ሰባቱም የእንግሊዝኛ ስያሜ የሆኑት ቀናት የጣዖት ስም አላቸው ። ሰን ዴይ- የፀሐይ ቀን ማለት ነው ። መን ዴይ የጨረቃ ቀን ማለት ነው ። የወራቱ ስያሜም ጃንዋሪ ፣ ማርች ፣ ጁን ከሮማ ጣዖታት የተወሰዱ ስያሜዎች ናቸው ። የወሩ ዕለታት በጣዖታት በመሰየማቸው ወደ ክርስትና የመጡት አሕዛብ በዚያ ቀን ትዝታው ይረብሻቸው ነበር ። ይህን የጣዖታት ትዝታ ለማጥፋት በቅዱሳን ስም ቀኖችን መሰየም እየተለመደ መጣ ። በርግጥ የራሱ የሆነ የበዓላት ሥርዓት እንዳለም የታወቀ ነው።
ከከነዓን ጣዖታት የታወቀው በአል የሚባለው የዝናብ አምላክ ነው ። የሰው መሥዋዕት ይቀርብለት ነበር ። ሞሎክ የተባለ ጣዖትም የሕፃናት ግብር ይቀርብለት ነበር ። በኤፌሶን የነበረችው ጣዖት አርጤምስ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሴተኛ አዳሪዎች ነበሩባት ። ዝሙትንም እንደ መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር ። ጣዖታት መጀመሪያ ላይ የእንጨትና የድንጋይ ቅርጽ ናቸው ፣ ሰዎች አምልኮ ማቅረብ ሲጀምሩ ግን የአጋንንት ማደሪያ ይሆናሉ ። ሰይጣንም በገዛ ልጅ ሳይቀር እንዲጨክኑ በማድረግ የሰውን ሕሊና ለጭንቀት ይዳርጋል ። በዚህ ዘመንም ሀብት ለማግኘት የገዛ ልጆቻቸውን ግብር የሚሰጡ ፣ ሀብት ቢያገኙም በሚከስስ አእምሮ የሚመላለሱ ብዙ ምስኪኖች አሉ ። ከእያንዳንዱ ሀብት በስተጀርባ ወንጀል አለ የሚባለው ከእውነት የራቀ አይደለም ። ሰዎች ወደ ጣዖታት ሲሳቡ ከእግዚአብሔር ይለያሉ ። ሕያውን አምላክ በግዑዝ ስለ ለወጡ ታላቅ ቍጣን ያተርፋሉ ። ጣዖት አምልኮ አገርንም ያስረግማል ። ይህም ሰማርያ እንዴት በውኃ ጥም እንደ ተቀጣች የኤልያስን ታሪክ ስናነብ ይገባናል ።
ጣዖታት የሰውን መንፈስ ይረብሻሉ ፣ የሚያመልካቸውም እንደ እነርሱ ይሆናል ። መንፈሱ ይሞታል ። በትዳር ውስጥ ሰላምን ያሳጣሉ ፣ ልጆችን ባካና ያደርጋሉ ። ለሰማይና ለምድር ሠራዊት መስገድ ብቻ ሳይሆን ዕድልን ለማወቅ ሞራ መግለጥ ፣ መዳፍ ማንበብ ፣ አዋቂ የሚባሉትን መጠየቅ ጣዖት አምልኮና እግዚአብሔር የማይታገሠው ኃጢአት ነው ። የሚገርመው አጋንንታዊ መጠበቂያ የሚያሠሩ ሰዎች ናቸው ። የፈሩት እግዚአብሔርን ነው ? እግዚአብሔርን ሰግተው አጋንንትን ጠባቂ እያደረጉ ነው ? ወይስ ከአጋንንት በአጋንንት ለመዳን አስበው ነው ? የእውነትም ይሁን የውሸት መጠበቂያ አለን እያሉ የሚያወሩና የሚያስወሩ እግዚአብሔርን ንቀዋልና ይናቃሉ ። የአስማተኞች ጻዕር/ጣር እንኳ ልክ የለውም ። ሲኦልን በምድር የጀመሩ ፣ ጠላትን አለምዳለሁ ብለው የታሰሩ ናቸው ።
“ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም ፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል ፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል ፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” ይላል ። (ማቴ. 6 ፡ 24) ። ገንዘብ ጣዖት ተብሏል ። ፍላጎታችን ፣ ሀብትና ዝና ፣ ሥልጣንና የምንወዳቸው ሰዎች ጣዖት ሊሆኑብን ይችላሉ ። በአጭር ቃል እምነት ፣ ተስፋ ፣ ፍቅር የምንጥልበት ሁሉ ጣዖት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ክብር ምስጋና ይድረሰውና ለዘመናዊነት … እያሉ ያወራሉ ። ሥልጣኔንም የሚያመልክ አለ ። ልብ አድርጉ ሰው የሚቀጣው ባመለከው ነውና ሥልጣኔውም ወደ ጥፋት እንዳያደርሰን መጠንቀቅ ይገባናል ። እገሌ ከሌለ እኔ አልኖርም ማለት ጣዖት አምልኮ ነው ። በገዥዎች መመካት ጣዖት አምልኮ ነው ። የእኔ ዘርና ቋንቋ እያሉ መናገር ፣ የራስን ዘርና የራስን ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ መውደድ ጣዖት አምልኮ ነው ። ብዙ ሰው የተሳሰረው በዘርና በቋንቋ ነው ። አገልጋይን እንኳ የሚቀርበው የአገሬ ልጅ ብሎ ነው ። ዘረኝነት ያሳንሳል ። ማነስ የማይሰለቻቸው በመጨረሻ ደቀው ይበናሉ ። ለሰው አካልና ቁንጅና ማዜም ፣ ስንኝ መግጠም ጣዖት አምልኮ ነው ። እንደ ዳዊት ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ መባል ነበረበት ።
እኛ መቅደስ ነንና ጣዖት ሊነካን አይገባም ። ከጣዖት ጋር ንክኪ ሊኖረን አያስፈልግም ። ለእግዚአብሔር የሰገደ ጉልበት ለሌላ ሊሆን አይቻለውምና ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም.