ወዳጄ ሆይ
ይህች ዓለም ለስላሳ እባቦችና የሚያገሱ አንበሶች ያሉባት ዓለም ናት ። የእባብ ልስላሴ ያዘናጋል ፣ ቀጥሎ ግን ሞትን ይጋብዛል ። የአንበሳ ድምፅ ግን ያስደነግጣል ፣ ለመጠንቀቅም ግን ይረዳል ። ከእባብ ልስላሴ የአንበሳ ግሳት ይሻላል ። ጻድቅ የሚመስሉ ክፉዎችና ኀጥእ የሚመስሉ እውነተኞች በዓለም ላይ አሉ ። ጭምቶች ውስጣቸው ባቢሎን ነው ። አንገት ደፊዎች የማያውቁት ነገር የለም ። ዝምተኞች የተናገሩ ቀን ቃላቸው መራራ ነው ። ከአልችልም ባይነትና ከፍርሃት የምትላቀቀው ያለማቋረጥ በመለማመድ ብቻ ነው ። ዓለሙ ያንተ ነውና ሰይጣን ይፍራህ እንጂ አንተ ሰይጣንን አትፍራው ። ተጠሪነትህ ለኅሊናህ ከሆነ የምትፈራው ሕግ የለም ። በጎ መሥራት ራስን የማክበር ውጤት ነው ። እውነት መናገርም ሰሚን ማክበር ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ድራማ ከእውነቱ ኑሮ ይልቅ ቢያምርም ያልቃል ። ሐሰትና ሽንገላም ሁልጊዜ አያበላም ። ሳታስብ የምትናገረው ነገር እውነት ብቻ ነው ። ውሸት ድሪቶ በመሆኗ መልኳ ብዙ ነው ። መንፈሳዊነት አንገትን ሳይሆን ልብን በመስበር የሚገለጥ ነው ። በተሰበሩ አንገቶች ውስጥ የቆሙ ብዙ ልቦች እንዳሉ እግዚአብሔር ያውቃል ። ጉልበትን ሳይሆን ምኞትን ማሸብረክ እርሱ እውነተኛ አምልኮ ነው ። የላዩ የውስጡ መግለጫ ሲሆን እግዚአብሔር ይከብራል ፤ የላዩ የውስጡ መሸፈኛ ሲሆን እግዚአብሔር ያዝናል ።
ወዳጄ ሆይ
ከዋክብት በቀንም አሉ ፣ ብርሃኑ ግን አላወጣቸውም ። አጠገብህ ያሉትን እውነተኛ ሰዎች የምታውቃቸው የመከራ ምሽት ሲመጣ ነው ። አበቦችን በሌሊት አታያቸውም ፣ መልካቸውና ንግግራቸው ያማረም በመከራ ቀን አይገኙም ። ብቻውን ከሚበርር ባለ ክንፍ ፣ ብዙዎችን ተሸክሞ የሚያዘግም ሠረገላ ይሻላል ። ራስህን ለማኖር ብቻ ባለራእይ አትሁን ። ራስን ለማኖር ዓላማ ፣ ሰዎችን ለመርዳት ራእይ ያስፈልጋል ። ራስን ማኖር ስኬት ፣ ሰዎችን ማኖር ክብረት ነው ። ከራእይ እንጂ ከስኬት ደስታ አይገኝም ።
ወዳጄ ሆይ
ማግኘትህ ድሆች ወዳጆችህን አያስረሳህ ። ማወቅህም ያልተማሩትን ንቆ ከሊቃውንት መንደር አያውልህ ። ትልቁ ጥበብ እኔ የማስፈልገው የት ነው ብሎ ስፍራን መለየት ነው ። በቦታህ ዋና ያለ ቦታህ ትርፍ ነህ ። ያልሰከነ ውኃና እውቀት አይጠጣም ።
ወዳጄ ሆይ
ወደ እኔ ካልመጣ ብለህ የምትጠብቀውን ወዳጅህን እርሱ ካለበት ዘንድ ሂድ ። ወዳጅነትንና ትዳርን የሚያፈርስ መግደርደር ያለበት ፍቅር ፣ ፉክክር ያለበት ትጋት ነው ።
ወዳጄ ሆይ
ብርሃንን ስታይ እዚያ ቦታ ላይ ከጨለማ ጋር ከባድ ጦርነት እንደተደረገ አስተውል ። እውነትን በነጻ ስታገኝም ውድ ዋጋ የከፈሉ ስላሉ ነው ። ጨለማ
ስታይ ያንተን ጥቂት ጥረት የሚጠብቅ ጉዳይ እንዳለ አስተውል ። በቁራጭ ሻማም ጨለማን መዋጋት ይቻላል ።
ስታይ ያንተን ጥቂት ጥረት የሚጠብቅ ጉዳይ እንዳለ አስተውል ። በቁራጭ ሻማም ጨለማን መዋጋት ይቻላል ።
ወዳጄ ሆይ
ማግኘትህን የሚወድ ሌባ ብቻ ነው ይባላል ፤ ይሰርቅሃልና ። ማግኘት ብዙ ጠላት ያስነሣል ። አላዋቂዎችም ስታውቅ እብድ ነው ብለው የሕሊና ስደተኛ ያደርጉሃል ። ድንቁርና ግዛት ነውና እውቀት እንዳይደፍረው ይታገላል ።
ወዳጄ ሆይ
እውቀትህ የሚያስታብይህ ከሆነ ሁለት ነገር ጎድሎታል ማለት ነው ፤ እርሱም ማነስና ፍቅር ። ያልሞላ ገንቦ ይንቦጫቦጫል ፣ የሞላ ግን ድምፅ አያሰማም ። በኪስ ውስጥ የሚጮኸው ሳንቲም ነው ፣ ዋጋው ከፍ ያለ የገንዘብ ኖት ግን ፀጥ ይላል ።
ምክር 15
ዲአመ ሚያዝያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም.