የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጾመ እግዚእ /2/

ጾመ እግዚእ /2/
“ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት ከዮርዳኖስ ተመለሰ ፥ በመንፈስም ወደ ምድረ በዳ ተመርቶ ፥ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ ። በነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም ፥ ከተጨረሱም በኋላ ተራበ ።” /ሉቃ. 4፡1-2/ ።
ጌታችን በዮርዳኖስ የባሕርይ አባቱንና የባሕርይ ሕይወቱን የመንፈስ ቅዱስን ምስክርነት ከተቀበለ በኋላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ ። እንኳን ተለዋዋጭ የሆነውን የሰውን ምስክርነት ይቅርና የእግዚአብሔርን ምስክርነት ብናገኝም በጾምና በጸሎት መሰወር እንደሚገባ ሊያስተምረን ነው ። መሰወር ብቻውን ጠቃሚ አይደለም ፣ በጾምና በጸሎት መሰወር ይገባል ። በሩቅ ምሥራቅ ልማድ ጽሞና የሚያደርጉ ሰዎች አሉ ። መንፈሳዊ ጽሞና ግን ቃሉን በማንበብ ፣ በጾምና በጸሎት የሚደረግ ነው ። ጌታችን በመንፈስ ተመርቶ ወደ ምድረ በዳ እንደ ሄደ ይናገራል ። መንፈሳዊ ምሪት ለአንድ ምእመን በጣም አስፈላጊ ነው ። ሰው እግዚአብሔር ካልመራው ስሜቱ አሊያም ዘመኑ ይመራዋል ። ማንኛውንም መልካም ነገር ስናደርግ እያደረግሁ ያለሁት ከእግዚአብሔር ጋር ነው ወይስ ከእኔ ጋር ነው ? ብለን መጠየቅ ይገባናል ። ምክንያም ያለ እግዚአብሔር መሰብሰብ ለመበተን ነውና ።
ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾሙ ብዙ ነገሮችን ያስታውሰናል ። የመጀመሪያው ጾም ከአምልኮ አንዱ ክፍል እንደሆነ እንረዳለን ። ጌታችን በተራራው ስብከቱ በማቴዎስ ስድስት ላይ ስለ ጾም አስፈላጊነት አላስተማረም። ስለተቀደሰው ጾም አስተማረ እንጂ ። ጾም ጥያቄ የሌለው መንፈሳዊ ትጥቅ ነው ። ሥር የሰደዱ ችግሮችም በጾምና በጸሎት እንደሚወገዱ ጌታችን ተናግሯል ። ማቴ. 17፡21 ። ራሱ አብነት ከሆነባቸው መንፈሳዊ ሁነቶች አንዱ ጾም ነው ። ጾም የሥጋና የነፍስ ጤንነት መጠበቂያ ነው ። የሰውን ዕድሜ ከሚያሳጥሩ ነገሮች አንዱ ምግብ ነው ። በመጠኑና በልኩ መመገብ ካልተቻለ ምግብ ዕድሜ ያሳጥራል ። ጾም ግን የሥጋንም ጤንነት ይጠብቃል ። በዛሬው ዘመን እግዚአብሔር የለሾች ሳይቀር በሳይንሳዊ እውቀት ተመርተው እየጾሙ ነው ። እኛ ግን ከሥጋዊ ዓላማ ነጻ ሁነን የእግዚአብሔርን ፊት በጾምና በጸሎት እናስሳለን ።
አርባ ቀን በጌታችን አገልግሎት ላይ ትልቅ ትርጉም አለው ። ጌታችን አገልግሎቱን ሲጀምር አስቀድሞ አርባ ቀን በጾምና በጸሎት ነበረ ። ከትንሣኤ በኋላም ምድራዊ አገልግሎቱን ለመፈጸም አርባ ቀን እያስተማረ ቆይቷል ። የአገልግሎቱ መንደርደሪያና ማዘጋጃ አርባ ቀን ነበር ። የማዘጋጃና የማጠቃለያ ጊዜ ያስፈልጋል ። ሕይወትም አገልግሎትም ልክ እንደ መጽሐፍ ነው ። መጽሐፍ መግቢያና ማጠቃለያ እንዳለው ሕይወትና አገልግሎትም መግቢያና ማጠቃለያ ያስፈልገዋል ። አሊያ ከመሐል የጀመረ መሐል ላይ ያቆማል ። ሙሴ አርባ ቀን በደብረ ሲና ቆይቶ ሕገ ኦሪትን ተቀብሏል ። ጌታችንም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ የመንግሥቱን ወንጌል ሰብኳል ።
በዲያብሎስ ተፈተነ ይላል ። ይህ አዳምን ያስታውሰናል ። ጌታችን ዳግማዊ አዳም ሁኖ መምጣቱ ደም መላሽ ፣ ካሣ ከፋይ መሆኑን ያሳያል ። አዳም በዲያብሎስ ለአንድ ጊዜ ተፈትኖ ለ5500 ዓመታት ወድቋል ። ጌታችን ግን አርባ ቀን ተፈትኖ ድል ነሥቷል ። አዳም በገነት ጌታችን በምድረ በዳ ተፈተኑ ። አዳም በትዕቢት ወደቀ ። ጌታችን በትሕትና አሸነፈ ።
የጾም አንዱ ዓላማ በትሑት ሰብእና በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ነው ። ጌታችን ተራበ ተብሎ ተነግሮለታል ። የሚራብ ሥጋ መዋሐዱን ለመግለጥ ነው ። ዳግመኛም የረሀብተኞችን ረሀብ ማየቱን ለማስረዳት ነው ። ጾምም የተውነውን ምግብ ለረሀብተኞች የምንሰጥበት እንጂ የቁጠባ ባሕል የምናዳብርበት አይደለም ። ለቁርስ የምናወጣውን ደምረን ምጽዋት መስጠት በግድ ይገባናል ። አሊያ ጾሙ የረሀብ አድማ ይሆንብናል ።
ወርሃ ጾሙ አንደበታችንን ክፉ ከመናገር ፣ ጆሮአችንን ክፉ ከመስማት ከልክለን የምንጾምበትና ምሕረት የምንቀበልበት ያድርግልን ።

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ