መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ቅድስት ዓርብ/ቀዳም ሥዑር

የትምህርቱ ርዕስ | ቅድስት ዓርብ/ቀዳም ሥዑር

ፌኒሎን ተመስጦውን እንደ ጻፈው

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሚያዝያ 10 ቀን 2012 ዓ.ም.
www.ashenafimekonen.blogspot.com
ቀዳም ሥዑር ከክርስቶስ ሞት እስከ ትንሣኤው ድረስ ያለውን ፤ ይህም ሥጋው በጨለማ መቃብር ውስጥ የነበረበት ጊዜ የሚወክል ነው ። በዚህ (የተመስጦ ጽሑፍ ውስጥ) ፌኒሎን የተባለ ፀሐፊ እግዚአብሔር የራሱን ሕይወት ነጥቆ ከኢየሱስ ሞቱ ጋር ኅብረት ያደርግ ዘንድ እንደሚሻ ይናገራል ። እግዚአብሔር ይህንን ሥራ በእኛ ይሥራ ዘንድ ስንፈቅድ እንዲህ (ይሆንልናል) ብሎ ይጽፋል፡- “የማይወሰን ፍቅር በእኛ ውስጥ ያፈቅራል፣ ፍቅራችንም የእግዚአብሔር የራሱን ጠባይና መልክ ይይዛል” . . . መልካም ንባብ!
*****
ዛሬ ወደ ሕሊናዬ የሚመጣው ኢየሱስ መከራ የተቀበለበት ሞትና እንደገና የሚቀጥለው ሕይወት ። ትንሣኤው ከሞቱ ያነሰ እውነት አይደለም ። ሞቱም ከሥቃይና ከመከራ ሕይወት ወደ ደስታና ሐሤት የሚደረግ ጉዞ ነው ። አዳኝ ሆይ ! አመልክሃለሁ ፣ በመቃብር ውስጥ እወድሃለው ፣ በመቃብር ውስጥም ራሴን በአንተ አለብሳለው እሸፍንማለሁ ። ከዚህ በኋላ ዓለም ትመለከተኝ ዘንድ አልሻም ። ከዚህ በኋላ ራሴንም እመለከት ዘንድ አልሻም ። ወደ ጨለማና ወደ ትቢያነት ወረድኩ ። ከሕያዋን ጋር ዳግም አልቆጠርም ። ሙታን ይርሱኝ ከእግራቸው በታችም ይረማመዱብኝ ! እኔ ሞቻለሁ ለእኔ የተዘጋጀልኝ ሕይወትም በእግዚአብሔር ዘንድ ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአለና።[1] 
እነዚህ ድንቅ እውነታዎች ናቸው። ። ስለዚህ “ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?” (ሮሜ 6፥3) የሚሉት የሐዋርያው ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? በእኛ ይሠራ ዘንድ የሚገባው ይህ የክርስቲያንነታችን ምልክት የሆነው ይህ ሞት ወዴት ነው ? ይህ የመቃብር ቦታስ ወዴት ነው ?

እኔ እታወቅ ፣ እመሰገን ፣ ልዩና ዝነኛ እሆን ዘንድ መፈለጌ እንዴት ያለ ጨካኝነት ነው ? ለጎረቤቶቼ የሚያስቡበት አንዳች ነገር እሰጥ ዘንድ እፈልጋለሁ ፣ የጎረቤቶቼን ልብ እቆጣጠርና እሞላ ዘንድ ፣ ራሴን በስመ ጥርነትና በወዳጅነት ውስጥ ጣኦት አደርግ ዘንድ እፈልጋለሁ ። በመሠዊያው ላይ የሚጤሰውን ትንሽ ዕጣን ከእግዚአብሔር መስረቅ የእግዚአብሔር የሆነውን መውሰድ ከሚሻና ራሱን ሌሎች ፍጡራን ላይ ጣኦት ማድረግ በመሻት ነፍስን ከሚሰርቅ የረከሰ ተግባር ጋር ሲነጻጸር ምንም ነው ።
ውዱ እግዚአብሔር ሆይ ፣ ሰዎች እንዲወዱኝና በክብር እንደሚመለከቱኝ ራሴን ማፍቀርና መውደድ መቼ ነው የምተወው ? ፍቅር ላንተ ብቻ የተገባ ነው ። በአንተ ፣ ለአንተና ላንተ ካለኝ ንጹሕ ፍቅር ውጪ አንዳች ነገር ላለማፍቀር ቆርጫለሁ ። እንደ እንግዳና መጻተኛነቴ ንጹሕ ከሆነ ክርስቲያናዊ በጎነት ካልሆነ በስተቀር ራሴን አፈቅር ዘንድ አይገባኝም ። ሌሎች እንዲወዱኝና እንዲያፈቅሩኝ ስፈልግና ስሻ ማፈር አይገባኝምን ?
ከንቱ የሆነው ስሜታዊነቴ በክርስትና በጎነት ከሚገኘው ፍቅር አይረሰርስም። ጨለምተኛና አስከፊ የሆነው ኩራትና ትዕቢቴ “ይህ ፍትሐዊ አይደለም! በእርሱ ላይ አምፃለሁ !” ይላል ። እግዚአብሔር ሆይ ኩራትና ትዕቢቴን ቅጣው ። እኔ ካንተ ጋርና ላንተ ነኝና ከራሴ በተቃራኒ እሆናለሁ ። ከከንቱነቴ በተቃራኒ ላለው ላንተ ክብርና ፍትህ እወግናለሁ ። ራስህን የምታመልክ ከንቱ ፍጥረት ! ስለዚህ ከእግዚአብሔር ውጪ ምን አለህ ? ክርስቲያናዊ በጎነት ላይ ያልተመሠረተው የዚያ ደማቅ ፣ ኅብረትና የፍቅር ግንኙነት መጨረሻ ምንድን ነው ? እንዲህ ያለ ኢፍትሐዊነት ሲሰማንና እግዚአብሔር ለራሳችን እንዳናደርግ የከለከለንን ነገር ሌሎች ለእኛ ያደርጉልን ዘንድ ስንሻ እንዴት ክርስቲያናዊ በጎነትን እንሻለን ።
እግዚአብሔር በፍጡራኑ ላይ ፍቅርን አትሟል ። ፍቅርን እንዲህ እናደርገው ዘንድ ነው የእርሱ ፍላጎት ? እርሱ ማፍቀር እንችል ዘንድ አላደረገንምን ? ይህንን ያደረገልንስ እያንዳንዳችን ይህ ንጹሕ ፍቅር ካለው ብቸኛ ዓላማና ምክንያት ዘወር እንል ዘንድ ነውን ? እግዚአብሔር ሆይ እንዲህስ አይደለም! ሰዎች ያፈቅሩኝ ዘንድ አልሻም ። ሰዎች ላንተ ካላቸው ፍቅር የተነሣ በትንሹ ያከብሩኝ ዘንድ ነው የሚገባው ። ጎረቤቶቼ ለእኔ ስላላቸው ፍቅር ካወቅሁና ከተሰማኝ ለፍቅራቸው አብዝቼ ያልተገባሁ እሆናለው ከእኔ ይወሰድ ዘንድም አብዝቼ እፈልጋለሁ ።
ጌታ ሆይ ይህ ስለ ዝና ሆነ ስለ ወዳጅነትም እውነት ነው ። እንደ ፈቃድህ ስጥ ውሰድም። ለአንተ ክብርን የሚሰጥህ ከሆነ ከራሱ ከሕይወት በላይ ለእኔ ውድ የሆነው ዝና ለእኔ እንደ መርገም ጨርቅ ይሁንብኝ ።[2]በመቃብር እንዳሉ ሙታን ሰዎች ደጋግመው ተላልፈውኝ ከሄዱ ፣ ሰዎች እንደ ምንም ከቆጠሩኝ ፣ ሰዎች ከጠሉኝ ፣ ሰዎች ከአንዳች ነገር ካላተረፉኝ ይህ ጥሩና መልክም ነው ። አሁንም በውስጤ ከነገሮች ጋር ያለ በፈቃድ የሆነ ቁርኝት፣ ዝናና ክብርን የማግኘት ስውር የሆነ ፍላጎት በውስጤ ካለ ከክርስቶስ ጋር አልሞትሁም የትንሣኤውን ሕይወት እየተካፈልኩ አይደለም ።[3]
ወደ አዲሱ ሰው ሕይወት የምንሻገረው ከክፋት ፍጹም መወገድና ከአሮጌው ሰው ብልሹ ሕይወት ሙሉ መጥፋት በኋላ ነው ።[4] ሁሉም ነገር መሞት አለበት ። ምቾት ፣ መጽናናት ፣ የአእምሮ ሰላም ፣ ጠንካራ ወዳጅነት ፣ ክብር ፣ ዝናና ስም እነዚህ ሁሉ መሞት አለባቸው ። ሁሉም ነገር መቶ እጥፍ ሆኖ ይሰጠናል ነገር ግን (አስቀድሞ) ሁሉም ነገር ይሞት ዘንድ ይገባዋል ።[5]ሁሉም ነገር ይሠዋ ዘንድ ይገባል ። በእኛ ዘንድ ሁሉንም ነገር ስናጣ ሁሉንም ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ እናገኘዋለን ። በእኛ ዘንድ የነበረን ንጽሕና የሌለው አሮጌ ሰዋችን በአዲሱ ሰውነት ንጽሕና ተመልሶ ይሰጠናል ። እሳት ውስጥ የሚገባ ብረት እውነተኛና ንጽሑ ባሕርይውን እንደማያጣ በተቃራኒው ዝገቱና ቆሻሻቸው እንደሚነጥሩና እንደሚነጹ (በእኛም ዘንድ እንዲህ ነው) ።[6]
ውዱ እግዚአብሔር ! በዚህ ምክንያት በእኛ ውስጥ የሚቃትተውና የሚጸልየው ያ መንፈስ ቅዱስ ራሱ በእኛ ውስጥ አብዝቶ ፍጹም በሆነ አፈቃቀር ያፈቅራል ።[7]ልባችን እንዴት አብዝቶ ታላቅ ይሆናል ፣ እንዴትስ አብዝቶ ቀናተኛ ፣ ቸርና ደግ ይሆናል ! በጠባብ ድንበር ተወስነን እንደ ደካማ ፍጡራን ነንና አናፈቅርም ። የማይወሰን ፍቅር በእኛ ውስጥ ያፈቅራል ፣ ፍቅራችንም የእግዚአብሔር የራሱን ጠባይና መልክ ይይዛል ።
በሥቃዩና ጣረ ሞቱ ወቅት፣ በሞቱና በመቃብሩ ውስጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ራሳችንን አንድ ማድረግንና መተባበርን ብቸኛ አሳባችንና ዓላማችን አድርገን እንያዝ ። በንጹሕ እምነት ራሳችንን በጨለማ ሌሊቶች እንቅበር ። ራሳችንን ለሞት ፍርሃትና ድንጋጤ አሳልፈን እንስጥ ። እኔ ራሴን እንደዚህ ዓለም ፍጥረት በፍጹም መመልከት አልሻም ። እኔ እየረሳሁት እንዳለሁ ፣ ራሴንም መርሳት እንደምፈልገው ዓለሙ ይርሳኝ ! ጌታ ኢየሱስ የሞትከው እኔ እሞት ዘንድ ብቻ ነው ። ሕይወቴን በኃይል ውሰድ ። ከዚህ በኋላ እተነፍስ ዘንድ አታድርገኝ ። አንዳች ነገር መልሼ እንድይዝ አታድርገኝ ። ልቤን እስከ መጨረሻው ድረስ ግፋት ። መሥዋዕቴ ላይ ገደብና ድንበር አላበጅም ። 


[1] በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና  . . . “ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።” ቆሎ 3፥3
[2]የመርገም ጨርቅ . . . . “ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።” ኢሳ 64፥6
[3] ከክርስቶስ ጋር አልሞትሁም . . . ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን። ሮሜ 6፥7-8
[4]አዲሱ ሰውና አርጌው ሰው . . . “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” ኤፌ 4፥22-24
[5]ሁሉም ነገር መቶ እጥፍ ሆኖ ይሰጠናል . . . ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም። ማር 10፥29–30
[6]ከዝገትና ቆሻሻቸው እንደሚነጥሩና እንደሚነጹ . . . “ሦስተኛውንምክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ እኔም። ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ እርሱም፦ እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል።” ዛካ 13፥9
[7] በእኛ ውስጥ የሚቃትተውና የሚጸልያው . . . “እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” ሮሜ 8፥26።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ