ወዳጄ ሆይ !
የቀሳውስትና የጳጳሳት ረድዕ ስትሆን አገልግሎትህን በክብር ለመፈጸም ምሥጢር ጠባቂ ሁን ። የገዳም አበምኔት ስትሆን አባትና እናታቸውን ትተው ለመጡ መነኮሳት አባትና እናት እንደሆንህ እወቅ ።
ወዳጄ ሆይ !
መሠዊያ መሥዋዕትን ይጣራል ፣ መሥዋዕትም መሠዊያ ይፈልጋል ። ክርስትናም ዋጋ ከፋዮችን ይሻል ። ክርስቲያኖችም መሥዋዕት የሚሆኑለትን ዓላማ በትክክል ማወቅ አለባቸው ። ያለ ዋጋ የኖረ መልካም ነገር የለምና ያለ ዋጋም ነገ ላይ ማድረስ አይቻልም ።
ወዳጄ ሆይ
ወይን ጠጣ ብለው ግድ ሲሉህ እንዳይቀየሙኝ ብለህ አትጠጣ ። ራስህን መግዛት አቅቶህ ከሚታዘቡህ በቁጥብነትህ ቢቀምሁ ይሻላል ።
ወዳጄ ሆይ !
አገልጋይ ሆነህ ስትታዘዝ አትከፋ ። ክርስቶስ የመጣው በባሪያ መልክ ነውና ። እርሱ በጌትነት አርአያ ቢመጣ አይደንቅም ነበር ። የዘላለም ጌታ በባሪያ መልክ መምጣቱ ግን ድንቅ ነው ። አገልጋይነትን ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ የባረከው ተግባር ነውና ደስ ይበልህ ። አንተ የሰው አገር ተሰድደህ ተመችቶህ እንኳ ከፍቶህ ከሆነ ክርስቶስ ግን ወደማይመቸው ወደ ሲና በረሃ እንደ ተሰደደ አስታውስ ። አንተ ለምነህ እንጀራ ስታገኝ በእንባ ትጎርሰዋለህ ፣ ክርስቶስ ግን በመስቀል ላይ ተጠማሁ ብሎ ሆምጣጤ እንደ ሰጡት አስብና ትሑት ሁን ። አንተ በራስህ መቃብር ስትቀበር ክርስቶስ ግን በተውሶ መቃብር እንደ ተቀበረ እወቅ ።
ወዳጄ ሆይ !
ማወቅ መልካም ነው ። የታላላቅ ሰዎችን ምሥጢር ለማወቅ መታደልም ደስ የሚል ነው ። ታላላቅ ሰዎች ከሰው የደበቁትን ምሥጢር ከነገሩህ በአንገትህ ሰይፍ ይዘህ እንደምትዞር እወቅ ። ዝምታና የምሥጢር መቃብር መሆን ብቻ ዕድሜህን ያረዝማል ።
ወዳጄ ሆይ !
የምንሮጠው ለየራስ ነው ፣ የምንመገበው ግን ተመሳሳይ ነው ። አንዱ ያለ ዕረፍት ይሮጣል ፣ ሌላው እያረፈ ይሠራል ። የሚመገቡት ግን ተመሳሳይ ነው ። ወንዝ ብትወርድ የወንዙን ውኃ በሙሉ አትጠጣም ። እሸት ብትበላ የእርሻውን ፍሬ በሙሉ አትበላም። ተፈጥሮ ራሱ ልክህን እየነገረ በቃ ይልሃል ። ስለሚያስፈልግህ እንጂ ስለምትፈልገው ነገር አእምሮህን ሰላም አትንሣ ።
ወዳጄ ሆይ !
ወፍ በቅርንጫፍ ፣ አይጥ በጉድጓድ ፣ ጉማሬ በባሕር ፣ ዝንጀሮ በገደል ፣ መላእክት በሰማይ ፣ ሰው በምድር ይኖራሉ ። ቅርንጫፍን መኝታ ፣ ጉድጓድን መኖሪያ ፣ ባሕርን ቤት ፣ ሰማይን አገር ፣ ምድርን ተስማሚ ያደረገ እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔር የመደበልህ ቦታ ከአደጋና ከሞት የምትተርፍበት ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
ባለመቻልህ አትበሳጭ ፣ ሰው ሁሉ ቢችል ኖሮ አንተን የሚያኖርህ ፣ አንተም የምታኖረው አይኖርም ነበር ። አለመቻል ጭምትና ጸሎተኛ ያደርጋልና ውደደው ። ምኞትህን እግር ካልሰጠኸው እያደከመህ ይመጣል ። እግዚአብሔር የሚባርከው ምኞትህን ሳይሆን ተግባርህን ነውና የተግባር ሰው ሁን ።
ወዳጄ ሆይ !
ውኃ ራሱን ሳያረካ ሌላውን እንዳረካ ይኖራል ። ሌላውን ለማንጻት ብሎም ይቆሽሻል ። አንተ ግን ረክተህ የምታረካ ፣ ተቀድሰህ የምትቀድስ ሁን ። የሚበቃህን ካላወቅህ ከሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከገዛ ተፈጥሮህ ጋርም ግጭት ውስጥ ትገባለህ ። ቢፈቅዱልህም በሰዎች ነጻነት ውስጥ አትግባ ።
ወዳጄ ሆይ !
ዮሴፍ በከነዓን ሲሸጥ በግብጽ ይገዙታል ። አንተም አንድ ቦታ አይፈልጉህም ሌላው ቦታ ግን በውድ ይገዙሃል ። ዮሴፍ ወንድሞቹ ሲገፉት ባዕዳን ይቀበሉታል ። እግዚአብሔርን የሚያውቁ ሲከፉበት አያውቁም የሚባሉ ይራሩለታል ። ወኅኒ ጣልነው ሲሉ ቤተ መንግሥት ያገኙታል ። መገፋትህ የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ይሆናልና ደስ ይበልህ ። እልፍ ስትልም እልፍ ታገኛለህ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 19 ቀን 2013 ዓ.ም.
https://t.me/Nolawii
እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣ ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ