የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተዘረጋው ጥላ

“ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን 1ጢሞ 1፡2
በዚህ ዘመን ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ ካልን ጸጋ ፣ ምሕረትና ሰላም ናቸው ። የሰው ልጆች ኑሮ የመጠባበቅ ፣ ምን እሰጣለሁ ? ሳይሆን ምን እቀበላለሁ ? የሚል ስሌት ውስጥ ከገባ ዓመታት ተቆጥረዋል ። ጸጋ ማለት የማይገባ ደግነት ነው ። ለማይገባቸው ሰዎች የማይገባቸውን ነገር ካላደረግን ይህን ዘመን መሻገር ይከብዳል ። ሰዎች እኔ ተጎዳሁ እንጂ ሌላውን ጎድቻለሁ ለማለት የሞራል ከፍታን ማግኘት አልቻሉም ። በሕይወት ውስጥ ትልቁ የሞራል ከፍታ አልቻልኩም ብሎ አቅምን ማወቅና አጥፍቻለሁ ብሎ በደልን ማመን ነው ። ሁሉን ነገር ለእኔ ብቻ ማለት ፣ እንደሚበሉት ሳያረጋግጡ መሰብሰብ ፣ የራስን ስሜት እንጂ የጎረቤትን አለማዳመጥ ዕለት ዕለት እየበዛ ነው ። በነጻ ማፍቀር አይቻልም ፣ ለማያውቁትና ምንም ላላደረገ ሰው ውለታ መዋል እብደት ነው የሚል አስተሳሰብ እየፈላ ነው ። ሰዎች ራሳቸው ማድረግ ያቃታቸውን ደግነት ሌሎች ሲያደርጉት እውነት ነው ብለው ከመቀበል ውሸት ነው እያሉ ማጣጣል አብዝተዋል ። ጸጋ ማለት ቀድሞ ማፍቀር ፣ ቀድሞ መልካም ማድረግ ፣ በራስ ፍቅር ላይ ተመሥርቶ ያንን ወገን መውደድ ፣ ብድር መላሽነቱን ሳያገናዝቡ ስጦታን መስጠት ነው ። አመሰግናለሁ ሲባሉ የሚሰጡ ሰዎች ምላሽ ሲያጡ ያቆማሉ ። ዘመኑ ሰዎች ሲደረግላቸው ይገባኛል ብለው የሚያስቡበት ፣ መንፈሳዊነት ሳይሆን ሰብአዊነት እየጠፋ ያለበት ነው ። ይህን ዘመን የጸጋ መንገድ ካልሆነ ምንም ሊታደገው አይችልም ።

ሁለት ነገሮች እየደበዘዙ እንዳይመጡ ያሰጋል ። ለተቸገሩት እንጀራ ፣ ለበደሉን ይቅርታ መስጠት እንዳይከዳን ያስፈራል ። ችግረኛውን ስናይ ውስጣችን የቀን ገቢያቸው ይህን ያህል ደርሷል ፣ ሠርተው አይበሉም ወይ ? ይላል ። ብንሰጥም በፍጹም ለጋስነት ሳይሆን በመጠራጠር ነው ። ነፍሳቸው ታስራ ይቅርታ የሚለምኑን ሰዎችን ይቅርታ መስጠት አለብን ። ታስረዋልና ምንም መንቀሳቀስ አይችሉም ። ትልቁ ችግራቸው የጸሎት መንገዳቸው ዝግ መሆኑ ነው ። ሌላውን አሳዝኖ መጸለይ በእግዚአብሔር መቀለድ ነው ። አንድ አባትን ልጁን ገድለህበት ጮማ ብትቆርጥለት ደስ ይለዋልን ? የሰዎችን ልብ ሰብሮ መጸለይም ወደ ተዘጋ ሰማይ መገስገስ ነው ። ዛሬ ጸሎት አላነሰም ፤ ንጹሕ ልብ ግን እየጠፋ ነው ። ሌላው ችግር በጸሎት ይፈታል ፣ የጸሎት መስመር ከተዘጋ ግን በምንም ይከፈታል ? ከምህላ በፊት ይቅርታ እንደሚያስፈልግ እንዴት ተዘነጋ ?
በእውነተኛ ልብ ሁነው ይቅርታ የሚጠይቁ መሳሳታቸውን አምነዋልና ይቅርታችንን ልንሰጣቸው ይገባል ። ምሕረት ማለት ለተራበ እንጀራን ፣ ለበደለ ይቅርታን መስጠት ነው ። ጥሩ የለበሱ ሰዎች ጥሩ መብላታቸውን እጠራጠራለሁ ። ልብስ የዓመት ነው ፤ ሆድ ግን የዕለት ነው ። አምና በገዙት ልብስ እንዳንለካቸው መጠንቀቅ ያስፈልጋል ።
ሰላም ዕለታዊ ርእስ ፣ የመንግሥታት ስብሰባ አጀንዳ ናት ። ሰላም እንዳይመጣ የሚጥሩ ብዙ ወገኖች አሉ ። የጦር መሣሪያ ነጋዴዎች ፣ የሕዝብ ቊጥር እንዲቀንስ የሚያሰሉ አዋቂ ተብዬዎች ፣ በዕዳ የሚፈለጉ ወንጀለኞች ፣ መኖርን የተመረሩ ስልቹዎች ፣ ሥራን ጠልተው በመዝረፍ መክበር የሚሹ የጥፋት ጓዶች ፣ ትዕቢት ያነቃቸው ነገሥታቶች ፣ ግላዊ ጉዳታቸውን አገራዊ የሚያደርጉ ተገፊዎች እነዚህ ሁሉ ሰላምን አይፈልጉም ። ሰላም እንዳይሆንም ይጥራሉ ። ሰላም ስትያዝ እርካሽ ፣ ስትጠፋ ግን ውድ ናት ። ሰላም በማጣት ገበሬ የዘራውን አያጭድም ፣ ነጋዴ ሮጦ አያተርፍም ፣ የተለያየው ወገን አይገናኝም ፣ ልጆች ለድንጋጤና ለአእምሮ ስብራት ይዳረጋሉ ፣ በሽተኞች መታከም አይችሉም ። ጤና ባይኖር በገንዘብ ለመዳን ይሞከራል ። ገንዘብ ባይኖር በጤና መጽናናት ይቻላል ። ሰላም ግን ሁሉም ነገር ነውና ከራሱ ውጭ ምንም ምትክ የለውም ። ሰላም ብንሆን እንኳ በቀጣይ አሥር ዓመታት ማደግና መለወጥ ከቻልን መልካም ነው ። አንድ ቀን ሰላም ስናጣ የአንድ ዓመት ዕድገታችን ይዘገያል ። ሰላም መጣት የዛሬ ቊስል ፣ የነገ ጠባሳ ነው ። ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሰላም ያስፈልገናል ። ሰላም ግን ዋጋ ያስከፍላል ። ከእኔ ይቅር ካላሉ ሰላም ከየት ይገኛል ?
ሐዋርያው፡- “ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን” ብሎ መመረቁ እውነት ነው ። የእግዚአብሔር ሰዎች የሚያዩበት መነጽር ረቂቅ ነውና ሐዋርያው የጎደለንን በትክክል አውቋል ።
ጸጋ ፣ ምሕረትና ሰላም የሚገኙት የእግዚአብሔር አባትነት የክርስቶስ ጌትነት ሲገባን ብቻ ነው ። የእግዚአብሔርን አባትነት ስንረዳ ጸጋን የምንቀበል ብቻ ሳይሆን በጸጋ የምንለቅቅ እንሆናለን ። ምሕረት ተደርጎልናልና እንደ ተቀበልነው ለመስጠት አንፈተንም ። ሰላምን አግኝተናልና ሌላውን አናውክም ። የክርስቶስ ጌትነትም ሕይወታችንን ሲገዛ ጸጋ እናገኛለን ። ጸጋ ማለት የዘላለም ሕይወት ነው ። ይህ የሚገኘው ወልድ ዋሕድ ፣ ቤዛ ኩሉ ዓለም ብሎ በክርስቶስ በማመን ነው ። በክርስቶስ ጌትነት የምናገኘው እንጀራን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ የኃጢአት ይቅርታን ነው ። ይህም ምሕረት የተባለው ነው ። የእግዚአብሔር ሥልጣን ባይኖር የአንድ ቀን እንጀራ መቊረስ ባልቻልን ነበር ። እርሱ ባይሆንም እኛን ይቅር የሚል አይኖርም ነበር ። እርሱ ይቅር ላለንም የሚበሳጩ ብዙ ፈሪሳውያን አሉ ። ሰላሜን እሰጣችኋለሁ በማለት ኪዳን የገባልን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ። ሰላም የእርሱ መለኮታዊ ገንዘብ ናት ።
ብዙ ሰው በነፍሱ እየባከነ ነው ። እኔን የሚቀበል አምላክ የለም እያለ ለገዛው ነገር እንደገና እየተገዛ ለመኖር የወሰነ ነው ። ስብከቶችም ፍርድ እንጂ ወንጌል አይደሉም ። የሚያደናብር ፣ በሌላው ኃጢአት የራሱን ጽድቅ የሚሠራ ሰባኪ አያሌ ነው ። በዚህ ዘመን ጸጋ ወይም የሥላሴ ቸርነት አብዝቶ ሊነገር ይገባዋል ። “ደም በደም አይጠራም” እንዲሉ ኃጢአት በሌላ ኃጢአት አይወገድም ። የክርስቶስ ደም ለምሕረት ቁሟል ። እኔ አልድንም በማለት ዘወትር ሰላም በማጣት ፣ በሱስ ውስጥ የተደበቁ አያሌ ወገኖች አሉ ። አይዟችሁ እግዚአብሔር እናንተን በጸጋው ወዶአችኋል ። በምሕረቱም ነፍሳችሁን ከእስራት ይፈታል ። ሰላሙንም ሰጥቶ የጨው ውኃ ከመጠጣት ፣ ወይም ከኃጢአት ደስታን ከመፈለግ ያድናችኋል ።
የሐዋርያው ምርቃት በራሳቸው ብቃት ለሚመጻደቁ አሜን የሚያሰኛቸው አይደለም ። እኔ ኃጢአተኛ ነኝ የምትሉ ግን አሜን በሉ ። በአሚነ ሥላሴም ጽኑ ። ንስሐ ግቡ ፤ የበደላችሁትን ሰው ይቅርታ ጠይቁ ። በልባችሁም እንዲህ ጸልዩ፡-
ጌታ ሆይ ከአሉተኛ ትውልድ ፣ ይህን አሉ ከሚል ማንነትም አድነኝ ። የተዘረጋልኝን የቸርነትህን ጥላ እንድጠለልበት እፈልጋለሁ ። ምሕረትና ሰላምህ ከእኔ ጋር ይሁን ። ያለፈውን ዘመን ስህተቴን ይቅር በል ። ለዘላለሙ አሜን ።
1ጢሞቴዎስ /7/
ኅዳር 11 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ