የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ሰማይ ልውጣ

 የማያምን ሰው ጠፈረ ሰማይን ያያል ፣ የሚያምን ግን ከሰማዩ በላይ ያለውን ዙፋንህን ያያል ። አንተም የተሰወርህ ስትሆን ለምትወደው ግን ራስህን ትገልጣለህ ። ለሚሻህ የጌትነትህን ምሥጢር ታብራራለህ ። የኪሩቤል ሠረገላ አንተን አይችልህም ። በሰማይ ትኖራለህ ብንልም ስለ ልዕልናህ ለመናገር እንጂ ሰማይ ወስኖህ አይደለም ። የኃጢአተኛው ኃጢአት አያረክስህም ። በሽተኞችን አትሸሽም ። የደካማው ድካም አይገርምህም ። የድሀው ልመና አያሰለችህም ። በርህን የሚያንኳኳ አይረብሽህም ። ተራዬ መቼ ነው ? የሚሉህ አያበሳጩህም ። ከገናኖች በላይ ገናና ነህ ። ከልዑላንም በላይ ልዑል ነህ ። ያልተቀበልህ ባለጠጋ አንተ ነህ ። ያልተቸርክም ቸር አንተ ብቻ ነህ ። በሰማይ ሠራዊት ፣ በምድር አማንያን ፣ በሞቱትና በሕይወት ባሉት አንደበት ትመሰገናለህ ። አዳራሽህ እልፍኝ ነው ፤ እልፍኝህም አዳራሽ ነው ።ለሚያምኑህ እልፍኝህ አዳራሽ ነው ፤ የተገለጠ እንጂ የተሰወረ ነገር የለህም ። ለማያምኑህ ግን አዳራሽህ እልፍኝ ነው ። የተገለጠው ቃልህ እንኳ ስውር ይሆንባቸዋል ።
እመጣለሁ ትላለህ መቼ እንደምትመጣ የሚያውቅ ማንም የለም ። ስለ ዘመኑ እንጂ ስለ ቀኑ ከቅዱሳንህም ሰውረሃል ። በመሰወርም ትባርካለህ ። ቀኑን ብናውቀው ከቀኑ በፊት እንሞት ነበረ ። በአቅማችን ልክ ያስተማርከን አንተ ነህ ። ክብርህን የዘመረ ፣ ምስጋናህን አሟልቶ ያቀረበ ማንም የለም ። ትጉሃን ከትጋታቸው በላይ ትሆንባቸዋለህ ። ምስጋናህን ባይፈጽሙትም መርካትን ግን አትከለክላቸውም ። አንተ በመታወቅም ታስደንቃለህ ፣ ባለ መታወቅም ታስደንቃለህ ። ውለታህ እንቅልፍ የለሽ ያደረጋቸው ብዙ ቅዱሳን አሉህ ። እኔ ግን ጭቃ እያላቆጥሁ ፣ መሬት ለመሬት እሳባለሁ ። የደመናውን መጋረጃ ፣ የሰማዩን መንጦላዕት ገልጬ ፣ የማይጠቀለለውን ሥላሴነትህን ፣ የማይከፈለውን መለኮትህን ላመሰግን ገና ነኝ ። እባክህን ከምስጋናሀ በዓል ላይ አድርሰኝ ። በዓል ሁኖ ለዘላለም ይኑር ። ከሙሽርነት በኋላ ወደ ትግል አልግባ ። ባንተ ደስ እንዳለኝ ልቅር ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና/12
መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ