የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይሰክር

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ፤ የማይሰክር” 1ጢሞ. 3፡3
የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
www.ashenafimekonen.blogspot.com
ብዙ ሕይወት ፣ ብዙ ትዳር ፣ ብዙ ቤተሰብ ፣ ብዙ ፍቅር ፈርሷል ። የፈረሰውም በመጠጥ ነው ። በኖኅ ዘመን መላው ዓለም በውኃ እንደ ጠፋ ዛሬም መላው ዓለም በመጠጥ እየጠፋ ነው ። የሰው ልጆች ዕለቱን የሚውሉት በትክክል በማሰብ ሳይሆን በመደንዘዝ ነው ። ጤነኛ ሁኖ ወደ መጠጥ ቤት የገባው ሰው ሲወጣ እያበደ ነው ። በሰላምታ ገብቶ እየተሳደበ ይወጣል ። መጠጥ ቤት ገብቶ ራሴን እገዛለሁ ማለት ዘበት ነው ። ነገሮችን መጋፈጥ የማይፈልጉ ፣ አቋራጭ ደስታ የሚሹ እነርሱ በመጠጥ ይደነዝዛሉ ። በተለያዩ ቢሮዎች ጉዳይ ያላቸው እንዲያደፋፍራቸው ብለው ይጠጣሉ ። ሰዎች ወደ መጠጥ እንጂ ወደ ስካር በራሳቸው አይገቡም ። ወደ ስካር የሚወስዳቸው መጠጡ ነው ። ብርጭቆ መጀመሪያ እንጨብጠዋለን ፤ ቀጥሎ ይጨብጠናል ።
ሰዎች ወደ መጠጥ የሚገቡት በተለያየ ምክንያት ነው ። ስካር አላማጅ አለው ። አልጠጣም የሚለውን ሰው መጠጥ ለማስጀመር ብዙ በጀት የሚበጅቱ ሰዎች አሉ ። አብላኝ የሚላቸውን ያልፋሉ ፣ አጠጣኝ ለሚላቸው ግን ቸር ይሆናሉ ። ለጽድቅ የታሰረ እጅ ሰውን ለማስከር ግን ይፈታል ። ጠጪዎች ሌላውን ለማስጀመር የሚፈልጉት አንደኛ አጃቢ ፍለጋ ነው ። ሁለተኛ እነርሱ የቸገራቸው ቀን ያ ተማሪያቸው ከየትም ፈልጎ እንዲያጠጣቸው ነው ። ሦስተኛ ያንን ሰው እንደ ፈለጋቸው ለማዘዝ ነው ። ሱስ ረጅም ገመድ ነው ። እየሰደቡት እንኳ ሱሰኛ ከአስተማሪዎቹ ቤት አይርቅም ። ሱስ ሐሰተኛ ደግነት ያለው ሲሆን የገዛ ልጆቹንና ሚስቱን እያስራበ ሌሎችን ይጋብዛል ። በደጅ ጥሩ ሰው ፣ ተጫዋች ያደርገውና ወደ ቤቱ ሲገባ በጥባጭና ግልፍተኛ ያደርገዋል ።

መጠጥ እብደት ነው ። እብደትነቱ ልዩ የሆነው አንዱን ቀን ሁለት በማድረግ ጠዋት ጨዋ የነበረውን ሰው ከሰዓት እብድ ያደርገዋል ። አሁንም እብደትነቱን ልዩ የሚያደርገው በገንዘብ የሚገዛ መሆኑ ነው ። የመጠጥ መግቢያውና ማጠቃለያው ምንድነው ካልን መግቢያ ዘፈን ሲሆን ማጠቃለያው ዝሙት ነው ። ውጤቱ ጸጸትና በሽታ ነው ። ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው ይባላል ። ውኃ የሚወስደው ሰው ሳቅ ያፍነዋል ። ሳቁም አቅም እያሳጣው ወደ ሞት ወደ መስጠም ይሄዳል ። መጠጥም ጨዋታ ፣ ደስታ ፣ ነጻነት ያለበት ይመስላል ። ሰዎች እየሳቁ የሚሞቱበት ስፍራ ቢኖር መጠጥ ቤት ነው ። የሚደንቀው መንግሥት በምሁርነትና በተቆርቋሪነት የሚገሥጸውን እስር ቤት ይከታል ። ሰካራም ሲሳደብ ግን ጥበቃ ይደረግለታል ። በአገራችን እውነት ለመናገር እብድ ፣ ዘመናይና ሰካራም መሆን ያስፈልጋል ። የስካር ዓለም ጨካኝ ነገሥታት እንኳ የናቁት በመሆኑ ሰዎች እየጠጡ ብሶታቸውን ይናገሩበታል ። መጠጥ አዋራጅ ነገር ነው ። በመጠጥ ስፍራ የተገኙ ባለጠጎች ፣ ባለሥልጣናትና ሽማግሌዎች እንደ ሕፃን ሊታዩ ፣ ሊናቁና ሊሰደቡ ይችላሉ ። ሰው ራሱን ጨፍልቆ መለኪያ ውስጥ ሲከትት መጠኑ አንድ ብርጭቆ ያህል ይሆናል ። ብዙ ተንኮለኛና ጠላት ያለባቸው ሰዎች በፍጹም መጠጥ  አይቀምሱም ። ሰው ተመርዞ የሚገደለው ብዙ ጊዜ በመጠጥ ነው ። ክፉዎች እንኳ መጠጥ የሚያራቁት እንደሆነ አውቀው ይጠነቀቃሉ ። በየአገራቱ ያሉ ዲፕሎማቶች የዚያን አገር ምሥጢር የሚያገኙት የዚያን አገር ባለሥልጣናት በማጠጣትና አብሮ በማምሸት ነው ። በመጠጥ ውስጥ ያሉ የደኅንነት ሠራተኞች የአገራቸውን ምሥጢር አሳልፈው ይሰጣሉ ። መጠጥ አገርን ጭምር ለጉዳት ይሰጣል ።
ሄሮድስ በዘፈን ተማረከ ፣ በመጠጥ ልብ ሁኖ መጥምቁ ዮሐንስ አንገቱ እንዲቆረጥ አዘዘ ። መጠጥ የቅዱሳንን አንገት የሚያስቆርጥ ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ ጨርሶ አትጠጡ አይልም ፤ ጠጡም አይልም ። በሰው ልጆች ታሪክ ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞ እንደ ታየው ግን አለመጠጣት ክብር አለው ። ባለመጠጣት የምናጣው ነገር የለም ፤ በመጠጣት ግን ብዙ ነገሮችን እናጣለን ። መጠጥ ሰው ከቤቱ ውጭ እንዲያመሽና እንዲያድር ያደርገዋል ። ብዙ ሚስቶች ቤት ጠባቂ ዘበኛ ሁነው የቀሩት በመጠጥ ምክንያት ነው ። መጠጥ ለልጆች ክፉ አርአያ ነው ። መጠጥ ኢኮኖሚን የሚያናጋ ነው ። መጠጥ የሐሰተኛ ደስታ መገኛ ነው ። መጠጥ ማታ ንጉሥ የሚያደርግ ጠዋት የሚያኮስስ ነው  ። መጠጥ ጤናን የሚጎዳ ፣ ያለ ጊዜው የሚገድል ነው ። መጠጥ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ፣ ከምግባረ ብልሹዎች ጋር የሚያውል ነው ። መጠጥ ንቀትና አደራ በላነትን የሚያመጣ ነው ። ሰካራም ጋ የሚቀመጥ የዕድር ገንዘብ የለም ። ሰካራም ከትዳሩም ፣ በማኅበራዊ ሕይወቱም በላይ ስካሩ ይበልጥበታል ። ሰካራም ተንቀሳቃሽ ሬሳ ነው ። ከቆሙት በታች ፣ ከሞቱት በላይ ነው ። እብድ ቢጨምት እስከ እኩለ ቀን ነው ይባላል ። ሰካራም ጨዋ የሚሆነው እስከ እኩለ ቀን ነው ። እርሱም በማታ ድካሙ ስለሚተኛ ነው ። ሲነሣ መነጫነጭና መሳደብ ይጀምራል ። እብድና ብርድ በግድ ያስቃል ይባላል ። ሰካራምም በግድ የሚያስቅ ነው ። አሁን ዘፍኖ አሁን ያለቅሳል ።
ሰዎች ወደ መጠጥ የሚገቡት ጓደኛ ፍለጋም ነው ። በመጠጥ ቤት ሐሰተኛ ኅብረት አለ ። ዛሬ አንዱ ከከፈለ ነገ ደግሞ ሌላኛው ይከፍላል ። ሰካራም  ቤት አይሠራም ፣ ከሠራም ቶሎ አይገባም ፣ ከገባም ቶሎ አይተኛም ይባላል ። መጠጥ ከገዛ ቤት ስደተኛ ያደርጋል ። ጠጪ ማለዳው የተበላሸበት ነው ።ማቀዝቀዣ ሚሪንዳ ፣ ሽሮ ፍትፍት ፈላጊ ነው ። ጠጪ በገዛ ሚስቱ የተናቀ ነው ። ያለ ፍላጎቷ እርሱ በፈሳሽ የወሰደውን መጠጥ እርስዋ ደግሞ በትንፋሽ ትወስዳለች ። ብዙ ጠጪዎችና ሱሰኞች ሁለት ትዳር መሥርተው የሚኖሩ ናቸው ። የመጀመሪያው ቤታቸው ለክብራቸውና ለልጆች ማሳደጊያ ሲጠቀሙበት ሁለተኛውን ደግሞ ለዘላንነት ይጠቀሙበታል ። መጠጥና ሱስ የስንፍና መገኛ ነው ። መጠጥ የማሰብን ኃይል እየቀነሰ ይመጣል ። ጠጪዎች ትዕግሥት ስለሚያጥራቸው በሽሽት የሚኖሩ ናቸው ፤ ከጤነኛ ሰው ጋር ለመገናኘትም ነጻነት አይሰማቸውም ። በጸጸት ስለሚሰቃዩም ጠዋት አዝነው ማታ ይመለሳሉ ። ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል የሚባለውም ይፈጸምባቸዋል ። ሰዎች በብርቱ ኀዘን ምክንያትም ወደ መጠጥ ይገባሉ ። ሌሎችም በየመጠጥ ቤቱ ያለው ጭፈራ ደስታ እየመሰላቸው ይገባሉ ። ገንዘብ ለማግኘት የሚሹም ባለሥልጣኖቹ ያሉት መጠጥ ቤት ነውና የጨለማ ቢሮዎችን ሲያስሱ ያድራሉ ። ጨረታው ፣ ጉዳዩ ፣ ፍርዱ የሚያልቀው መጠጥ ቤት ነው ። አገር ጣር የያዛት በመጠጥ ነው ።
በመጠጥ መንፈስ ሁነው አንገት የቀሉ ፣ አሮጊት የደፈሩ ብዙዎች ናቸው ። መጠጥ ሰውን ከእንስሳ ያነሰ ያደርገዋል ። ስንቱን እናወራለን ። የስካር መዘዙ ብዙ ነው ። በጸጸት የሚሰቃዩ ሰዎችም ስካርን መደበቂያ ያደርጉታል ። ነገር ግን ጨለማ በጨለማ አይሸነፍም ፤ ጨለማ በትንሽ ብርሃን ግን ይሸነፋል ። ለጸጸት መድኃኒቱ ንስሐ መግባትና በክርስቶስ ደም መታጠብ ነው።
ኤጲስ ቆጶስ የማይሰክር ሊሆን ይገባዋል ። ሾፌር መጠጣት የለበትም ። የሕይወት ኃላፊነት በእጁ ነውና ። የነፍስ አደራ ያለበት ኤጲስ ቆጶስም ሊሰክር አይገባውም ። ይልቁንም በምንኩስና ያሉ አባቶች ፈጽመው ሊጠጡ አይገባቸውም ። መነኩሴ ምናኔው ከመጠጥ ጭምር ነው ። ብዙ ዘመን በመጠጥ ምክንያት ስንሰደብ ኑረናል ። ካህናት በመጠጥ ምክንያት የክህነትን ክብር አዋርደዋል ። ስካርም የኦርቶዶክሳዊነት መለያ እስኪመስለንም መጠጥ ያልጠጣ ሌላ ነው ብለናል ። ይህ አለማወቅ ነው ፤ በእውቀት እንጂ በመጠጥ መወዳደር ክብር አይደለም ፤ የትም አያደርስም ።
ኤጲስ ቆጶስ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተመረጠ ነውና ሊሰክር ቀርቶ ሊጠጣ አይገባውም ። ቃሉ፡- መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” ይላል ። ኤፌ. 4፡18 ። መንፈሰ እግዚአብሔር ያደረበት ሰው በመጠጥ ሊነዳ አይገባውም ። በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ያለም በመጠጥ ቁጥጥር ሥር መሆን አይገባውም ። ይህ ማባከን ነውና ። ስካር ኅሊናን ፣ እውቀትን ፣ ምሥጢርን ፣ ጤናን ፣ ገንዘብን ፣ ወዳጅነትን ፣ ትዕግሥትን … ማባከኛ ነው ። ብዙ ኃላፊነት ያለባቸው በትንሽ መጠጥ አቅላቸውን ይስታሉና መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል ።
የእስራኤል አምላክ ሆይ እርዳን ።
1ጢሞቴዎስ 40
ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ