“ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ።” ዮሐ. 14፡1
ባንተ ካላመንሁ በራሴና በታላላቆች አምናለሁ ። ይህ ሁሉ ግን የሚያረገርግ መሠረት ፣ የሚነቃነቅ ምሰሶ ፣ የሚያፈስስ ጉልላት ፣ የማይጨበጥ ጉም ነው።ባንተ በወልደ እግዚአብሔር ደግሞም በባሕርይ አባትህና በባሕርይ ሕይወትህ እንዳምን እርዳኝ ። ጌታዬን ባጣውስ እያልሁ ልቤ ሲታወክ ፣ ወዳጄ ባይኖርስ እያልሁ ውስጤ ሲሰጋ ፣ ልጆቼ ቢበታተኑስ እያልሁ አቅሌን ስስት ፣ አገሬ ቢተራመስስ እያልሁ በፍርሃት ስናጥ እባክህን ባንተ ማመንን አስተምረኝ ። ሞትን እንጂ ትንሣኤን ማሰብ ሲቃተኝ ፣ አብሮ እራት የበላውን ይሁዳን በማሰብ ስጨነቅ ፣ ፎክሬ ባልገኝስ ብዬ ጴጥሮስነቴን ስጠራጠር እባክህ ባንተ እንዳምን እርዳኝ ። የያዝሁት ለነገ አይበቃም ብዬ ገና ላልመጣ ቀን ስወጠር፣ ብታመምስ ብዬ ባልመጣ በሽታ ሳቃስት እባክህን ባንተ እንዳምን እርዳኝ ። ልቤ እንደ ባሕር አልረጋ እያለ ሲታወክ ፣ ክፉ ቀኖች እንደ ማዕበል ሲንጡኝ ፣ የያዝሁትን ለመንጠቅ ሁሉም ሲሟገቱኝ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የነፍሴ መልሕቅ ሁነኝ ። ባንተ ማመን የሚያዩትን አለማመን ነው ። ባንተ ማመን ትንሣኤን ማሰብ ነው ። ባንተ ማመን የዘላለም ፍቅርን መዘመር ነው ። እባክህ ባንተ እንዳምን እርዳኝ ፣ ያን ጊዜ የልቤ ማዕበል ይገሠጻል ። በጸናው ስምህ ለዘላለሙ አሜን ።