የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በአሳብ መለያየት መነጋገርን አይከለክልም ።

 

ወዳጄ ሆይ !

ክርስቲያን ማለት ክርስቶስ በምድር ማለት ነው ። ስለዚህ በበረት ብትወለድም በድህነት ቤትህ አትፈር ። ብትሰደድም ግብጽን አስታውስ ። ለሚያንሱህ ታዛዥ በመሆንህ ቢከፋህ በባሪያ እጅ መጠመቁን አስብ ። ያለ ስህተትህ ብትከሰስ ኃጢአት ሳይኖርበት እንደ ኃጢአተኛ የተቀጣውን መድኅን አስብ ። ሳምራዊቷን ሴት ፍለጋ በቀትር ፣ ኒቆዲሞስን ለማገልገል በእኩለ ሌሊት ትጋ ። ከቀራጮች ጋር ለመብላት ፣ ኃጢአተኞችን ለማቀፍ ዝግጁ ሁን ። ከሞት ስትነሣ ፣ ማጣትህ በማግኘት ፣ መሰደድህ በሥልጣን ሲተካ የካዱህን ጴጥሮሶች ፍለጋ ውጣ ። 

ወዳጄ ሆይ !

ያለ እግዚአብሔር መቍጠር ሲቆጥሩ መኖር ነው ። ያለ እግዚአብሔር ማሰብ መዋተት ነው ። የክርስቶስ ሰላም ገንዘብ የማይገዛው ፣ ዕረፍቱም ያማረ ቤተ መንግሥት የማይሰጠው ነው ። እግዚአብሔር ያብጀው ብለህ ስትቀመጥ እርሱ ይሠራዋል ። እግዚአብሔር ያውቃል ብለህ ስታምን በእውቀቱ ያጸድቅሃል ። ያለማቋረጥ የምትጸልየው ያለ ማቋረጥ ለመቀበል አይደለም ። 

ወዳጄ ሆይ !

ልብ ብርሃን የምትሆነው በአራት ነገሮች ነው ። የመጀመሪያው የፍቅር ፊት ስታይ ፣ ሁለተኛ መልካም ወሬ ስትሰማ ፣ ሦስተኛ ስትጸልይ ፣ አራተኛ እግዚአብሔር አዋቂ ነው ብላ ስታምን ነው ። ነፍስ ካልተረጋጋች ሥጋ ሲንቀጠቀጥ ይኖራል ። የቀኑን ትግል አንተ ትግል ትለዋለህ ፣ እግዚአብሔር ግን የጸሎት ርእስ ይለዋል ። እግዚአብሔር እንኳን በአፍህ በልብህ የተመካኸውንም ያፈርሳል ። ትምክሕት ሲሰማህ “ሁሉ ባንተ ነው ጌታዬ” በማለት ክብርን ለአምላክህ ስጥ ። በአፍህ ምስጋና ሲሞላ በልብህ ደስታ ይሞላል ። በእጅህ ስትጎርስ በልብህ አመስግን ፤ ያን ጊዜ ሆድህና መንፈስህ እኩል ይጠግባሉ ።

 

ወዳጄ ሆይ !

አምነህ እየተኛህ አምነህ መውጣትን አትፍራ ። ስትበላ ድሀ አደጎችን ፣ ስትጠጣ በበረሃ የሚኖሩትን ፣ ስትለብስ የተራቆቱትን ፣ ወደ ቤትህ ስትገባ ጎዳና የወደቁትን ፣ ስትተኛ ዕረፍት ያጡ በሽተኞችን ፣ ስትሠራ ሥራ ያጡትን ፣ ስትራመድ እግር አልባዎችን ፣ … አስብ ። ሁሉን መርዳት ባትችልም አንዱን መደገፍ የዓለምን ሥቃይ መቀነስ ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

በፈተናህ ሰዎችን ተጠያቂ ከማድረግ እግዚአብሔር ያስተማረህን ማስታወስ ያጽናናል ። ሰዎች ካደረሱብህ ጉዳት የደረሰልህ መድኃኔ ዓለም ይበልጣል ። ትንሽዋን ጎጆህን እንደ ቤተ መንግሥት ካልቆጠርካት ቤተ መንግሥት ቢሰጥህም እንደ አማረ እስር ቤት ይሆንብሃል ። በቅናት ያደገ እኔን ብቻ ይድላኝ ይላል ። በምቀኝነት ያደገ አብረን እንጥፋ ይላል ። በዝቅተኛነት ስሜት ያደገ ጌጥ የማይጠግብ ይሆናል ። 

ወዳጄ ሆይ !

ተሳዳቢን ዝም የምታሰኘው ስድቡን ስትዝናናበት ነው ። የሚቀኑብህን የወለደው ያለህ ነገር ነው ። ቅናት ከፍ ያለበት ሰው በበሽተኛም ይቀናል ። ለምታስለቅስህ ዓለም ስቀህ ጠብቃት ። ይህ ከንቱ ዓለም እንደ ውሻ ሲሮጡለት ይከተላልና ደፍረህ ፈተናን ተጋፈጥ ። ካልደፈረሰ አይጠራም ስትል መጀመሪያ ያንተ ቤት እንዲደፈርስ መፍቀድ አለብህ ። በሌላው ሞት “እግዚአብሔር ሰጠ ፣ እግዚአብሔር ነሣ” ትላለህ ፣ ባንተ ጉዳይ ግን “እኔ አገኘሁ ፣ እግዚአብሔር ወሰደ” ባይ ነህ ። 

ወዳጄ ሆይ !

ትምህርት ሰብእናን ካልገነባ መቅረት አለበት ። ማለዳ ስትነሣ ምንም የለኝም አትበል ፤ ገና ያልተነካ የ24 ሰዓት ሀብት አለህ ። ቤትህ ሲቃጠል እየጮኽ ፣ በሲጋራ እሳት አንተ ባለቤቱ ስትቃጠል ግን ዝም ትላለህ ። ያለ ራእይ የሚኖር ብዙ ነው ፣ ያለ ራእይ የተፈጠረ ግን አንድም የለም ። አንተ ባለቤቱ ካልታየህ ሰዎች ስላዩልህ አትራመድም ። ትዳር ማለት አብሮ መወለድና አብሮ መሞት ሳይሆን አብሮ መጓዝ ነውና ተስማማ ። በአሳብ መለያየት መነጋገርን አይከለክልም ። 

መድኅን ክርስቶስ ሆይ የተለያዩትን አንድ አድርግ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ