መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ምሥጢረ ሥላሴ በፀሐይ ሲመሰል

የትምህርቱ ርዕስ | ምሥጢረ ሥላሴ በፀሐይ ሲመሰል

እግዚአብሔር ምሳሌ የሌለው አምላክ ነው ። የሰውን አለማወቅ ለማገዝ ግን ምሳሌ እንጠቀማለን ። እግዚአብሔር በአንድነቱ ሁለትነት ፣ በሦስትነቱም አራትነት የሌለበት ፤ አንድም ሦስትም ሁኖ የሚኖር ነው ። መለኮቱ አንድ ሲሆን ሁለትነት አይስማማውም ። ሦስትነቱም አራትነት አይጨመርበትም ። መለኮቱ ሁለትነት አይደመርበትም ፣ የአካላት ሦስትነቱም አራትነት አይነገርለትም ። ሦስትነቱ ወደ ሁለትነት ዝቅ አይልም ፣ አንድነቱም በሦስትነቱ መከፈል የለበትም ። መለኮት በአካላት እንደማይከፈል ፣ አካላትም በመለኮት አይጠቀለሉም ። ዘላለም ሥላሴ ፣ ዘላለም አንድ ሁኖ ይኖራል ። ሦስት አካላት ቢታዩም ፣ ግዛቱ አንድ ነው ። ሦስት ገጻት ቢታዩም ዙፋኑ አንድ ነው ። ሦስት መልክ ቢታይም ባሕርዩ አንድ ነው ። ምሥጢረ ሥላሴን በሙሉነት ልወቅ ማለት ኃጢአት ነው ። ምንም ማወቅ አልፈልግም ማለትም በደል ነው ። ምሥጢረ ሥላሴን በሙሉነት ልወቅ ማለት አእምሮን ሲያሳጣ ፣ ምንም ማወቅ አልፈልግም ማለት ደግሞ ሃይማኖትን ያሳጣል ። ስለ ምሥጢረ ሥላሴ በተማርን ቍጥር ምሥጢሩ ፣ ምልአቱ ያለው አንተው ጋ ነው ፣ አንተ ራስህን ታውቃለህ ብለን በምስጋና መደምደም እርሱ እምነት ይባላል ።

ምሥጢረ ሥላሴ ከሚተነተንባቸው ምሳሌዎች ፀሐይ ቀዳሚዋ ናት ። ፀሐይ ሦስትነት አላት ፣ ክበብዋ ፣ ብርሃንዋና ሙቀትዋ ። ሥላሴም ሦስትነት አለው ። ፀሐይ ሦስትነት ስላላት ሦስት ፀሐይ አትባልም ፣ ሥላሴም ሦስትነት ሲነገርለት አንድ አምላክ መሆኑን እንመሰክራለን ። የፀሐይ ክበብ ፣ ብርሃንና ሙቀት በምልአት እንዳሉ አካላተ ሥላሴም በምልአት ይኖራሉ ። በክበቡ አብ ፣ በብርሃኑ ወልድ ፣ በሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላል ። የፀሐይ ክበብ ያለ ብርሃኑና ያለ ሙቀቱ ኖሮ አያውቅም ፣ አብም ያለ ወልድና ያለ መንፈስ ቅዱስ ለቅጽበት ኖሮ አያውቅም ። የፀሐይ ክበብ ከቦታው አይናወጥም ፣ አብም ከስፍራው አይናወጥም ። በቤተ ልሔም ተወለደ ፣ በጽርሐ ጽዮን ተገለጠ አይባልለትም ። ክበቡ የብርሃንና የሙቀት መገኛ እንደሆነ አብም ወልድን ይወልደዋል ፣ መንፈስ ቅዱስን ያሠርጸዋል ። የፀሐይ ክበብ ከብርሃንና ከሙቀት እንደማይገኝ አብም ወላዲ አሥራጺ ይባላል እንጂ ተወላዲና ሠራጺ አይባልም ። የፀሐይ ክበብ ከስፍራው ሳይናወጥ ብርሃንና ሙቀትን ይልካል ፣ አብም ከስፍራው ሳይናወጥ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ይልካል ። የፀሐይ መኖርዋን ያወቅነው ቀና ብለን ክበቡን አይተን አይደለም ፣ በብርሃንዋ ስናይ ፣ በሙቀትዋ ከብርድ ስንድን የፀሐይን መኖር አውቀናል ። አብንም በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አውቀነዋል ። የፀሐይን ክበብ በቀትር ቀና ብለው ቢያዩት ማየት የማይቻል ነው ፣ አብም አይታይም ።

ወልድ በብርሃን ይመሰላል ። የፀሐይ ብርሃን መገኛው ክበቡ እንደሆነ ወልድም ከአብ ተወልዷል ። ፀሐይ ያለ ብርሃንዋ ፀሐይ ተብላ ተጠርታ አታውቅም ። እንዲሁም አብ መባል ዘላለማዊ ስም ነውና ያለ ወልድ አብ ተብሎ የኖረበት ዘመን የለም ። የፀሐይ ክበብ ፣ ብርሃንና ሙቀት መገኘታቸው እኩል እንደሆነ ሥላሴም በዘመን አይቀዳደሙም ። የፀሐይ ብርሃን ወደ ዓለም እንደሚመጣ ፣ ወልድም ተልኮ ወደ ዓለም መጥቷል ። መላክና መላክ(ጠበቅ አድርገህ አንብብ) በሥላሴ መንግሥት የሥራ ድርሻ እንጂ መበላለጥን አያሳይም ። ሥላሴ የዘመን መቀዳደም ፣ የክብር መበላለጥ የለበትም ። ክርስቶስ ከፀሐይ አብ የተገኘ ብርሃን መሆኑን መጻሕፍት መስክረዋል ። የዕብራውያን ፀሐፊም የክብሩ መንጸባረቅ ይለዋል (ዕብ. 1፡3)። ብርሃን ከክበብ ሳይለይ በዓለም እንዲታይ ክርስቶስ ከአብ ሳይለይ ወደ ምድር መጥቷል ። ያለማቋረጥ ብርሃን ከክበብ እንዲወጣ ክርስቶስ ያለ መለያየት ከአብ ጋር ይኖራል ። ዘላለማዊ ልደቱም ተከፍሎ የሌለበት ነው ። አንድ ልጅ ከወላጅ ሲወለድ መከፈል/መለየት አለበት ፣ የወልድ ልደት ግን ልዩ ነውና መከፈል የለበትም ። እንደ ክበብና ብርሃን አብሮ ነዋሪ ነው ።

የፀሐይ ብርሃን ከዓይን ጋር ይዋሐዳል ። ክበቡ አይዋሐድም ፣ አብም ሥጋ ለበሰ አይባልም ፣ ሙቀትም አይዋሐድም ፣ መንፈስ ቅዱስም ሰው ሆነ አይባልለትም ። የፀሐይ ብርሃን ከዓይን ጋር ቢዋሐድ የዓይን ብሌን መሰንጠቅ የለበትም ፣ ብርሃን ክርስቶስም ከድንግል በተወለደ ጊዜ ማኅተመ ድንግልናዋ እንደ ጸና ነው ። ብርሃን ከዓይን ጋር ሲዋሐድ ከምልአቱ ሳይጎድል ነው ። በዓለም ሁሉ እያበራ ከዓይን ጋር ይዋሐዳል ፣ እንዲሁም ወልድ ሥጋ በለበሰ ጊዜ በአርያም እየተመሰገነ በድንግል ማኅፀን ነበረ ። ከላይ አልጎደለም ፣ ከሥር አልተጨመረም ። ከሥላሴ መንበር ሳይጎድል ከታች ሥጋ ለብሶ ታየ ። አንድ አካል ሁኗልና ሥጋ በመልበሱ በሥላሴ ላይ አራተኝነት አልመጣም ።

መንፈስ ቅዱስ በሙቀት ይመሰላል ። የፀሐይ ሙቀት ከብርሃኑ ሳይሆን ከክበቡ እንዲገኝ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ተገኝቷል ። ከአብና ከወልድ ይሠርጻል የሚሉትን አንቀበላቸውም ። ብርሃኑ ባለበት ሙቀቱ እንዳለ ወልድ በከበረበት ጉባዔ መንፈስ ቅዱስ አለ ። ሙቀት ፍጥረት የሚገኝበት ነው ። መንፈስ ቅዱስም አዲስ ልጆችን ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል ፣ ወልድ ሥጋን ሲነሣ ሠራተኛው እርሱ ነው ፣ ምእመን ከውኃና ከመንፈስ ይወለዳል ። ወላጅ መንፈስ ነው ። ሙቀት ብርድን ያርቃል ፣ መንፈስ ቅዱስም ብቸኝነትን ያስወግዳል ። ያዘኑ ሰዎች ብዙ ሰው ከቦ ያጽናናቸዋል ። መንፈስ ቅዱስም ሙቀት ነውና ያጽናናል ። ሙቀት በሽታን ይገድላል ፣ መንፈስ ቅዱስም መንጽሒ ነውና ኃጢአትን ያስተሰርያል ። ሙቀት ከክበቡ አይለይም ፣ መንፈስ ቅዱስም ከአብ አይለይም ። መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ነውና አብ ያለ መንፈስ ቅዱስ የኖረበት ዘመን የለም !

የአብ ጸጋ ፣ የወልድ ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን ! አሜን ።

ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ