አለሁ ያሉ የማይኖሩብሽ ፣ መንገድ ያዘጉ መቃብር የሚገቡብሽ ፣ መሬት ለመርገጥ የተጸየፉትን ከመሬት በታች የምታስተኚ ፣ ትራስ ይቆረቁራቸው የነበሩትን ድንጋይ የምታንተርሺ ፣ ጽዩፍ የነበሩትን ያለ ነጭ የማይለብሱትን ጭቃ ላይ እስከ ዕለተ ምጽአት የምታስተኚ ፣ ሽቱአቸው ከሩቅ ይጣራ የነበሩትን ፈራሽ በስባሽ የምታደርጊ ፣ የተከፈቱ አፎችን ለዘላለም ጸጥ የምታደርጊ ፣ ቤቴ ቤቴ የሚሉትን ከቤት አውጥተሸ መቃብር የምታሳድሪ ፣ ግፍ ለመናገር የማይፈሩትን አንገት የምትሰብሪ ፣… ዓለም አታላይ !
ረሀብና ጥጋብን አልችል ያሉ የሚተራመሱብሽ ፣ ወዳጁን እየገፋ ጠላቱን ወዳጅ ለማድረግ የሚለፋ ትውልድን የተካሽ ፣ ፍቅርሽ ሐሰተኛ ጠላትነትሽ እውነተኛ የሆነ ፣ “ዓለም አንድ መንደር ሁኗል” እያልሽ ሰውን በጠባብነት የምታሰለጥኚ ፣ መንደርተኝነትን የምታስተምሪ ፤ ስለ መላው የሰው ዘር በልቅሶ እያወሩ ስለ ራሳቸው ብቻ የሚኖሩ ቀጣፊዎችን የምታመርቺ …ዓለም አታላይ !
እሰው ተዝካር ላይ ሰርግሽን የምትፈጽሚ ፣ በሌላው ሞት ለመኖር እቅድ የምታወጪ ፣ በአደባባይ ነጻነትን እያወራሽ በጓዳ ስንቱ በእስር የሚማቅቅብሽ ፣ ቀይ የሚወዱ ሹሞችን በቀይ ምንጣፍ እያራመድሽ በክብር ስም የምትሳደቢ ፣ ቀን በኮሩበት ከረባት ማታ ላይ አንቀሽ የምትገድዪ ፣ ቸርን እያጠቃሽ ስስታምን የምታከብሪ ፣ የተሸላለሙትን አንገት ለአንገት እንዲቀላሉ የምታደርጊ ፣ ዘላቂ ፍቅር ዘላቂ ጠብ የለኝም ብለሽ በክብር የምታወሪ ፣ ያረፈደው ሳቅ የማይውልብሽ ፣ በተዘፈነበት ቤት የሚለቀስብሽ… ዓለም አታላይ !
የሚያድንሽን ክርስቶስ ሰቅለሽ ፣ የሚገድልሽን በርባን የምትፈቺ ፣ በጥበብ ስም ዝሙትን የምታቆነጂ ፣ ለፈጠረው መዘመርን ነቅፈሽ ለተፈጠረው የምትዘፍኚ ፣ ሰዎች ለመቆሸሽ የሚጸዱብሽ ፣ ሽቱ ተቀብተው አመድ ላይ የሚንከባለሉብሽ ፣ የቀን ጌቶች የማታ ወራዶች የሚሆኑብሽ ፣ እናትና ልጅ ለንብረት ብለው ፍርድ ቤት የሚቆሙብሽ ፣ ሽማግሌ የልጅ ልጁን የሚያገባብሽ ፣ የሃይማኖት ካባ ለብሰው በቅናት አዋቂን የሚያጠፉብሽ ፣ መናንያን ከብደውሽ ገዳዮች የቀለሉሽ… ዓለም አታላይ !
ሳቅሽ የሚያልቅ ልቅሶሽ የሚረዝም ፣ ጉራማይሌ ተነቅሰሽ የማረክሽውን በጥርስሽ የምታደቂ ፣ የጠዋቱ ባለጠጋ ከሰዓት ለማኝ የሚሆንብሽ ፣ ነግሦ የሰነበተው በወኅኒ ሞቱን የሚጠባበቅብሽ ፣ የልጅነት መልክን በእንዶድ አጥበሽ ወና የምታደርጊ ፣ እህል የሚነቅዝብሽ ፣ ልብስ የሚነትብብሽ ፣ ወርቅ የሚደብስብሽ ፣ ደጉ ክፉ የሚሆንብሽ ፤ ያጎረሰውን እንዲነክስ ፣ ያኖረውን እንዲገድል ሰውን የምታሰለጥኚ ፣ ከላይ ወርቅ የለበሱ ከሥር ማቅ የታጠቁብሽ ፣ በትልቅ ቤት ትልቅ መከራ አምጪዋ …. ዓለም አታላይ !
ከላይ ፈሪሀ እግዚአብሔር ከሥር ይሉኝታን የጣሉ አግድም አደጎች የሚፈነጩብሽ ፣ አሁን ተሽሎኛል ያለው ገመምተኛ ቀጥሎ የሚሞትብሽ ፣ ሰው አያወራ የሚያልፍብሽ ፣ ድኛለሁ ብሎ ያወራው- ሬሳ የሚሆንብሽ ፣ እምቡጥ የመሰለው ቀዘባ የሚረግፍብሽ ፣ አደባባዩን የሞላው ቆንጆ ደብቁኝ ደብቁኝ የሚልብሽ ፣ በማይረካ ፍላጎት ፍጥረት የሚጨነቅብሽ… ዓለም አታላይ !
እበላለሁ ባይ የሚበላብሽ ፣ የሰውን ንብረት የቀማ በጸጸት የሚቀጣብሽ ፣ ቀለበት ያሰረ ቀለበቱን የሚያደቅብሽ ፣ ጋብቻ በፍቺ የሚጠናቀቅብሽ ፣ ለፍተው የተነሡት ፎቶ የሚቀደድብሽ ፣ ወዳጅነት በክዳት ነፋስ የሚበተንብሽ ፣ ምንም የማያውቁ ለጋዎች የሚጨነቁብሽ ፣ ጥቂቶች እንዲኖሩ ሚሊየኖች የሚሞቱብሽ ፣ .. ዓለም አታላይ !
መልክሽ እንደ እስስት የሚቀያየር ፣ ያየሽውን ልምሰል ባይ ፣ ተረኛ ወዳጅ እንጂ ቋሚ ወዳጅ የማታውቂ ፣ ለቆመ እንጂ ለወደቀ ቦታ የሌለሽ ፣ የከፈለ የሚያዝብሽ ፣ ፍቅርሽ ከእንካ ጋር የሆነ ፣ የባለጠጋ አስቀያሚ የለውም የምትዪ ፣ የሰውን ዋጋ የማታውቂ ፣ ያጣ ልጇን እናት እንኳ የምትጠላበት ፣ አበባ እየገዛሽ ሰው የምትገድዪ ፣ የወጣት ዋጋ ከዶሮ ዋጋ ያነሰብሽ … ዓለም አታላይ !
የድሀ ልጅ ወርቅ አለምድ ብሎ የሚራወጥብሽ ፣ የባለጠጋ ልጅ በምቾት የሚሰቃይብሽ ፣ የካህን ልጅ የሚባልግብሽ ፣ የባለጌ ልጅ ጻድቅ የሚሆንብሽ ፣ ባለ ጊዜው የጊዜ ምስኪን የሚሆንብሽ… ዓለም አታላይ !
እንደ ነጋም እንደ መሸም አይቀርም ፣ ሲነጋ ለምስጋና ፣ ሲመሽ በትዕግሥት መቆም የሰው ወግ ነው! ስቃ በምትገድል ዓለም ፣ ቆስለህ የፈወስከን የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ ተመስገን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 23 ቀን 2018 ዓ.ም.