የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማትረሳ

 ተስፋ ያደረግሁት ከእኔ ቢርቅም አንተ ግን በአማኑኤል ስምህ ከእኔ ጋር ሁን ። ያከበርኩት ቢያዋርደኝ አንተ ግን በወርቀ ደምህ መገዛቴን ንገረኝ ። አለኝታ ያልኩት ደጁን ቢዘጋብኝም አንተ ግን የጠፋው ልጅ አባት ሁነኝ ። አስታዋሼ ያልኩት ፍጹም ቢረሳኝም አንተ ግን የማትረሳ እምዬ ነህ ። የእኔ ያልኩት እንደ በረዶ ቢሟሟም አንተ ግን የማታልቅ ሀብቴ ነህ ። ይጠግነኛል ያልኩት ቢሰብረኝም አንተ ግን ሐኪሜ ነህ ። ያድነኛል ያልኩት ቍስሌን ቢያድሰውም አንተ ግን አዲስ ራእይ የምትሰጠኝ ነህ ። ይመጣል ያልኩት ቢቀርም አንተ ግን ቀጥረህ የማትቀር ነህ ። ያልታየውን አየሁልህ የሚል  ሸንጋይ ቢገጥመኝም አንተ ግን ዓይኔ ነህ ። ላይደርስልኝ ቆይ መጣሁ እያለ ቢያዘናጋኝ አንተ ግን ደመናን ጠቅሰህ ፣ ባሕር ተራምደህ ትመጣለህ ። ለካባ ያሰብኩት ቀሚሴን ቢወስደውም አንተ ግን የጽድቅ ሸማዬ ነህ ። ይሰውረኛል ያልኩት ቢያጋልጠኝ አንተ ግን የመማጸኛ ከተማዬ ነህ ። ይደርስልኛል ያልኩት እልም ቢልም አንተ ግን በረከቴ ነህ ። ለትርፍ ክፍያ ስጠብቅ ደመወዜን ባጣም አንተ ግን መኖሪያዬ ነህ ። በግራዬ ሰዎች ቢከዱኝ አንተ ግን በቀኜ ወዳጆች ታመጣልኛለህ ። ቀኑን ሳልገምት ቢደርስብኝም አንተ ግን ቀድመህ አዘጋጅተህልኛል ። ጉልበቴ የከዳኝ ቀን አንተ ግን ተነጥፈህልኛል ። ልነሣ ስል አልጋ ላይ ስቀር አንተ ግን አስታመኸኛል ። የተንተራስኩት ክንድ ሲዝል አንተ ግን ችለኸኛል ።
ይወደኛል ያልሁት ቢጠላኝም አንተ ግን ውዴ ሆነህልኛል ። ያድነኛል ያልኩት ገዳይ ቢሆንም አንተ ግን መርዙን አርክሰህልኛል ። መኖሬን ስጠራጠር አንተ ግን ብዙ ቀን ጨምረህልኛል ። ይሾመኛል ያልኩት ቢያዋርደኝም አንተ ክርስቶስ አክብረኸኛል ። ናልኝ ያልኩት ቢቀርም አንተ ግን ሳትለየኝ ፈጥነህ ደርሰህልኛል ። የከበቡኝ ሲበተኑ አንተ ግን መላእክትን አዝዘህልኛል ። ይለምኑልኛል ያልኋቸው ቢዘርፉኝ አንተ ግን ቅዱሳንን ሰጥተኸኛል ። ያዝንልኛል ብዬ ቍስሌን ያሳየሁት ጥዝጣዜ ቢጨምርብኝ አንተ ግን ዳሰኸኛል ። አለቀ ያልኩት ገና እንጭጭ ቢሆንም አንተ ግን የዳርቻዬ አዛዥ ነህ ።
ተስፋዬ ሆይ በእኔ አቆጣጠር ዘገየህ ። ወይ ቶሎ ና  ወይ ልቤን ትዕግሥት ሙላ ። ውስጤን ሳስበው ገና በዓለም ለመኖር እከጅላለሁ ። በአፌ ማራናታ ፣ በልቤ ቆይ ጌታ እላለሁ ። ገልብጠህ ስማኝ ፣ እንደ ልቤ ሳይሆን እንደ አፌ አድርግልኝ ። እንደ እኔ ሳይሆን እንደ አንተ ይቅር በለኝ ። አለው ያሉኝን ደግ ነገር እባክህ ጨምረህ ስጠኝ ። አላመኑኝም ብዬ በሰው ከማዝን አምንሃለሁ ብዬ ባንተ መደሰት አብዛልኝ ።
ወዳጅ ሆይ በቃልህ ያልተማርን በሬሳ አንማርም ። እኛን ለማስተማር ዘመኑን ብታስጨንቅም ፣ ስትለቀን ያው ነን ። እባክህ ዝም ብለህ ወዳንተ መልሰን ። አሳዳጁን ጳውሎስን ገንዘብ ያደረግህ እኛንም ለክብርህ ለመኖር አብቃን ። እናቱን እንደ ናፈቀ ልጅ መምጫ መምጫህን እያየን እንኑር ። ቀኑ ሳያልቅብኝ ምስጋናዬን ላቅርብልህ ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይገባል ። ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 23
ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ