የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰው ማለት

 “በርታ ሰው ሁን” 2ነገሥ. 2፡3
ንጉሥ ዳዊት ልጁ ሰሎሞንን የመከረው የመጨረሻው ምክር ነው ። ሰው መሆን ጥልቅ ምሥጢር ያለው ፣ በዚህ ዓለም ላይ የመገኘታችንን ዓላማ የሚያሟላ ነው ። በዘመናት የተነሡ የእግዚአብሔር ሰዎች ሰው ፈልገዋል ። በየዘመናቱ የጮኹ ፈላስፎችም ሰው በመፈለግ ቃትተዋል ። የፈለጉት ሰው መልኩና ቅርጹ ሰው የሆነ ሳይሆን ልቡ ሰው የሆነ ነው ። በጎነትን የለበሰ ፣ ፍቅርን የደረበ ፣ ፍትሕን የተዋበ ሰው ፈልገዋል ። “ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሰው የጠፋ ዕለት” ተብሏል ። በማይጨው ጦርነት ኢትዮጵያ ድል ሲርቃት ፣ ንጉሡ አገር ለቀው ለአቤቱታ ሲጓዙ ገበሬው ያለሁት መሪ እኔ ነኝ አገሬን አላስደፍርም ። ነጻነቴን ሰጥቼም በክብር ልኖር አልችልም በማለት ራሱን ሹሞ ተዋጋ ። የሚደንቀው ጨዋነቱ ንጉሡ ሲመጡ የነጻነቱ ዓርማ አድርጎ ተቀበላቸው እንጂ እኔ ልንገሥ በማለት አልተጣላም ። ሰው በጠፋ ቀን ሰው ሁነው የተገኙ አያሌ ኢትዮጵያውያን አሉ ። ደጃች በላይ ዘለቀ ፣ ራስ አበበ አረጋይ ፣ የአድዋው ድል ሳይበቃቸው በሽምግልናቸው የተዋጉ ደጃች ባልቻ … እነዚህ ሁሉ ሰው የጠፋ ቀን ሰው ሁነው የተገኙ ናቸው ። ዛሬ በቋንቋችን የምናወራው ፣ ስማችን የጣልያን ያልሆነው ፣ ነጻ ባንዲራ የያዝነው በእነዚህ ሰው ሁነው በተገኙት አርበኞች ነው ። የተዋጉት ለአገር ፣ ለሃይማኖት ፣ ለነጻነት ነው ። እነዚህ ሦስት ነገሮች ከሌሉ የሰውነት ክብር ዝቅ ይላል ።
ንጉሥ ዳዊት፡- “በርታ ሰው ሁን” ብሎ ሲናገር ጌታችን ደግሞ “ከሰዎች ተጠበቁ” በማለት ተናግሯል ። ማቴ. 10፡17 ። የአዲስ ኪዳንን መጻሕፍት ብቻ በማገላበጥ በሰውነት ወግ ስላልተገኙና የእንስሳትና የአራዊት ስያሜ ስለተሰጣቸው ሰዎች እናያለን ።
  1-  እፉኝት፡- እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?” ማቴ. 3፡7 ። ይህንን ቃል የተናገረው መጥምቁ ዮሐንስ ነው ። ስለ እፉኝት እባብ የሚተረክ አለ፡- እፉኝት የተባለ የእባብ ዘር በዘመኑ አንድ ጊዜ ብቻ ከሴቷ ጋር ሩካቤ ባደረገ ጊዜ ይሞታል ። ሴቷ እፉኝትም የፀነሰቻቸው ሆዷን ቀደው ሲወጡ ትሞታለች ይባላል ። እፉኝት ስትፀንስ ባሏን ትገድላለች ፣ ስትወልድ ልጆችዋ ይገድሏታል ማለት ነው ። መጥምቁ ዮሐንስ የእፉኝት ልጆች በማለት ከሰውነት ክብር የወረዱትን ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንን ገሥጾአል ። እፉኝት ዘር የሰጣትን ትገድላለች ፣ ክፉዎችም ለአገር ለትውልድ የሚተርፍ ነገር የሰጡትን ሰዎች ይገድላሉ ። ማወቅ ዕዳ እስኪመስል በአገራችን ስንት ሊቃውንት ተፈጁ ። ጮሌ እንጂ እውነተኛ መኖር ያልቻለባት ፣ እሳት የላሱ ደንቆሮዎች ያደከሟት አገር ናት ። ሥርዓት ሲለወጥ አብረው የሚለወጡ ፣ መገልበጥ የማይሰለቻቸው ፣ ከታቦትም ከዳጎንም ኅብረት ያላቸው አያሌ ናቸው ።እነዚህ እንደ እፉኝት ፣ ዘር የሚሰጡትን በመግደል የሰለጠኑ ናቸው ። ዘር የሰጣትን የገደለች እፉኝት የምትወልዳቸው ይገድሏታል ። መልካም ያደረጉትን ፣ አገር ያቀኑትን በማጥፋት የተሰማሩ ፍጻሜአቸው በወለዱአቸው መሞት ነው ። “አብዮት ልጇን በላች” እየተባለ ሲነገር የነበረው እፉኝትነት ሰልጥኖ ስለነበር ነው።
 ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ለክብርና ለሥልጣን ሲጋደሉ ብዙ ነቢያትንና አባቶችን አስገደሉ ። በዘርፋፋው ቀሚሳቸው ውስጥ ጦርና ጎራዴ ነበር ። የቻሉትን ራሳቸው ፣ ያልቻሉትን ለሮማውያን አሳልፈው በመስጠት አገርን አመከኑ ። መጨረሻ ግን በወደዷቸው ሮማውያን ተደመሰሱ ። በነጠላ የሚገድልልን ጠላት መጨረሻ ላይ በጅምላ ይገድለናል ። ዛሬም ያስተማሩንን ፣ ያገለገሉንን ፣ ያጽናኑንን መግደል ቋሚ ሥራ ሁኗል ። በመግደል ስብከት የፀነስናቸው ሲወለዱ እኛን መግደላቸው እርግጥ ነው። ክፋትን በማስተማር የምንወልዳቸው ከእኛ የባሱ ክፉዎች ይሆናሉ ። ሌላውን በመግደል የኖረ ማንም የለም ። ገዳዮች ለጊዜው ይንጎማለላሉ ፣ ቀጥሎ በወለዱአቸው ልጆች ይወገዳሉ ። የዓለም ታሪክ የምንለው በአመዛኙ የእፉኝት ታሪክ ነው ።
    2-  ድንጋዮች፡- ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።” ማቴ. 3፡9 ። ድንጋዮች በማለት መጥምቁ ዮሐንስ የገለጣቸው አሕዛብ ናቸው ። ልጆቻቸውን ለጣዖታት ሲሠዉ ምንም የማይሰማቸው ፣ ርኅራኄ የራቃቸው ድንጋዮች ነበሩ ። የማይርሱ ፣ በፍቅር የማይማረኩ ፣ ውለታን የማያስቡ ፣ ብዙ አማልክትና ብዙ ትዳርን የተለማመዱ ድንጋዮች ነበሩ ። ድንጋይ የኒውክለር መነሻ ናት ፣ አቤል የሞተው በድንጋይ ነው ። ድንጋይ ገዳይነት ነው ። ሰው መሆን ያቃታቸው ድንጋይ ይሆናሉ ። ለገዛ ልጆቻቸው ሳይቀር ኃላፊነት የማይሰማቸው ፣ ወልደው የሚክዱ ፣ በየስፍራው በመውለዳቸው ክብር የሚሰማቸው እነዚህ ድንጋይ ናቸው ።ልጆቻቸውን ለዘመናዊነትና ለኃጢአት ሲሠዉ ቅር የማይላቸው ፣ ገንዘብ ያምጣ እንጂ ልጅ ቢሸጥ መልካም ነው ብለው የሚያስቡ ከሰውነት ወደ ድንጋይ ዝቅ ያሉ ናቸው ። በቀላሉ የማይነኩ የድንጋይ ልብ ያላቸው ፣ ፍቅር የማይስባቸው ፣ በአንድ የማይረጉ ፣ ለአሚናቸው የማይታመኑ ድንጋይ ተብለዋል ። ጌታ ግን ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆችን ያስነሣል ። በነቢዩ ሕዝቅኤልም፡- የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ” በማለት ተስፋ ሰጥቶ ነበር። ሕዝ. 36፡26 ።
  3- ውሾች፡- በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ ።” ማቴ. 7፡6 ። ውሾችና እሪያዎች የተባሉት መናፍቃን ወይም የስህተት ትምህርት የሚያስተምሩ ናቸው ። የተቀደሰና ዕንቁ የተባለው የእግዚአብሔር ቃል ነው ። ውዱን ቃል እንዲሁ ማባከን እንዲረገጥና መልሰው እንዲሰድቡን የሚያደርግ ነው ። ውሻ የተፋውን መልሶ ይልሳል ። የኑፋቄ ትምህርት የለከፈው ሰውም ወጣሁ ሲል ተመልሶ ይያዛል ። የኑፋቄ ትምህርት በቀላሉ ከነፍስ ውስጥ አይወጣም ። ኑፋቄ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ነገር ግን እግዚአብሔር የለሽ ሰውን የሚፈጥር ነው ። እርያም ታጥቦ መልሶ ጭቃ ላይ ይንከባለላል።የመናፍቃን ንስሐም እንደማይረጋ ከአርዮስ ታይቷል ። ከስህተት ትምህርት መጠበቅ ያለብን ዋጋ ስለሚያስከፍል ነው ። ኑፋቄ ዘመንን በሚመስል ነገር የሚጨርስ ነው ። ኑፋቄ እኔ ልክ ነኝ ለማለት እነ እገሌ ተሳስተዋል እያለ የሚያዜም ነው ። ራስን ለማየት ጊዜ ያሳጣል ። ዘወትርም እንዲህ ተብሏል እንዲህ ብለን መልስ እንስጥ የሚል የሙግት ዓለም ነው ። መቃወምና መንቀፍ ፣ ራስን ግን መቆለል ዓይነተኛ ባሕርይው ነው ።
“በርታ ሰው ሁን” የሚለውን የንጉሥ ዳዊትን የመጨረሻ ምክር መስማት በእውነት ተገቢ ነው ። ሰው በመጨረሻ ሰዓት የሚናገረው ሐቁን ብቻ ሳይሆን የዘመኑን የተጨመቀ ምክርም ነው ። በርትቶ ሰው ያልሆነ እፉኝት ሁኖ መጀመሪያ ገዳይ ከዚያም ሟች ይሆናል ። ድንጋይ ሁኖ የማይርስ ፣ ለገንዘብ እንጂ ለፍቅር ግድ የሌለው ፣ ማንም ቢወድቅ የማያዝን ይሆናል ። ውሻ ሁኖ የተፋውን ይልሳል ፣ ወጣሁ ሲል ይያዛል ። በማይረጋ ንስሐ ይኖራል ።
“በርታ ሰው ሁን ።” ዛሬም ሰው እየጠፋ ነው ። እውነት የሚናገር ደግ ሰው እያጣን ነው ። መተማመን ጎድሎንም ፊትና ኋላ መሄድ የማንችል እየተጠባበቅን የምንጓዝ የጅብ መንገደኞች ሁነናል ። ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው መሆን ያስፈልገናል እንጂ “ሰው የለም” እያልን ማዘን ምን ይጠቅመናል ? ሰው የለም ማለት ክብር የለውም ፤ ሰው ሆኖ መገኘት ግን ለዛሬ ደስታ ፣ ለነገ ታሪክ ነው ።
የዓለማትና የዘመናት ፣ የዳርቻዎችና የአድማሳት ፈጣሪ ፣ መቻልህ አጋዥ ፣ መሥራትህ አማካሪ የሌለው ፣ እኔ ነኝ ብለህ ያሳረፍከን ፣ በስምህም ነጻ ያወጣኸን ቡሩክ የዓለም ተስፋ ተመስገን ። እባክህን ሰው መሆንን አድለን ።አንተ የመረጥከው ዓይነት ሰው አድርገህ ሥራን ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 26
ግንቦት 26 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ