“እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም ።” 1ጢሞ. 1፡4 ።
በዚያ ዘመን ባለ ሀብቶች እርሻቸውና መኖሪያቸው የተለያየ ነበር ። በእርሻው ላይ ገበሬዎችና ልጆቻቸው ፣ ንብረትና ንግዶች አሉ ። ይህን ትልቅ ተቋም የሚያስተዳድር መጋቢ ሾመው ይሄዳሉ ። በዓመቱ ሲመጡ የገባውንና የወጣውን ሂሳብ ይተሳሰባሉ ። መጋቢውም እርሻንና ተክሉን መቆጣጠር ፣ ለገበሬዎቹ በጊዜ ደመወዝ መክፈል ፣ ቤተሰቡን መመገብ ፣ በሠራተኞች መካከል ጠብ እንዳይነሣ መንገዶች መዝጋትና ከተነሣም የማስታረቅ ኃላፊነት ነበረበት ። መጋቢውም በዓመቱ ጌታው ይቆጣጠረዋልና ገቢውንና ወጪውን በመዝገብ ተቆጣጥሮ ማስቀመጥ ነበረበት ። ጌታውም በመጣ ጊዜ ደስ ከተሰኘበት ሽልማት ይጠብቀዋል ። ባሮቹ ቀርበው ደብድቦናል ካሉ ፣ ቤተሰቡ ቀርቦ አስርቦናል ብለው አቤቱታ ካቀረቡ ከቦታው ይነሣ ነበር ። በደህና ለማስተዳደሩ ምስክርነት ካገኘ ፣ ሥራው ተመዝኖ ካለፈ የበለጠ ኃላፊነት ይሰጠዋል ። በጥቂቱ ታምኗልና በብዙ ይሾማል ።
መጋቢነት የእግዚአብሔር ሥራም ነው ። ሌሊትና ቀኑን ክረምትና በጋውን ማፈራረቁ ፣ ሁሉን ሳይሰለች እንደ ፍላጎቱ መሸከሙ ፣ በስህተቱ ይቅር ማለቱ መጋቢነቱ ነው ። መጋቢው እግዚአብሔር መጋቢዎችን ይሾማል ። እነዚህ አገልጋዮች ፣ የቃሉ ሠራተኞች እንደ እነርሱ ያሉትን አገልጋዮች መንከባከብ አለባቸው ። አገልጋይ በአገልጋይ መጨከን የለበትም ። “የእናቲቱ ደኅንነት የፅንሱ ደኅንነት ነው” ይባላል ። የአገልጋዮች ደኅንነት የምእመናን ደኅንነት ነውና መጋቢው ለአገልጋዮች ቅድሚያ መስጠት ይገባዋል ። እየራበው ከመጣ የሚያገለግለውን ሕዝብ ሊበላ ይችላል ፤ ሐሰትን ሊያስተምርና ውሸታም ነቢይ ሊሆን ይችላል ። የሚያጠፋው እንደ አቅሙ ነውና ቸል ሊባል አይገባውም ። ባሮቹን የሚደበድብ መጋቢ ይጠየቃል ። አገልጋይ ሁኖ አገልጋይን የሚጎዳም ይጠየቃል ። መጋቢው ቤተሰቡን መመገብ ወይም ምእመናንን በእግዚአብሔር ቃል ማጽናናት ይገባዋል ። የጣፈጠ ምግብ ለማቅረብም መዘጋጀት ያስፈልገዋል ። ስብከት መልእክት እንጂ ጩኸት አይደለም ። ስብከት የክርስቶስ ድምፅ እንጂ የንግግር ችሎታ አይደለም ። ስብከት የአእምሮ ጭማቂ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ነውና ተግቶ ማዘጋጀት ይገባዋል ። መጋቢው እርሻውን መቆጣጠር አለበት ። ያልታረመ ፣ ውኃ የበዛበትን መለየት አለበት ። ቸል የተባሉ ስህተቶችን በቶሎ ማስወገድ አለበት ። ቸልታ ዘርን ሲያመክን ፣ አረምን ግን የበለጠ ያሳድገዋል ። እንክበካቤ የበዛባቸውም ደካማ ሊሆኑ ይችላሉና ሁሉን በእኩል ማስተናገድ ይገባዋል ። በፊት ለፊት በር እያስገባ በኋላ በር እንዳያስወጣ መጠንቀቅ አለበት ። ትዕግሥቱ ስንፍና ፣ ትጋቱ መክነፍ እንዳይመስል መመርመር አለበት ። አንድ ቀን የሾመው ጌታ ሥራውን ይመዝናልና ያንን ቀን እያሰበ መትጋት ይገባዋል ። የባሮቹ ጠባይ ፣ የቤተሰቡ ሞራል ሳይሆን የእርሱ በደንብ ማገልገል ይታያልና ለራሱና ለአገልግሎቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገዋል ። መጋቢ የቀን ሠራተኛ ሳይሆን የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ ነውና ቀንና ሌሊት በሥራው ላይ መሆን ይገባዋል ።
“እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም ።” 1ጢሞ. 1፡4 ።
እንደዚህ ያሉ ነገሮች የተባሉት ልዩ ትምህርት ፣ ከቃሉ በላይ የሚከበር ተረትና የትውልዶች ታሪክ ናቸው ። እነዚህ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉ ። ክርክር የሥጋ ሥራ ነው ፣ ዓላማው ማሳወቅ ሳይሆን የበላይ መሆን ነው ። የበላይ በመሆን ውስጥ ደግሞ ፍቅርና ትሕትና ይጠፋሉ ። መጋቢዎች በተለያየ ሁኔታ ይሆናሉ ። በእምነት ላለ መጋቢ ግን የማይጠቅሙ ነገሮች ክርክር የሚያመጡ ነገሮች ናቸው ። መጋቢዎች፡-
በሥጋ ይሆናሉ፡- ቦክሰኛ ፣ ካራቲስት ፣ ባለ ጥቁር ቀበቶ ተራጋጮች ፣ ባለ ሽጉጥ አገልጋዮች በልዩ ትምህርትና ተረቶች ተጠቃሚ ናቸው ። ወይም የሚጠቀሙ ይመስላቸዋል ።
በስሜት ይሆናሉ፡- ወቅታዊ ርእስን እንደ ሰበር ዜና የሚያስተጋቡ ፣ ለአሙቁልኝ የሚፈለጉ ፣ በእሳት ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ ፣ እግዚአብሔርን በስድብ አስከብራለሁ የሚሉ በስሜት ያሉ አገልጋዮች በዚህ ነገር ይጠቀማሉ ። ክርክር ሲበዛ ገላጋይ ይሆናሉ ። ተረት ሲበዛ የተረት አባት ይሆናሉ ። የትውልዶች ታሪክ ሲነሣ ጎሣዬ ይህ ነው ይላሉ ። በዚህ ለመጠቀም ይሞክራሉ ።
በእውቀት ይሆናሉ፡- ይህ ቃል በዕብራይስጡ የለም ፣ በግሪኩ እንዲህ ይላል ፣ የላቲኑ ትርጉም አያነሣውም ፣ የሰባ ሊቃናት ትርጉም እንዲህ ይለዋል የሚሉ ሰዎች ክርክር ሲነሣ አለን ብለው ይገባሉ ። በዚህም አዋቂ ለመባል ይጥራሉ ። ክርክር ግን በእምነት ላለ መጋቢ አይጠቅምም ። ክርክር የበላይነትን ማስመስከር ነው ። እምነት ደግሞ የበታች ነኝ ማለት ነው ።
በእምነት ይሆናሉ፡- አገልጋዮች የሚጠቀሙትም ሆነ የሚጠቅሙት በእምነት ሲሆኑ ነው ። በእምነት ያለ አገልጋይ የማይታየውን እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ያያል ። በሰው ዘንድ አንቱ ለመባልና ትልቅ ተብሎ ለመወደስ ጊዜ የለውም ። ክርክሮች እንዳይነሡ ይጥራል ። ሰዎች የእግዚአብሔርን ማንነት ተረድተው ለክብሩ በሚመጥን ኑሮ እንዲገለጡ ይመክራል ። ሰማይን በማየት የምድሩን እንዲንቁ ያስተምራል ።
የሚጠቅመውን እንድንይዝ እግዚአብሔር ይርዳን !
1ጢሞቴዎስ /9/
ኅዳር 14 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ