ቀኝህ በኃይሉ ከበረ ፣ ቀኝህ ያለ አጋዥ ገነነ ፣ ቀኝህ ጦም አዳሪውን አጠገበ ፣ ቀኝህ የተፍገመገሙትን ደገፈ ፣ ቀኝህ ጥቅመ ሰናዖርን አፈረሰ ፣ ቀኝህ የሰዶምን ምድር ደመሰሰ ፣ ቀኝህ ፈርዖንን አስጥሞ ምስኪኖችን አሻገረ ፣ ቀኝህ ናቡከደነፆርን ሣር አስግጦ ዳንኤልን አተረፈ ፣ ቀኝህ ሥጋ ማርያምን ለበሰ ፣ ቀኝህ በሥጋና ደም ተዛመደን ፣ ቀኝህ በመስቀል ላይ ዋለ ፣ ቀኝህ ሞትን ሰበረ ፣ ቀኝህ ሲኦልን በዘበዘ ፣ ቀኝህ ያመኑትን በእሳት በሰይፍ ውስጥ አሳለፈ ፣ ቀኝህ ይህችን ቀን ፈጠረ ። የእግዚአብሔር ቀኝ ቡሩክ ነህ ። የእግዚአብሔር ክንድ ልዩ ነህ ። ደዌን ነቃዩ ፣ ሞትን አርካሹ የእግዚአብሔር ቀኝ ወዴት ነህ ?
ቂም ሳይለቀኝ ጸሎት ፣ በቀል ይዤ አገልግሎት ፣ እልህ አንቆኝ ስብከት ፣ እየተናደድሁ ምጽዋት ፣ እየገደልሁ መሥዋዕት ፣ እያስለቀስኩ ስብሐት እስከ መቼ ነው ? የእግዚአብሔር ቀኝ ሆይ አስጥለኝ ። ከራሴ ጋር ክርክር እስከ መቼ ነው ? ጽድቅን እያየ ኃጢአትን የረገጠውን ይህን ሥጋዬን ምን ላድርገው ? የምወደውን ትቼ የማልወደውን የማደርግ ጎስቋላ ሰው ነኝ ። ክብሬ ጌታዬ ሆይ ራሴን ከራስህ አስታርቅልኝ ። የጽድቅ መሻቴን መታዘዝ ፣ ስለ ድካሜ ማልቀሴን ሰማዕትነት አድርግልኝ ። ከሰዎች ጋር ክርክር እስከ መቼ ? ፊታቸው ሲጠቁር ሰማይ የጠቆረ ፣ ሰላምታቸው ሲቀዘቅዝ በመንበርህ የሌለህ ይመስለኛል ። ማመኔ በሰው እንጂ ባንተ አይደለምና የእግዚአብሔር ቀኝ ሆይ ከፍ አድርገኝ ። ከጭቃ ኑሮዬ አውጥተህ በዓለቱ ላይ አቁመኝ ። ሰውን እያየሁ እንዳልኖር እርዳኝ ። የኖርኩላቸው ቀርቶ ያልኖርኩልህ አንተ ግን አዳንከኝ ። ሕሊናዬን ክሰህ በፊትህ አቆምከኝ ። ከሰይጣን ጋር ክርክር እስከ መቼ ? ተከሳሹን ከሳሽ ፣ ተኰናኙን ኰናኝ መፍራቴ ለምንድነው ? እላለሁ ። አንተን ብቻ በማየት ልክበር ።
በሽታን እንጂ ኃጢአትን አልፈራም ። እንደ ባለጌ ልጅ እየተቀጣሁ እሳደባለሁ ። እኔው በድዬ ይቅርታ መጠየቅ እሻለሁ ። የሥጋን ሞት እንጂ የነፍስን ሞት አልፈራም ። የሥጋ ሞት የግድ ፣ የነፍስ ሞት ግን የፈቃድ ነው ። በደሉና ተቀጡ እላለሁ ። የዳር እሳት መሐል እንደሚደርስ ዘንግቻለሁ ። የእግዚአብሔር ቀኝ ሆይ ከከበረ አስተሳሰብ ላይ አውለኝ ።
ቃልህን ከመስማት ጋር መታዘዝን ፣ ድሀን ከመርዳት ጋር መጸለይን ፣ ከፍቅር ጋር ምጽዋትን ፣ ከአገልግሎት ጋር አሥራትን ፣ ከኑሮ ጋር ስብከትን ፣ ከጽድቅ ጋር ክህነትን ፣ ከበረከት ጋር ኑሮን ፣ ካንተ ጋር ሕይወትን ስጠኝ ። ብዙ መናገር ጆሮዬን ደፈነው ፤ ብዙ ማየት ልቤን አደነደነው ። ከውጭ መዓት ይልቅ የልቤ ጥንካሬ ያስፈራኛል ። አንተ ለቅጣት ስታመቻች ልብ እንደ ፈርዖን ይደነድናል ። ጌታዬ ሆይ ሰው ክቡር መሆኑ ጠፍቶኝ ስንት ሞተ እላለሁ ። ሰውን ቍጥር አድርጌ ዜና እናፍቃለሁ ። አንድ ሰው ብዙ መሆኑን ዘንግቼ ማዘን ትቻለሁ ። የዓመት አሳቤን ትቼ የዕለት ነዋሪ ሆኛለሁ ። ዓለምን በአንድ ዓይነት ቋንቋ ስለምታስተምርበት ጥበብህ ምስጋና አቀርባለሁ ። ምኞቴ ከርከም ብሎ እስቲ ልዋል ብያለሁ ። የዘመን ጌልጌላ የምኞት ሸለፈቴን እስከ ወዲያኛው ገርዞ ይጣለው ። የዓለምን ከንቱነት እንዲህ በመስክ ላይ ስላስተማርከን ተመስገን ። የክፍሉ ትምህርት አልገባ ብሎን ይኸው ቤተ ክርስቲያንም ተዘጋ ። ተምረን በጽድቅ ይከፈትልን ። አሜን ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይሁን ። ከልባችን እስከ አርያም ። ከዛሬ እስከ ዘላለም ድረስ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 20
መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም.