የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጻፍክልኝ ሕይወት ነው

የጻፍከኝ በብራና አይደለም ፣ የጻፍከኝ በልብህ ነው ፤ ስለዚህ ሊሰርቅ የሚመጣው ሌባ አያገኘኝም ። የጻፍከኝ በቀለም አይደለም ፣ የጻፍከኝ በደምህ ነው ፤ ስለዚህ የጠላት ብዛት አያጠፋኝም ። የጻፍከኝ በአሸዋ ሰሌዳ አይደለም ፣ የቀረጽከኝ በዓለት ላይ ነው ፤ ስለዚህ የዘመን አቧራ አይሸፍነኝም ። የጻፍከኝ በወረቀት ላይ አይደለም ፣ የጻፍከኝ እንዳትረሳኝ በመዳፍህ ላይ ነው፤ ስለዚህ በረከቴ ፈጣን ነው ። የጻፍከኝ ልትደመስሰኝ አይደለም ፣ የጻፍከኝ ለዘላለም ነው ፤ ስለዚህ ነገ አያሰጋኝም ። የጻፍከኝ ለገበታ ላይ አይደለም ፣ የጻፍከኝ ለበጉ ሰርግ ነው ፤ ስለዚህ የማያልፍ ዓለም አለኝ ። የጻፍከኝ በሞት መዝገብ አይደለም ፣ የጻፍከኝ በሕይወት መጽሐፍ ነው ፤ ስለዚህ የሞት ግርማ አያስደነግጠኝም ። የጻፍከኝ በአሳሳቢ አይደለም ፣ የጻፍከኝ በፍቅርህ ነው ፤ ስለዚህ በሰዎች ሐሜት አትጠላኝም ። የጻፍከኝ ለኮንትራት አይደለም ፣ የጻፍከኝ በማይፈርስ ውል ነው ፤ ስለዚህ ታምነህ አትከዳኝም ። የጻፍከኝ ዕዳ አለበት ብለህ አይደለም ፣ የጻፍከኝ ዕዳው ተከፍሎለታል ብለህ ነው ፤ ስለዚህ ወደ ቤትህ ስመጣ አታሳቅቀኝም ። የጻፍከኝ ለውግዘት አይደለም ፣ የጻፍከኝ ይቅር ለማለት ነው ፤ ስለዚህ አክብረህ አታዋርደኝም ።
የጻፍከው የትላንት ታሪኬን የዛሬ ድካሜን አይደለም ፣ የጻፍከው የነገ ተስፋዬን ነው  ። የጻፍከኝ ከአገር እንዳይወጣ ብለህ አይደለም ፣ የጻፍከኝ መንግሥቴን ሰጥቼዋለሁ ብለህ ነው ። የጻፍከኝ ከውርስ ይነቀል ብለህ አይደለም ፣ የጻፍከኝ የእኔ ሁሉ የእርሱ ነው ብለህ ነው ። የጻፍከኝ ለሞት አይደለም ፣ የጻፍከኝ ለሕይወት ነው ። የጻፍከው የሕይወቴ መጽሐፍ መግቢያው ፍቅርህ ፣ ማጠቃለያው መንግሥትህ ነው ።
የጻፍክልኝን አታሎ ማንም አይወስደውም ። የጻፍከውን የከሳሽ ብዛት አይሰርዘውም ። የጻፍክልኝ ያለው በልብ ነውና ሌባ አይሰርቀውም ። ለእኔ ያልከው ለሌላ እንዳይሆን ለአንድ ሰው ብቻ የሠራኸው ነው ። የጻፍክልኝ የማይኮረጅ ጥበብ ያለበት ነው ።
እንደ ጻፍክልኝ ልኑር ። እንደ ጻፍክልኝ ልቅር ። በጻፍከው ላይ ደርቤ ልጻፍ ። የጻፍክልኝን እንዳልሰርዝ እርዳኝ ። እንደ ጻፍክልኝ ልገለጥ ። እንደ ጻፍክልኝ ልዋል ። እንደ ጻፍክልኝ ልጓደድ ። የተጻፈልኝን ትቼ የተጻፈላቸውን እንዳላይ ዓይኔን ከምቀኝነት ጠብቃት ። እግሬንም በጽሕፈቱ ፈለግ ምራት ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይሁን ። ከልባችን እስከ አርያም ፣ ከምታልቀዋ ከዛሬዋ ቀን እስከ ዘላለም ድረስ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 21
መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ