የትምህርቱ ርዕስ | ፈቃድህ ይሁን

“የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን ።” የሐዋ. 21፡14 ።
ጌታ ሆይ የምወደው ያለ ችግር እንዲሆን መመኘቴ በእውነት ከንቱ ነው ። ወፍጮ ቤት ገብቶ ዱቄት ሳይነካው የሚወጣ ፣ በዚህ ዓለም ኑሮ መከራ ሳያገኘው የማያልፍ ማነው ? እኔ ግን የእኔ የምለው ሁሉ ያለ መከራ እንዲኖር እፈልጋለሁ ። ጌታዬ ሆይ መምከር እንጂ ማስገደድ በማልችልበት ዓለም ከጸሎት ጋር መምከርን ስጠኝ ። እኔ በቃል ብመክር አንተ ግን በሕይወት እያሳለፍህ መምከር የምትችል መምህር ነህና ላንተ ስፍራ መልቀቅን አስተምረኝ ። የሰው ልጅ በመጀመሪያ ምርጫው የኋላ ውጤቱ ይታወቃልና የማውቀው ነገር ፍርሃት እንዳይሆንብኝ ፣ የእኔ ለምላቸውም መምረጥ ባለመቻሌ እንዳላዝን እባክህ አስተምረኝ ። ያልከው አይቀርምና መጨነቄ ፣ ሊሆን ያለው ይሆናልና መባዘኔ ከንቱ ነው ። ሁሉን ላንተ ሰጥቶ ማረፍ ይሁንልኝ ። ልመልሰው ያቃተኝን ፣ ልይዘው ስል ያመለጠኝን ሁሉ ፈቃድህ ይሁን ብዬ እንዳርፍበት እለምንሃለሁ ። ስለ ልጆቼ ፣ ስለ ትዳሬ ፣ ስለ አገልጋዮቼ ፈቃድህ ይሁን ማለትን አስተምረኝ ። ፈቃዴ ፈቃድህን ላይለውጠው ፣ መሻቴ ሰውን ከመንገዱ ላይመልሰው እንዲሁ መዋተትን ከእኔ አርቅ ። አገልጋዮቼ የተፈጠሩት ላንተ እንጂ ለእኔ አይደለም ፣ የእኔ በምላቸውም ላይ ፣ እኔ ካለኝ ዓላማ አንተ ያለህ ዓላማ ይበልጣል ። እኮ ጌታ ሆይ ፈቃድህ ይሁን ብዬ ማረፍን ስጠኝ ።
መንገድ ዘግቼ የሚዘለውን ፣ በር ቆልፌ ሰብሮ የሚወጣውን ፣ እየለመንሁ የማይመለሰውን ነገር ፈቃድህ ይሁን ብሎ መተውን አስተምረኝ ። የእኔ መሻት ይህ ነው ፤ የሚሆነው ግን ተቃራኒ ነው በምልበት ሰዓት ፈቃድህ ይሁን ማለትን አስተምረኝ ። በበጎ አሳብ እንዳልቀጣ ፣ መራራትም ግርፋት እንዳይሆንብኝ ፈቃድህን ካላከበረ ፍቅር አድነኝ ። ሰው ቢኖር የእኔ ነው ብል እንኳ ቢሞት ግን ያንተ ብቻ ነው ። ቢኖርም ቢሞትም ላንተ ነውና ስለ ሰው አንተን እንዳልከስህ ፣ ስለ ወዳጆቼ ለምን ነካህብኝ እንዳልልህ እርዳኝ ። የሆነውን ነገር ብቻ ሳይሆን የሚሆነውንም እንድቀበል ፣ መገረሜ ባንተ ብቻ እንዲሆን እለምንሃለሁ ። ብቻ ጌታ ሆይ የአቅሜን ሞክሬ አፈትልኮ ሲወጣ ፈቃድህ ይሁን ማለትን አስተምረኝ ። እኔ ምድርን እያየሁ ስከላከል ፣ አንተ ሰማይን ባየህለት ሰው ፈቃድህ ይሁን ማለትን አስተምረኝ ። ምንም ነገር ጥያቄ እንዳይሆንብኝ አንተ ሰው ሁነሃል ። ሰው እስከ መሆን ፍቅር ዝቅ ካደረገህ ለሰው የምታደርገው ሁሉ በጎ ነው ። እባክህን የጌታ ፈቃድ ይሁን ብሎ ዝም ማለትን አስተምረኝ ።
ስረታ ፈቃዱ ይሁን እላለሁ ። ነገር ግን አስተያየትና ወሬ አበዛለሁ እንጂ ዝም ማለት አልችልምና ፈቃድህ ይሁን ብሎ በልብ ማረፍን ፣ በአንደበት ዝም ማለትን አስተምረኝ ። የደጎች ዕድሜ ማጠር ፣ የመልካሞች ዘመን አጭር መሆን ግራ ሲያጋባኝ ፣ እንደምፈልገው ቀርቶ ነገሮች እንደታሰበላቸው ሲጓዙ ፈቃድህ ይሁን ብሎ ዝም ማለትን ፣ አንተን አለማማትን አድለኝ ። ኃይሌ የሚባክነው በንግግሬ ነውና ዝም ማለትን አስተምረኝ ። ጥያቄዬ የሚበዛው “ለምን ?” በማለት ነውና ፈቃድህ ይሁን ማለትን አለማምደኝ ። ጣዕም ባለው ስምህ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለሙ አሜን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም