“የእግዚአብሔር መንፈስ ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል ። እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል ። ዓይኑም እንደምታይ አይፈርድም፥ ጆሮውም እንደምትሰማ አይበይንም” ኢሳ. 11፡2-3 ።
ስለ መሢሑ ከተነገሩ ትንቢቶች አንዱ ነው ። እነዚህ ሀብታትም ሰባት ሀብታት ናቸው ። ጥበብ ፣ ማስተዋል ፣ ምክር ፣ ኃይል ፣ እውቀት ፣ እግዚአብሔርን መፍራት ፣ በማየትና በመስማት አለመፍረድ ናቸው ። እነዚህ ሀብታት ጥንድ ፣ ጥንድ በመሆን ተቀምጠዋል ። ጥበብና ማስተዋል ፣ ምክርና ኃይል ፣ እውቀትና እግዚአብሔርን መፍራት በጥንድ ሲቀመጡ ፤ እንዳየና እንደ ሰማ አለመፍረዱ ለብቻው ተቀምጧል ። ጥበብ ያማረ ፍጻሜ ወይም ሥራን በውበት መደምደም ነው ። ጥበብ የሌለው ነገር ሁሉ የባከነ ነው ። ማስተማርም ፣ መምራትም ፣ መሥራትም ፣ መዳኘትም በጥበብ ሊሆን ይገባዋል ። እውቀትን የገፉ ሰዎች ጥበብን መግፋት አይችሉም ። ጥበብ ልብን የመማረክ አቅም አለው ። ጥበብ ደረቅ ንግግሮችንና ተግባራትን ያስቀራል ። የማይገባ ዋጋ እንዳንከፍል ከሚያግዘን ነገር አንዱ ጥበብ ነው ። ጥበብ ማለት ብልጠት ማለት አይደለም ። እውነትን በፍቅር የማሰረጽ አቅም ነው ።
ማስተዋል ከመናገር ከማድረግ በፊት ውጤቱን መገምገም ነው ። ማስተዋል ከትላንት ጉዳቶችና ከዕድሜ ልምድ የሚገኝ ሲሆን በዋናነትም የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ነው ። ማስተዋል ነገሮችን ሁለት ጊዜ የማየት ዓይን ይሰጣል ።ማስተዋል ዛሬን ሳይሆን ነገን ፣ ራስን ሳይሆን ሰዎችን በቸር የሚያይ ነው ። በማስተዋል ውስጥ ፍጥነትና ቁጥብነት ተዋድደው ይሄዳሉ ። ማስተዋል አደጋን ባያስቀር እንኳ አደጋን የመቀነስ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ። ማስተዋል ጊዜያዊ ደስታን የሚንቅ ፣ ሰማይን አሻግሮ የሚመለከት ነው ።
ምክር ትልቅ የመንፈስ ቅዱስ ሀብት ነው ። ማንም ሰው መምከር አይችልም ። እንኳን መምከር ለመመከርም አቅም ያስፈልጋል ። ምክር በፍቅር ከረጠበ ልብ ውስጥ የሚወጣ የእውነት ወንዝ ነው ። ምክር ትልቅ ምጽዋት ነው ። ነገሥታትና ባለጠጎች ሳይቀር የሚፈልጉት ስጦታ ምክር ነው ። ምክር ሕይወትን ቀላል የማድረግ አቅም አለው ። ምክርን ሲሰሙት ሳይሆን ሲኖሩት ትልቅ ጥቅም ያስገኛል ። ምክር ከአደጋ በፊት የሚያስጠነቅቅ ሲሆን ከአደጋ በኋላም የመነሣት ጉልበት የሚሆን ነው ። ምክር የሌለው ሕይወት የሚማረው ዋጋ እየከፈለ ነው ። ምክር የመንፈስ ቅዱስ በመሆኑ ነጻ ስጦታ ነው ። ነገር ግን ርካሽ አይደለም ። እግዚአብሔር የምክር ጸጋን ይሰጣል ።
ኃይል ሌላውን ለመጣል ሳይሆን ራስን ለማሸነፍ የሚሰጠን ትልቅ በረከት ነው። የታመመውን ለመፈወስ ፣ የወደቀውን ለማንሣት የሚሰጥ ሀብት ቢኖር ኃይል ነው ። ኃይል የማይፈልግ ዓለምና ሰው የለም ። ሕይወት የኃይል ጥገኛ ናት ። ቀኑን በድል ለመፈጸም ብቻ ሳይሆን በዚህች ቅጽበትም በተስፋ ሙላት ለመሆን ኃይል ያስፈልጋል ። ሰው ኃይሉን ሲጨርስ የመኖር ፍላጎቱ እያነሰ ይመጣል ። ለትካዜም ይዳረጋል ። እግዚአብሔር ግን የኃይልን መንፈስ ይሰጣል ።
እውቀት ብርሃን ነው ። የሚያውቅ ሰው ከባዶነት ስቃይ የተፈወሰ ነው ። እውቀት ከስህተት ውሳኔ ይጋርዳል ። ያመኑበትን እንዳያፍሩበት ይረዳል ። ሰው ያመነበትን በድፍረት የሚይዘው ስለሚያምነው ነገር የሚያውቅ ከሆነ ብቻ ነው ። እውቀት የነፍስ ቀለብ ነው ። አእምሮ ያለ እውቀት እየዛገ ይመጣል ። ታዳሽ አእምሮ የምናገኘው በእውቀት ነው ። እውቀትን ማናዳብር ከሆነ መዘንጋት ውስጥ እየገባን እንመጣለን ። እግዚአብሔር የእውቀትን መንፈስ ይሰጣል ።
እግዚአብሔርን መፍራት ትልቅ ሀብት ነው ። እግዚአብሔርን የሚፈራ የሚያስፈሩት ነገሮች ሁሉ ይወድቁለታል ። እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እግዚአብሔር በዙፋኑ ሁኖ ሁልጊዜ ይታየዋል ። መውጣት መግባቱን የሚቆጣጠሩ የማይከደኑ ዓይኖች እንዳሉ ያውቃል ። እግዚአብሔርን መፍራት በብርሃንም በጨለማም እንድንቀደስ ያደርጋል ። እግዚአብሔርን መፍራት ምንም ባናተርፍ ኅሊናን ለማትረፍ ይረዳል ። እግዚአብሔርን መፍራት የእውቀት ጉልላት ነው ።
እንዳዩና እንደ ሰሙ አለመፍረድ ትልቅ ሀብት ነው ። ብዙ ሰው የዓይኑና የጆሮው ጥገኛ ነው ። ባየውና በሰማው ለመፍረድ ይቸኩላል ። የእግዚአብሔር መንፈስ ግን ከምናየውና ከምንሰማው ጀርባ ያለውን ድካም በማየት ያዝናል ። ይራራል ። ሰው ያንን ያደረገው ክፉ ስለሆነ ሳይሆን መልካሙን መለየት ስላልቻለ ነው በማለት በቅንነት ያያል ።
ሀብታቱ በጥንድ ተጠቅሰዋል ። “የእግዚአብሔር መንፈስ ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል ።” ጥበብና ማስተዋል በአንድ ላይ ተጠቅሰዋል ። ጥበብ ካለ ማስተዋል አለ ፤ ማስተዋል ጉድለቱን ሲያይ ጥበብ ደግሞ ይሞላዋል ። ምክርና ኃይልም በአንድ ላይ ተጠቅሰዋል ። ምክር ባለበት ድል አለና ። እውቀትና እግዚአብሔርን መፍራት በአንድ ላይ ተጠቅሰዋል ። እወቀት ኃይል ሲሆን ፈሪሀ እግዚአብሔር መሪ ነውና ። ከሁሉ በላይ ሰባተኛው ሀብት እንዳዩና እንደ ሰሙ አለመፍረድ ነው ። እኔ ያየሁትንና የሰማሁትን ክርስቶስ ቢያይና ቢሰማ ምን ያደርግ ነበር ? ማለት ይህ ያለ መፍረድ ሀብት ነው ። እነዚህን ሀብታት ይጨምርልን ።
ጌታ ሆይ ዛሬም እንደ ጥንቱ ፍቅር ነህ ። ዓመታት አያደክሙህም ። ውበትህም እንዳበራ ይኖራል ። በእነዚህ ሀብታት ውስጥ ራሳችንን ስናየው የጎደለን ይህ ነውና ሀብታቱን አፍስስልን ። የተዘባረቀውን ሕይወታችንን አስተካክልልን ። የዚህን ዓለም ሸለቆ እንድንወጣው እባክህን ጸጋን በሙላት ልቀቅልን ። ያንተ የሆነው በጎ ነገር ሁሉ አይለፈን ። በተባረከው ተስፋህ ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 11
ግንቦት 10 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ ተጻፈ በአዲስ አበባ