ሰውዬው ሀብታም ናቸው አሉ ። የእናታቸው ነገር ያሳስባቸው ነበር ። በሕይወት አሉ ቢባል ለመሄድ ስንፍና ይዋጋቸዋል ፣ ሞቱ ቢባል ባለመጦራቸው ኀዘኑ ታላቅ እንደሚሆንባቸው ያስባሉ ። አሳብ እግርን አይተካምና ዘመን አልፎ ዘመን መጣ ። አንድ ቀንም ሎሌውን ይጠሩና፡- “ቆላ ወርደህ የእናቴን ነገር ተመልከትና ስትመለስ ፣ ጤና ሆናም እንደሆነ ፣ ሞታም እንደሆነ አትንገረኝ” አሉት ። ሎሌውም የተባለበት ቦታ ደርሶ አጥሩ አጠገብ ሲደርስ ሰዎች ይሯሯጣሉ ። እኒያ የሀብታሙ እናት ሞተው አርባቸውን ለማውጣት ወዳጅ ሁሉ ይሯሯጣል ። ያም ሎሌ በረፈደው ሰዓት አዝኖ ሊመለስ ሲል የተሰጠው ትእዛዝ ትዝ አለው ። “ጤና ሆነውም እንደሆነ ሞተውም እንደሆነ አትንገረኝ” ያሉት እንደገና በጆሮው አቃጨለ ። በመጨረሻም ግማሽ ፀጉሩን ተላጭቶ ፣ ግማሹ ፀጉሩን አጎፍሮ ተመለሰ ። ጌታውም የተላጨውን አይተው፡- “ምነው ደህና አይደለም ወይ ? እናቴ ሞተች እንዴ ?” ሲሉ ሎሌውም፡- “ቢሞቱ ኖሮ መች ፀጉሬን አጎፍር ነበር” አላቸው ። “ታዲያ እናቴ ደህና ነች ወይ ?” ቢሉት “ደህና ቢሆኑ መች ፀጉሬን እላጭ ነበር” አላቸው ። በዚህ ጊዜ ተናደዱና፡- “ለምን በቅጡ አትነግረኝም” አሉት ። እርሱም፡- “መች በቅጡ ላኩኝና” ብሎ መለሰላቸው ይባላል ።
መስማት የማንፈልገው ክፉ ነገር አለ ። መሥራት የሚያስፈልገንን ግን አናከናውንም ። ስናስበው የሚዘገንነን ነገር ብዙ ነው ። መምጫውን ለመዝጋት ግን ከአልጋችን አልወረድንም ። ውለታቸውን እያሰብን በእንባ የምናስታውሳቸው ሰዎች አሉ ። ቆርጠን ግን ሄደን አንጠይቃቸውም ። “ለእገሌ ይህን በሽታ ይስጠው !” እያልን ከእንቅልፍ ነቅተን የምናዝንላቸው ሰዎች አሉ ፣ በጠዋቱ ግን ሄድን ከመጠየቅ የፌዝ ጓደኞቻችንን ስናስስ እንውላለን ። ይህ ነገር አስቸኳይ ነው በማለት ልባችን በስጋት ይደልቃል ፣ የማያስቸኩልና የማያስፈልግ ነገር ላይ ግን ተጥደን እንውላለን ። “እገሌ እኮ” ሲባል “አሁን ሳስበው ነበር” በማለት የወሬ ጨው ጣል እናደርጋለን ፣ አሁን ተነሥተን ለመጎብኘት ግን ልምሾ እንሆናለን ። “ለእገሌ ውለታ አንድ ጥሩ ቤት ገዝቼ ባሳርፈው” እንላለን ፣ ዛሬ የሚፈልገውን ዳቦ ለመስጠት ግን እንለግማለን ። እገሌም ታዲያ እኛን ሲያስብ “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ ፣ ገብስ የሚደርሰው ለፍልሰታ” እያለ ያዝንብናል ። የረፈደ ደግነት ከንፍገት እኩል ነው ። በጊዜው ያልሆነ እርዳታ ኪሣራ ነው ። “ለእገሌ ቆንጆውን የሬሳ ሳጥን አድርጉለት ብለን ገዝተናል ፣ በቁሙ ግን ይህችን ለቤት ኪራይ አውላት አላልነው ። የሬሳ ስፖንሰር መሆን ያስደስተናል ፣ የቁም ረዳት መሆን ግን ይቀፈናል ። “እገሌ ቤት እሄድ የነበረው ሲርበኝ ነው ፣ እርሱም እንዲህ አድርጎ ይጋብዘኝ ነበር” እንላለን ፣ “ራበኝ” ብሎ ደውሎ ግን ጨክነንበታል ።
ሞቱን መስማት የማንወደውን ሰው ኑሮውን እናጣፍጥለት ። መታመሙ የሚቆረቁረንን እንዳይታመም ትንሹን በሽታ እናክምለት ። “እርሱ እኮ የልጆቹ ነገር አያስችለውም” ከማለት ልጆቹ ሲቸገሩበት ቀኑን እናብራለት ። “እርሱ እኮ ሰው የጠገበ አይመስለውም ነበር” ከማለት የአንድ ቀን ምግቡን እንግዛለት ። ያልተመለሰ ደግነት ዕዳ ነው ። እግዚአብሔር ዛሬ በእጃችን በረከት ሲያኖር በበረከታቸው ያሰቡንን እንድናስብ ነው ። እነርሱ በረከታቸውን ወደ ራሳቸው ብቻ ቢያፈስሱ ኖሮ ዛሬ አንደርስም ነበር ። እኛም በረከታችንን መልቀቅ አለብን ። እግዚአብሔር የሚጎርስ ብቻ ሳይሆን የሚያጎርስ እጅ እንደሰጠን እናስተውል ።
ስለ እናቱ እያወራ ሃያ ዓመት በሰው አገር የቀረ ሰው አለ ። ስለ አባቱ እየተናገረ ከአገር ከወጣ ሠላሳ ዓመት የሆነው አለ ። የእናቴን ክፉ አያሰማኝ እያለ እጆቹ ግን ዱሽ የሆኑ ስንት ሰው አለ ! ጸሎት ተግባር ፣ ተግባርም ጸሎት መሆኑን የረሳ ብዙ ነው ። ስልክ እንኳ ደውሎ ፣ ራሱ መጥቶ የማያይ በሰው ሰው የራሱን ወገን የሚጠይቅ ፣ እናቱን የጎረቤቱ ጥገኛ ያደረገ ፣ ከእገሌ ውሰጂ እያለ ሰው ያየውን ስጦታ የሚያበረክት ብዙ አለ ። ሰው ያየው ስጦታ አይበረክትም ። ሰው ያየው ስጦታ የሚያየውን ለምቀኝነት ፣ የሚቀበለውን ለመሳቀቅ ይዳርጋል ። ምንም ነገር መስማት አልፈልግም ብለው ስለ አገር ፣ ስለ ሕዝባቸው ጆሮአቸውን ጠቅጥቀው የሚኖሩ አሉ ። አትንገሩኝ በማለት የሞተው ሳለ የሰሙት የሚንጣጡበት ብዙ ቲያትር አለ ። “የምጣዱ ሳለ ፣ የእንቅቡ ተንጣጣ” ይባላል ። እሳቱ ላይ ያለው የምጣዱ ታግሦ ፣ የበረደው እንቅብ ላይ ያለው አቃጠለኝ ማለቱ የማይመስል ነገር ነው ። አንዳንድ ነገሮችን በመልእክተኛ ሳይሆን ራሳችን ማየት አለብን ። ደብዳቤ እንደ ቃል ፣ ጆሮም እንደ ዓይን አይሆንም ። አገሩንም መጥቶ ማየት ፣ ወገንንም ቀርቦ መዳሰስ ይገባል ። የኖርንበትን ሰፈርና ቤት ፣ አብሮ አደግ ጓደኞች ፣ ያሳደጉንን ሽማግሌዎች ለማየት የማንጓጓ ከሆነ ፣ አቅም እያለንም ቆርጠን ካልተነሣን ከሰውነት አንሰናል ማለት ነው ።
ሁልጊዜ ስለዚያ ሰው ደግነት የምናወራላቸው ሰዎች እግራችን ሰንፎ ፣ አፋችን ሲተጋ ይታዘቡናል ። “እንዲህ እየወደድከው እንዴት እስካሁን አስቻለህ” ይሉናል ። የትዝታን እሳት መሞቅ እንጂ የዛሬን ፍቅር መግለጥ አለመቻል ትላንትን መኖር ፣ ዛሬን መሞት ነው ። የምንልካቸው ሰዎች ራሱ ሄዶ ቢያይ ይላሉ ። የማንጨነቅ ከሆነ ይጨነቁልናል ። ስንደነድን ሌሎች ይፈሩልናል ። ለእናታችን ከእኛ ይልቅ ጓደኛ አይቀርብም ። ለአገራችንም ከእኛ ይልቅ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች አይቀርቡም ። የሚያሳስቡንን ነገሮችን በጸሎትና በተግባር ልንወጣቸው ግድ ይላል ። አሊያ ወደፊት ላለመደሰት በራሳችን ላይ እንፈርዳለን ። ሰዎች ቆመው የሚጠብቁን አይደሉም ። በዛሬው ዘመን ከተሞች እንኳ እየፈረሱ ፣ ሐውልቶችም እየወደቁ ፣ ቅርሶችም እየወደሙ ነው ። ሰው ከእነዚህ ይልቅ ለማለፍ ስንዱ ነው ። ሞትን ተሸክሞ የሚጓዘውን ወዳጅ በቶሎ ማየት ከጸጸት ይጠብቃል ። በዚህ ዓለም ላይ ያለው ትልቁ ዋጋ ተገናኝቶ መጨዋወት ፣ ፍቅርን መግለጥ ነው ። እየቻልን ማርፈድ ኃጢአት ነው ።
ግልጽ ተልእኮ ግልጽ ግብ ይኖረዋል ። ሰዎች በቅጡ እንዲመልሱልን በቅጡ ልንልካቸው ያስፈልጋል ። ለዚህ ደግሞ ራእይ መሠረት ፣ ዓላማ ሕንፃ ፣ ተልእኮ ምሰሶ ፣ ጉልላት ግብ ሆነው መቀመጥ አለባቸው ። ባልገባን ነገር ላይ መተንተን ፣ በማናውቀው ነገር ላይ አሳብ መስጠት ፣ ሰዎች ሲሉ የሰማነውን ራእዬ ነው ማለት ፣ ሠርቶ ከመብላት ሰዎች የሠሩት ላይ ታጥቦ ቀረብ ማለት የትም አያደርስም ። በቅጡ ያልላክናቸው ሰዎች በቅጡ ባይሠሩ የሚደንቅ አይደለም ። ዝም አላልኩም ብለን የምንልከው ፣ የተልእኮውን መልስ ለመስማት የማንፈልገው ነገር ከሆነ መናገራችንም መላካችንም የውሸት ነበር ማለት ነው ። የእናታችንን መኖርም መሞትም መስማት የማንፈልግ ከሆነ መስማት የምንፈልገው የራሳችንን ነገር ብቻ ነው ። ባሕላዊው የፖለቲካ ብሒላችን፡- “እንዳያማህ ጥራው ፣ እንዳይበላ ግፋው” ይላል ። ደግሞም፡- “ውጣ አትበለው ፣ እንዲወጣ አድርገው” ይባላል ።
ምድራችን ፣ አገልግሎታችን ፣ ራእያችን ግማሽ ልጩ ፣ ግማሽ ጎፈሬ ነው ። አለ እንዳይባል የሞተ ነገር ይታያል ፣ የለም እንዳይባል የሕይወት ምልክቶች ይታያሉ ። ነገር ግን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ ከሕይወት ይልቅ ለሞት ይቀርባል ። ጎፈሬው መስማት ለምንፈልገው ነገር ነው ። ልጩው ደግሞ ለእውነቱ ነው ። መስማት የምንፈልገውና የሆነው ነገር በጣም የተለያየ ነው ። ለዚህም እግር የሌለው አሳባችን ፣ ጊዜን የማያከብረው ራእያችን ፣ ግልጽ ነገር የሌለው ተልእኮአችን በዋናነት ተጠያቂ ነው ።
ስለዚህ ቀዳሚ ተግባራችንን መለየት አለብን ። ለተግባራችንም ራሳችን መነሣት አለብን ። እውነት ተሰምቶን ከሆነ ነገ ማለትን መጠየፍ አለብን ፣ አሁን መጀመር አለብን ።
ጌታ ሆይ ግማሽ ልጩ ፣ ግማሽ ጎፈሬ የሆነውን ኑሮአችንን ነፍስ ዝራበት ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም.