መግቢያ » ትረካ » ልታነጻኝ ትችላለህ » ልታነጻኝ ትችላለህ -3

የትምህርቱ ርዕስ | ልታነጻኝ ትችላለህ -3

/ማቴ. 8፡2/

መጣብኝ ሳይሆን መጣልኝ የሚሉት አንድ እንግዳ አለ ። ይህ እንግዳ በእልፍኝ ሳይሆን በልብ የሚስተናገድ ነው ። ፍሪዳ እንዳያቀርቡለት ራሱ የጽድቅ መሥዋዕት ነው ። ሕመምን ተሸክሞ ፈውስን የሚሰጥ ነው ። የብፁዓን ተራራ በሺህ ሕዝብ ተጥለቅልቋል ። መናገሻ ከተማውን ሳይናገር የነገሠውን ንጉሥ ፣ ዙፋን ሳይሻ ልብን የወረሰውን መንግሥት ብዙዎች ይከተሉታል ። ነቢዩ “እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ” ብሎ ነበር ። በጽዮን ግን የነገሡት ለሥጋቸው ያደሩ ፣ የምድርን ኃይል ኃይላቸው ያደረጉ ሰዎች ብቻ ነበሩ ። በብፁዓን ተራራ የመንግሥቱን አዋጅ ሲናገር ልቤ ያለ መናገሻ ከተማ እንዴት አዋጅ ይናገራል ? ብሎ ነበር ። ለካ መናገሻ ከተማው የአማንያን ልብ ነበር ። ትምህርቱን ፈጸመ ። የተራራው ስብከት ስለተበላሸው ዓለም ሳይሆን ስለሚጠገነው እኔነት ፣ ስላጠፉ ሰዎች ሳይሆን ስለጠፋነው እኛ የሚናገርበት ነው ። አስቀድሞ ሲመጣ ከተራራው ጀርባ በዝንጀሮ ገደል በኩል ሄጄ ነበር ። አሁን ግን በጀርባው ሳይሆን በፊት ለፊቱ ልቆምና ልማጸነው ደፈርሁ ። ከተራራው ሲወርድ መምህሩ በእውነትነቱ እያንጸባረቀ ፣ ተማሪዎቹ በሰሙት ቃል ፊታቸው እያበራ ነበር ። የእኔን ለምጻምነት ሲያዩ ሁሉም ብን ብለው ሊሸሹ ይችላሉ ። ትምህርቱ ግን ግለቱ ገና አልበረደምና ቢያንስ ለመሮጥ አልደፈሩም ። እኔም መማር በጎ ባያሠራ እንኳ ክፉ እንዳይሠሩ ይሟታል አልኩኝ ። ለምጻምነቴ ዛሬ እንደጠቀመኝ እያዩሁት ነው ። ከተራራው ቁልቁል የሚወርደው ሕዝብ ከተራራው ግርጌ ያለሁትን ልብሴ ያለቀውን ፣ ለምጼ የነደደውን ሲያዩ ግራና ቀኝ ለሁለት ተከፈሉ ። ቅዱሱ አጠገባቸው ስላለ እንረክሳለን ከሚል ፍርሃት ድነዋል ። የአዲስ ኪዳን ተማሪዎች ሁነዋል ። አእላፋት በግራና በቀኝ ሲከፈሉ ከተራራው ራስ ላይ ያለውን ከተራራው ግርጌ ያለሁት እኔ ፊት ለፊት ተያየን ።

“በዘላለም ተራሮች ሁነህ በድንቅ ታበራለህ” የሚለውን ዝማሬ አቀረብሁለት ። ደግሞም “መምህር ሆይ አንተ የእውቀት ቃል ሳይሆን የሕይወት ቃል አለህ” አልኩት ። እርሱም ያለበት ድረስ ና አላለኝም ። ከተራራው አፋፍ ላይ እኔን አቁሙ በመፈወስ ተከታዮቹን ሊያስደንቅ አልፈለገም ። የእርሱ ፈውስ ለበሽተኛው የሚደረግ ርኅራኄ እንጂ ለማስታወቂያ የሚሠራ አልነበረም ። የማስታወቂያ ፈውሶች ከሰይጣን ቤትና ከእነ ሆድ አምላኩ ግቢ የሚገኙ ናቸው ። እኔ በየትኛውም መንገድ ቢሆን መዳን እፈልጋለሁ ። እርሱ ግን ሁለት መንገድ የለውም ፣ መንገዱ አንድ ነው ። ወደ ተራራው ግርጌ ፈጠነ ። ያለሁበት ድረስ ኑ የሚል ፈዋሽ አልነበረም ። ፈውስ አገልግሎት እንጂ ጌትነት አለመሆኑን የሚናገር ነበር ። ፈውስ የእግዚአብሔር ርኅራኄ መግለጫ እንጂ የፈውስ ሀብት ያለው አገልጋይ ብቃት ማረጋገጫ አይደለም ። ፈውስ ሁሉንም ጸጋ የሚጠቀልል ሳይሆን አንዱ ጸጋ ነው ። ፈውስ በሽተኛ ካለ ብቻ የሚደረግ አገልግሎት እንጂ የሚጮህ ሰው ምነው በኖረ ተብሎ የጉባዔ ቅድስና የሚለካበት አይደለም ። ቅድም የሰማሁት የተራራው ስብከት ግን ነፍሴን ሲፈውሳት ይሰማኝ ነበር ። በርግጥም ነፍሴን ፈውሶ ወደ ሥጋዬ ፈውስ እንደ መጣ ገባኝ ። ነፍስ ሳትፈወስ ሥጋን መፈወስ በሬሳ አጠገብ በረከት ማስቀመጥ ነው ።

ያ መድኅን ከኢየሩሳሌም ትቶ በተራራ ላይ መንግሥቱን ያወጀው እርሱም እንደ እኔ መገፋትን የሚያውቅ ነው ብዬ እንዳስብ አደረገኝ ። እርሱ ቤተ መንግሥቱን ገንዘብ አላደረገም ፣ ለተረሱት ተስፋ ለመሆን በኅዙናን መልክ መጣ ። መገፋት ብርቱ ሕመም አለው ። መገፋት ግን ጌታዬ እግር ሥር ስለጣለኝ መልካም ነገር ነው ። በዱር ሕይወቴ በፈቃድም በግድም ፣ በሕግም በሥርዓትም ተገልዬ የምኖርበት ምድረ በዳው ኑሮዬ አንድ ነገር አስተምሮኛል ። ሰው ብቻ ዘመድ አለመሆኑን ነግሮኛል ። ከሰማይ ጋር በዘመኔ ያወራሁት ፣ ከዛፎች ጋር በጋራ የተሰበኩት በበረሃው ኑሮዬ ነው ። የመገፋት ኑሮ እግዚአብሔርንና ተፈጥሮን ያወዳጃል ። ሰዎችን የምንፈልገው ሱስ ስለሆነብን እንጂ ስለ ፍቅር ብቻ አይደለም ። የፀጥታን ዜማ ያገኙትና ያጣጣሙት ጥቂቶች ናቸው ። አንድ ቀን ካልሠራሁ ልጆቼ ምን ይሆናሉ ? እል ነበር ። ዛሬ ግን ለዓመታት ስለያቸው የፈጠራቸው እንደሚያኖራቸው ገባኝ ።

ወደ እኔ የሚመጣው ተራ መምህር ፣ ከግሪክ ፈላስፎች ጋር የሚወዳደር ፣ የሮማውያን ጡንቻ ፣ የሄለናውያን ዘይቤ የሚያንበረክከው አልነበረም ። እርሱ ለካ መሢሕ ነው ። ከተራራው ግርጌ ያለሁትን ለመቀበል ወደ እኔ ፈጠነ ። “ጌታ ሆይ እኔ ወደ አንተ አንድ ርምጃ ስመጣ አንተ ወደ እኔ አሥር እርምጃ ትመጣለህ” አልኩት ። እርሱም ወደ እኔ እስኪደርስ ይናገር ነበር ። አእላፋትም በፀጥታ ይሰሙታል፡- “ወደ እኔ እስክትመጡ ብጠብቃችሁ ኑሮ ሳትመጡ የዕድሜአችሁ ጀምበር ይጠልቅ ነበር ። ወደ እናንተ የመጣሁት ወደ እኔ መምጣት ስለማትችሉ ነው ። መከራችንን መች አየልን እንዳትሉ ሥጋችሁን የተዋሐድሁት እኔ ነኝ ። ትንሽ ሥጋ ከመርፌ ትወጋ እንዲሉ የሥጋዬ ቁራጭ ፣ የአጥንቴ ፍላጭ ልላችሁ ፣ ዘመድ ልሆናችሁ የመጣሁት እኔ ነኝ ። በፍለጋ ደከመን ትላላችሁ ። ስገኝላችሁ ደግሞ ትሸሹኛላችሁ ። እናንተ ስማችሁን እያሰባችሁ ታፈገፍጋላችሁ ፣ እኔ ዘላለምን ሞት እያሰብሁ እጠራችኋለሁ ። ከእኔ በላይ ቢኖር እኔ ስፈርድባችሁ ያስጥላችሁ ነበር ። እኔው ከፈረድሁ ግን እኔው ካላዳንኋችሁ ማንም ይግባኝ ሰሚ አይሆንላችሁም ። … አለ ። ንግግሩን ገታ አድርጎ “አንተ ለምጻም” አለኝ ።

እኔም ደነገጥሁ ። ብሆንም ባውቀውም ፣ ራሴን እንዲያ ብዬ ብጠራውም ፣ ስሰማው ግን በረገግሁ ። ከዛሬ ጀምሮ ይህን ስም ፍቄዋለሁ ። የችግርህን ወራጅ ሳይሆን ምንጩን እደፍነዋለሁ እያለ አጠገቤ ደረሰ ። እኔም ለዘመናት ሰው ሲናገር ያልሰማሁ በረኸኛ ፣ ያልተናገርሁ አፍ ያለኝ ዱዳ ነኝና ተብረከረክሁ ። ደስታንም ለመሸከም አቅም ይፈልጋል ። እየተዝለፈለፍሁ እግሩ ሥር ወደቅሁ “ጌታ ሆይ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” አልሁት ። ውዴታ መቻል አለውና ። የፈቀድነውን ነገር ለማድረግ በቂ አቅም አለን ። ያልቻልነው ያልወደድነውን ነው ። ክርስቶስ ጌታዬ ለማንጻት ውዴታና ችሎታ አለው ። ልታነጻኝ ትችላለህ ብዬ በፊቱ ስወድቅ ራሴን ብቻ ሳይሆን ብዙ ለምጻሞችን ወክዬ ነበር ። የእኔ የሚታይ ለምጽ ነው ፣ የማይታይ የሐሜት ፣ የክፋት ለምጽ የወረራቸው አያሌ ናቸው ። ምኞት እንደ ሰጋር ፈረስ የሚጋልባቸው ፣ ፍትወት መንገድ ያሳታቸው ፣ የእውቀት አእምሮአቸውን የዝሙት አሳባቸው ያቆመባቸው ፣ እንደ ሰው ተፈጥረው እንደ እንስሳ የሚኖሩ ፣ ኃጢአትን መሰልጠን ፣ የአረማውያንን ግብር መንቃት ብለው የሚጠሩ ብዙ ለምጻሞች አሉ ። እነርሱን ሁሉ በኅሊናዬ ትከሻ ተሸክሜ አቤት ፣ አቤት እያልሁት እንደሆነ ይሰማኛል ።

ከጽድቅ ጋር ተፋትተው ስለ ጽድቅ እንቀናለን የሚሉ ፣ የውግዘት ቃላቸው የሚያስተጋባ ፣ እነርሱ ግን እውነት ያወገዘቻቸው አያሌ ፎካሪዎችም ለምጻም ናቸው ። አፍ እንጂ ጆሮ የሌላቸው ፣ በገነት የጠፉ አዳሞች ፣ በቤቱ የጠፉ ድሪሞች እነርሱም ለምጻም ናቸው ። ለምጻሞችን የለዩ ለምጻሞች ያሉባት ዓለም ናት ። እባክህን ሁላችንን አንጻን አልኩት ። ፈውሱ ቀጣይ የሚሆነው ግለሰቡ ብቻ ሳይሆን ቤቱም ሲፈወስ ፣ ቤቱ ብቻ ሳይሆን መንደሩም ሲቀደስ ነው ። ቆሻሻውን ልብሴን ፣ አውልቄ ላጥብ ያልቻልኩትን ዥንጉርጉሩን መልኬን ፣ የተጣበቀኝን ርኩሰት ፣ ከሰው የለየኝን ጠባሳ ጌታ በቃሉ ሻረው ።

“እወዳለሁ ንጻ” ሲል ደዌው ታዘዘለት ። የጠፋውን መልኬን አገኘሁት ። የተጣበቀኝን አሮጌ ልብስ አወለቅሁት ። በአዋጅ የለየኝ በአዋጅ ፈውሱን እንዲያረጋግጥልኝ ወደ ካህኑ ላከኝ ። ጌታዬ የውስጥ ደዌን ብቻ ሳይሆን የላዩንም ይፈውሳል ። ፈውሱ የተረጋገጠ እንጂ የሥነ ልቡና ጨዋታ አይደለም ። እኔም “ለምጻም ነኝ ፣ ለምጻም ነኝ” እያልሁ እንደወጣሁ አሁን ደግሞ “ንጹሕ ነኝ ፣ ንጹሕ ነኝ” እያልሁ የእስራኤልን ግዛቶች እያቋረጥሁ ፣ ደስታ ኃይል ሆኖልኝ ከመንደሬ ደረስሁ ። መልኬ የጠፋቸው አሁን ተጎብኝቻለሁና በድምፄ አወቁኝ ። ሁሉም ከየቤቱ የምስጋና ችቦውን እየመዘዘ ወጣ ። ከእኔ የመዳን ቀንዲል ላይ እየለኮሱ እልልታው በሰፈሩ አስተጋባ ። እኔም በተዝካሬ የተነሣሁ ነኝና በምስጋና ክንፎች በረርኩኝ ። ክብር ላዳነኝ ይሁን ። ቅዱስ ማቴዎስ በአጭሩ ገለጸው ። እኔ ግን አለሁ እናገራለሁ ። ሊያነጻችሁ ይችላል ደግሞም ይወዳል የረከሳችሁ ቅረቡት ። ከተራራው ክብሩ ስለ እናንተ ወርዷል ። ያላችሁበት መጥቶ ያለበት ይወስዳችኋል ….

ተፈጸመ
ሰኔ 5 ቀን 2011 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ