የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የፈጠርከውን አክብረው

 ከተጻፈው በላይ የሆንህ ፣ ከተዘመረልህም ይልቅ ድንቅነትህ የሚያበራ ፣ ከተሰበከው ጠልቀህ የምትኖር ፣ ከተቀደሰው ቅዳሴ በላይ መዓዛህ ልዩ የሆነ እግዚአብሔር አንተ ነህ ። የአቅማችንን ያህል እናመስግንህ እንጂ ይህ ልክህ ይህ መጠንህ አይደለም ። ምስጋናን የከንፈር ፍሬ ፣ መላ ሕይወታችንን የሚቃጠል መሥዋዕት ፣ በመጠን መኖራችንን የእህል ቊርባን ፣ ፍቅራችንን የኅብረት መሥዋዕት ፣ ንስሐችንን የኃጢአት መሥዋዕት ፣ ዓለም በቃኝ ማለታችንን የበደል መሥዋዕት አድርገን እናቀርብልህ ዘንድ እንወዳለን ። መሻት እንጂ አቅም የለንምና ካለ መቻል ታድነናለህ ። በፊትህ ሁሉም ነገር የተገለጠ ፣ የተራቆተና ባዶ የሆነ የካህናት አለቃ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የአሳባችንን ብክለት በመንፈስህ አየር አንተ ለውጠው ። በፊትህ እኛን ሁነን ስንመጣ ያንተ አድርገህ መልሰን ። ስንጀምር አንተ ፈጽምልን ፣ ስንፈጽምም ጅማሬአችንን እይልን ። የእኛ ጅምር ማለቅ ፣ የእኛ ፍጻሜ ደስታ የለውምና አንተ አግዘን ። የሚበጀንን ባለ ማወቅ በሞት ሰፈር የምንኖር ፣ እውቀት ተስኖን የእሳትን ውበት እንጂ ማቃጠል የማንለይ ልጆችህ ነንና አድገን እናሳርፍህ ዘንድ ሠርተህ ፈጽመን ። የምስጋናን ዘውድ ጭነህ ፣ በግርማ ተከበህ ፣ በራስህ ክብር ደምቀህ ትኖራለህ ።
የሰጠኸው እንጂ የሰጠህ ፣ የሾምኸው እንጂ የሾመህ ማንም የለም ። እንደማትችል ዝምታህ ፣ እንደማይሰጥ መዘግየትህ ይደንቃል ። ልቤ እንደ መሰንቆ ሁኖ አንተን ቢያከብርህ ፣ ዓይኔ እንደ ዋሽንት ሁኖ አንተን ቢያስስህ ፣ እጄ እንደ በገና ሁኖ ንጉሥነትህን ቢተርክ እመኛለሁ ። ዝንጉዎችን በማስታወስ ፣ አላዋቂዎችን በአእምሮ የምትባርክ እኔ መሪያቸው ነኝና እባክህ አበርታኝ ። የሰጠኸኝን ሳላየው ሌላ ያምረኛል ፣ በምንጩ አጠገብ ቆሜ የጥማት ሲቃ ይተናነቀኛል ። የሌለኝን ከመስጠትህ በፊት ያለኝን አሳውቀኝ ። መቶ የበሽታ ዝርዝር ቢመጣ ዘጠና አምስቱ የለብኝም ። ጌታ ሆይ ስለበዛው ጤና የማመሰግንህ ከቶ መቼ ነው ። ፀሐይ ባሪያህ ሁና ሳይደክማት ታበራለች ፣ አንተ ግን የዓለም ብርሃን ባልካቸው ልጆችህ መብራትነት ትደሰታለህ ። ባንተ ዘንድ የተወደደ መሥዋዕት አቀርብልህ ዘንድ እጄን በአምኃ ፣ አፌን በምስጋና ፣ ልቤን በመወሰን ባርክ ። ሕዝቡ ያንተ ነውና እንደ ጎርፍ ወደ ጥፋት ሲሄድ መልሰው ። የምድር መሪዎች የሚመሩትን ንቀው የሚናገሩት ሁሉ ቀላል ንግግር ነው ። የፈጠርከውን ወገን አንተ አክብረው ።
ተራራው ላይ ስወጣ ሁሉ ይታየኛል ። ወደ ተራራ ለመውጣት ግን ድካሜ ያሳስበኛል ። ያደከመኝ ተራራ ከፍታ እንደሚሆነኝ እባክህ አስረዳኝ ። ያልተገፋ ራስ ላይ አይወጣም ። የጎን ጦር የሌለበትም ስለ ዕድገት አያስብም ። ዛሬ የደረስኩበት ነገር ሁሉ ጠላቶቼ ላጥፋህ ሲሉ ያበሩኝ ነውና ጠላቶቼን ባርክልኝ ። ፈርዖንን አስነሥተህ እስራኤልን ለንስሐ የጋበዝህ ፣ የተመቻቸው ባሪያ ከመሆን ነጻነት ያላቸው ድሆች እንዲሆኑ ያነቃቃህ ፣ በክፉዎችም እየሠራህ ልጆችህን የምታበረታ አንተ ነህ ።
የምስጋናህ ጤዛ ነፍሴን ያርሳት ፣ የክብርህ ጠል ይረፍብኝ ። ያነሰ ኑሮ ከመኖር ፣ ዝቅ ባለ አስተሳሰብ ዝቅ ከማለት ጠብቀኝ ። ዘመንን የማይብህ ዓይኔ ነህ ተመስገን ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና /8
የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ