የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለእኛም እዘንልን

“ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው ።” ማቴ. 9፡36 ።
ጌታችን ይህን ቃል በሚናገርበት ጊዜ ጲላጦስና ሄሮድስ የሮማን መንግሥት ወክለው የሕዝቡ መሪ ነበሩ ። የሕዝቡ መንፈሳዊ ራስ ነን የሚሉ ካህናትና ሊቃነ ካህናት በመብዛታቸው በተራ ያስተዳድሩ ነበር ። የእግዚአብሔር ቤት ጠባቂ ነን የሚሉ አእላፋት ሌዋውያን የዘር ተዋረዳቸውን ጠብቀው አደግድገው ቆመዋል ። ከቤተ ክህነት ሥልጣን አንፈልግም ነገር ግን የአገርና የሃይማኖት ነገር ያሳስበናል የሚሉ ፈሪሳውያን በዘርፋፋውና በደማቁ ልብሳቸው ከተማውን ሞልተዋል ። ሰዱቃውያንም ሃይማኖትን ከምቾት ጋር መያዝ አለብን ብለው በሀብትና በባለሥልጣኖች ዘንድ ሞገስ በማግኘት ተደስተዋል ። ይህን ሁሉ አናይም ብለው ደግሞ የመነኑ በኩምራን ዋሻዎች ተደብቀው ቅዱሳት መጻሕፍትን በመገልበጥ ሥራ የተሰማሩ ኤሴያውያን  የሚባሉ ወገኖችም ነበሩ ። ጌታ ግን ሕዝቡ እረኛ የለውም በማለት ተናገረ ። ቊጥራቸው ስድስት ሺህ የሚያህሉ ፈሪሳውያን ምኩራባቱን ተቆጣጥረው በየመንደሩ ያለውን አገልግሎት በእጃቸው አስገብተው ነበር ። ሰዱቃውያን ደግሞ ቤተ መቅደሱን ያስተዳድሩ ነበር ። የእኔ አስተሳሰብና ሃይማኖት ይልቃል እያሉ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ይጣላሉ ። ለሕዝቡ የሚበጀውን የማሳየው እኔ ነኝ እያሉ የሃይማኖት ቡድኖች ይደባደባሉ ። ጌታ ግን ሕዝቡ እረኛ የለውም እያለ ነው ።
ጌታችን እረኛ አለመኖሩን የተናገረው ሕዝቡን እንጂ እረኞችን አይቶ አልነበረም ። ሕዝቡን በማየት እረኛ መኖር አለመኖሩን ማወቅ እንደሚቻል እያሳየን ነው ። ራስ ምታት የአንድ ሕመም ማሳያ መገለጫ ነው ሲባል እንሰማለን ። የመሪዎች መገለጫም ሕዝቡ ነው ። ሕዝቡ ብዙ ነው ፣ እረኛ ግን አልነበረውም ። የቊጥር አለመመጣጠን ሳይሆን የእረኝነት ልብ ያለው አልነበረም ። የከረሩ የሃይማኖት ክርክሮች ፣ ጠንካራ የሆኑ ስብከቶች ሊካሄዱ ይችላሉ ። ሕዝቡ ግን እረኛ አልነበረውም ። ሃይማኖትን በዕብራይስጥ ፣ በግሪክ ፣ በላቲን ፣ በሱርስት ቋንቋ የሚተረጉሙ ነገር ግን ሕዝቡን ማሰማራት ያልቻሉ እረኞች ነበሩ ማለት ነው ።
ሕዝቡ በመንደርም በምኩራብም ፣ በጲላጦስም በቀያፋም ኀዘነተኛ ነበረ ። ከቤተ መንግሥቱ ባይደላው የሚጽናናበት መንፈሳዊ እረኛ አልነበረውም ። ለሥጋው አድሮ ነፍሱን በደለ እንዳይባል ረሀብተኛ ነው ፤ ለነፍሱ አድሮ ሥጋውን በደለ እንዳይባል በክፋት የተያዘ ነው ። ጌታ እረኛ እንደሌላቸው አየ ። እረኛ የሌለው ሕዝብ ምልክቱ መጨነቅና መጣል ነው ። መጨነቅ ነገሮች አጋንኖ ማየት ነው ። ነገሮችን ያለ እግዚአብሔር ማየት እርሱ መጨነቅ ነው ። መጨነቅ ወደ ጎረቤት እንጂ ወደ እግዚአብሔር መጮህ አለመቻል ነው ። መጨነቅ የታወቁና ያልታወቁ በሽታዎች መነሻ ነው ። መጨነቅ ምግብ የሚዘጋ ወይንም ብዙ ምግብ የሚያስበላ ነው ። መጨነቅ በውስጡ ቀጥሎ እንዲህ ቢሆንስ የሚል ስጋት ያለው ነው ። የሚገልጥለት አጥቶ የሚያጋልጠው አገልጋይ ያተረፈ ሕዝብ የተጨነቀ ነው ። የተንሸራተተበትን ቦታ ትቶ የወደቀበትን ቦታ የሚያሳየው እረኛ ያለው ሕዝብ የተጨነቀ ነው ። ራሱን የሚያሰማራና ሕዝቡ ምን ይሆናል ? ሳይሆን እኔ ምን እሆናለሁ ? የሚል መሪ ያለው ሕዝብ የተጨነቀ ነው ። ጌታችን ሕዝቡ እረኛ የለውም እያለ ነው ። እረኝነት ጸጋ ነው ። እረኝነት ለአንዳንዶች የሚሰጥ ጸጋ ነው ። እረኝነት በዙር የሚደርስ የደቦ ሥራ አይደለም ። እረኝነት በተራ እንብላ የሚባልበት የጅብ ሰርግ አይደለም ።
የተጣለ ሕዝብ ፈላጊ ያጣ ሕዝብ ነው ። ከውጤቱ ይማር ተብሎ የተተወ ወገን ነው ። ለትልቁም ለትንሹም ትምህርት ሕይወቱን አስይዞ የሚማር ነው ። ገንዘቡ እንጂ እርሱ የማይፈለግ ነው ። “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚሉ እረኞች ሲነሡ ሕዝብ የተጣለ ይሆናል ። ሕዝቡን ሳይሆን ሥልጣናቸውን የሚጠብቁ መሪዎች የገጠመው ሕዝብ የተጣለ ይሆናል ። ሲያመሽ የት አመሸህ ? የማይባል ተስፋ የተቆረጠበት ፣ ሞቶ የሚኖር ሕዝብ እረኛ የሌለው ሕዝብ ነው ። በነውርና በጭካኔ የሚወዳደር ሰብሳቢ ያጣ ሕዝብ ነው ። ያ ሕዝብ ክርስቶስ ሲያስተምረው የሚቆጡ ፣ በጭንቀት ሲወድቅ ግን የማያስቡለት መሪዎች ገጥመውት ነበር ። ስለዚህ ጌታ አዘነላቸው ። በሥጋም በነፍስም እረኛ ያጣ ሕዝብ ነበርና አለቀሰላቸው ። ይህ ርኅራኄውን ያሳያል ።
እረኛ ያጡ በጎች የመጡበትን አስታውሰው ለመመለስ አይችሉም ። በየተራራውና በየዋሻው ይመሽባቸዋል ። የአራዊትን ድምፅ ሲሰሙ የሞት ጥላ ይጫናቸዋል ። ስለዚህ ይፈራሉ ፣ ይጨነቃሉ ። ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጡበት ፍጥነት የሚመለሱት እረኛ ካጡ ነው ። እንደ እረኛ የሚያሰማራ ፣ ማልዶ የሚፈልግ ፣ ከፊት ቀደሞ የሚወጣ ፣ ለምለም መስክ ላይ የሚያሰማራ ፣ ከጥሩ ውኃ አጠገብ የሚመራ ፣ ሲመሽ የሚሰበስብ ፣ ሲቆስሉ የሚያክም ፣ ሲደክሙ የሚሸከም ፣ አደራ አለብኝ ብሎ በቅዱስ ፍርሃት የሚጠብቅ እረኛ ያስፈልጋል ።
አዎ እረኛ የለም ብሎ የበሸቀው ሕዝብ ከጌታ ቃል በኋላ በእረኝነት ወንበር ላይ በተቀመጡት እንዳይነሣሣ ጌታችን በመቀጠል ተናገረ፡- በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- መከሩስ ብዙ ነው ፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው ።” እረኛን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው ። ነገር ግን ምእመናን መጸለይ አለባቸው ። ሲጸልዩ እረኞች ይሰጡአቸዋል ። እረኞች ሲገኙም ምእመናን መጋቢና ተቆርቋሪ ያገኛሉና ከጭንቀትና ከተስፋ መቊረጥ ይድናሉ ።
ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ጸልዩ ካለ በኋላ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ላይ ወደዚህ ሕዝብ ላካቸው ። ጌታ ማንን ልላክ ? ሲል ነቢዩ ኢሳይያስ እኔን ላከኝ እንዳለ ደቀ መዛሙርቱም እንዲጸልዩ ከታዘዙ በኋላ ለአገልግሎት ተሰማሩ ። እግዚአብሔር ሰውን እንዲጠቁሙለት አይፈልግም ፣ አሟልተህ እኔን ላከኝ እንዲሉት ይፈልጋል ። ተግባር የሌለው ጸሎት አያርግምና ። የእኛን ድርሻ በቅጡ ከተወጣን እግዚአብሔር ማድረግ ያለበትን ያለ አሳሳቢ ያደርጋል ።
በአገራችን በኢትዮጵያ በቅርቡ በምንሰማው ጥናት ሃያ ሰባት በመቶ የሚሆን ሕዝብ በአእምሮ ጭንቀት የተያዘ ነው ። ይህ ማለት ከመቶ ሚሊየን ሕዝብ ሃያ ሰባት ሚሊየን ሕዝብ በጭንቀት ይሰቃያል ማለት ነው ። ይህ ወደ ሐኪም ቤት የሄደው ቊጥር ይመስላል ። ከዚህም ሊልቅ ይችላል ። የዚህ ችግር እረኞች መታጣታቸው ነው ። ሕዝቡ የተጣለ ነው ። ሲሞት እንኳ የሚጮህለት የለውም ። የሚሞተው ሰው እኮ ነገ ሠርቶ አሥራት የሚያመጣ መሆኑን አሥራት ሰብሳቢዎች እንኳ መረዳት አልቻሉም ። ብዙ ትዳሮች ይፈርሳሉ ። ሊያስታርቅ የሚደክም ግን እየጠፋ ነው ። ወጣቶች በአደንዛዥ ዕፅ ተይዘው ይሰቃያሉ ። ራርቶ የሚያክማቸው እረኛ ግን አላገኙም ። መጠጥ ቤቶች ሙሉ ናቸው ፣ ይህ ሁሉ ሕዝብ ግን ቀበጥ ስለሆነ ብቻ አይደለም ፤ ሰብሳቢ ስላጣም ነው ። ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡትን የቡድናችንና የጠባችን አባል እንጂ የክርስቶስ ወገን አላደረግናቸውም ። በእያንዳንዱ ቀን ሰው ይወድቃል ፤ ይህ ሁሉ እኛ ወንጌልን ስላላስተማርን ነው ብሎ ራሱን ያየ ግን እየጠፋ ነው ።
በዚያው መጠን ምእመናን መዳፈርና ሥልጣን ያላቸውን ማዋረድ እንጂ መጸለይ አልቻሉም ። የሚጸልይ ሲቀበል ፣ የሚሳደብ ግን ያንን የቀረውን ጥቂት ነገርም እያጣ ይመጣል ። ጌታ ግን ዛሬም ያዝናል ። በእኛ ልብ ሁኖ ለተጨነቀውና ለተጣለው ሕዝብ ማዘን ይፈልጋል ። ለሕዝቡ እንዘንለት ።
የዕለት መና /3/
ግንቦት 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ ተጻፈ በአዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ