ስሜት የብረት ድስት ነው ፣ ሲጥዱት ቶሎ ይግላል ፣ ሲያወርዱት ቶሎ ይቀዘቅዛል፤ እውነት የሸክላ ድስት ነው ፣ ቶሎ አይግልም ፣ ቶሎ አይበርድም ። ስሜት የእንጀራ እናት ጡጦ ነው ፣ እውነት ግን የሚያጠግብ የወተት ጋን ነው ። ስሜት ችግኝ ነው ፣ እውነት ግን የሚያስጠልል ዛፍ ነው ። ስሜት መጣሁ ብሎ የሚሄድ የመስከረም ዝናብ ነው ፣ እውነት ግን የሚያጠግብ የነሐሴ ጠል ነው ። ስሜት የአሁን ንጉሥ ነው ፣ እውነት ግን ነገም የሚኖር ኃይል ነው ። ስሜት የርችት መብራት ነው ፣ እውነት ግን ግለቱ የሚጨምር የፀሐይ ብርሃን ነው ። ስሜት ቀን ነው ፣ ማታ ለመሆን ይቸኩላል ፤ እውነት ሌሊት ነው ፣ ወደ ቀን ይጓዛል ። ስሜት ሁሉን የሚያረክስ ነው ፣ እውነት ሁሉን የሚቀድስ ነው ። ስሜት ሮጦ የሚደክም ነው ፣ እውነት እያዘገመ የሚደርስ ነው ። ስሜት ተሳዳቢ ነው ፣ እውነት ግን አሸናፊ ነው ። ስሜት እገሌ የሚል ጠቋሚ ነው ፣ እውነት ግን እኔ የሚል ተነሣሒ ነው ። ስሜት ሰጥቶ የሚቆጭ ነው ፣ እውነት ግን ሰጥቶ የሚደሰት ነው ። ስሜት የእኔ ቃል የእግዜር ቃል የሚል ነው ፣ እውነት ግን የእግዚአብሔርን የሚያስቀድም ነው ። ስሜት ግልብ ነው ፣ እውነት ግን እውቀትን ያደላደለ ነው ። ስሜት ቢሞትም ሰማዕት አያሰኝም ፣ እውነት ግን የጽድቅ አክሊል አላት ። ስሜት ኢየሱስ ጌታ ነው እያለ በሥራው ያዋርደዋል ፣ እውነት ግን ክርስቶስን በሕይወቱ ያከብረዋል ። ስሜት በሬ ይነዳል ፣ እውነት ግን ራሱን ይሰጣል ።
ስሜት ግሎ ያጋግላል ፣ እውነት ግን ሰምቶ ይጋግራል ። ስሜት የቅጠል እሳት ነው ፣ አያበስልም ኋላም አመድ የለውም ፤ እውነት ግን የሚያበስል ቀጥሎም የሚያሞቅ ፍም ያለው ነው ። ስሜት ጊዜያዊ እብደት ነው ፣ እውነት ግን መጥኖ መኖር ነው ። ስሜት ተናግሮ የሚያስብ ነው ፣ እውነት ግን አስቦ የሚናገር ነው ። ስሜት ከውድቀቱ የሚማር ነው ፣ እውነት ግን በነጻ የሚማር ነው ። ስሜት ወደድሁ ሲል ያብዳል ፣ እውነት ግን ፍቅር ለዘላለም መሆኑን ያምናል ። ስሜት በአሳብ ይሰጥና ቆይቶ ይከለክላል ፣ እውነት ግን “የእኔ ድጋፍ የሚያስፈልገው ለማን ነው ?” ይላል ። ስሜት ጭብጨባ ምሱ ነው ፣ እውነት ግን ጭብጨባን የሚጠየፍ ነው ። ስሜት ፍሬን የለውምና ይጋጫል ፣ እውነት ግን ማብረጃ አለው ። ስሜት ኃይል ሲሆን ራሴ መሪ ካልሆንሁ ይላል ፤ እውነት ግን “እግዚአብሔር ሆይ ምራኝ” ይላል ። ስሜት ቊጣና ስድብ የሚባሉ ልጆች አሉት ፣ እውነት ግን እውቀትና ተግባር የሚባሉ ልጆች አሉት ።
ስሜት ከሚያደርገው የሚያወራው ይበዛል ፣ እውነት ግን ሥራው ይናገር ብሎ ያከናውናል ። ስሜት እንደ ማር ይጣፍጣል ፣ ከደቂቃ በኋላ እንደ እሬት ይመራል ፤ እውነት ግን መጀመሪያ መራራ ቀጥሎ ጣፋጭ ነው ። ስሜት ሲሰበክ በመነንሁ ይላል ፣ ቀጥሎ ይዘፍናል ፤ እውነት ግን መስቀሉን ለመሸከም ጎንበስ ይላል ። ስሜት አሁን አመስጋኝ አሁን ተራጋሚ ነው ፣ እውነት ለሁለቱም አይቸኩልም ። ስሜት ከነቆቡ የሚዘልል ነው ፣ እውነት ግን ዓላማውን የሚያከብር ነው ። ስሜት ልጅ ያደርጋል ፣ እውነት ግን ትልቅ ያደርጋል ። ስሜት ጦርነትን ይለኩሳል ፣ ማብረድ ግን አይችልም ፤ እውነት ግን ለሰላም ዋጋ ይሰጣል ። ስሜት “ካፈርሁ አይመልሰኝ” ይላል ፣ እውነት ግን ገና ለመታረም ይኖራል ። ስሜት ተግሣጽ ጠላቱ ነው ፣ እውነት ግን ምከሩኝ የሚል ነው ። ስሜት እስኪገባ የሚቸኩል ፣ ከገባ በኋላ ልውጣ የሚል ነው ፤ እውነት ግን ዋጋውን ተምኖ የሚገባ ፣ በትዕግሥትም ነገሩን የሚፈጽም ነው ። ስሜት ራሳችንን የምንታዘብበት ነው ፣ እውነት ግን ራሳችንን የምናርምበት ነው ።
ጌታ ሆይ በስሜት ሳይሆን በእውነት እንድመላለስ እርዳኝ !
ነሐሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.