የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ሥራ

“እንግዲህ፡- የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ? አሉት” ዮሐ. 6 ፡ 28 ።
ጌታችን ከንቱ ፍላጎታቸውን ገሥጾ ወደ እውነተኛውና ዘላለማዊው መንገድ ሲያመለክታቸው የጠየቁት ጥያቄ ነው ። ጌታችን ለማይጠፋው መብል ፣ ለዘላለም ሕይወት ፣ እግዚአብሔር ለሚሰጠው ለእርሱ ሥሩ ስላላቸው ይህን ጥያቄ አቀረቡ ። መድከም የሚገባው ፣ ማሰስም የሚገባው ለማይጠፋው ሲሆን እርሱም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ።
“ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው ።” ቊ. 29
ከተበተነው የሥጋ አሳብ አንድ ወደሆነው የመንፈስ አሳብ እየመጡ ይመስላል ። ነገር ግን ምኞትን በምኞት ፣ ጥያቄን በጥያቄ ለመመከት እየጣሩ እንደሆነ መገመት ይቻላል ። ምኞት የሚጋልበው ሰው ከምኞቱ ውጭ ማየት አይችልም ። ልቡ የቆመ ፣ የቆመ ነገር አያይም ። አሁን የመጣውን የአደባባይ ግሣጼ ለማለፍ ብቻ ያሰቡ ይመስላል ። በክርክር እንጂ በሕይወት የበላይ የመሆን አሳብ የላቸውም ። መንፈሳውያን ሳይሆኑ ፖለቲከኛ ይመስላሉ ። በክርክር የበላይ ሁኖ በሕይወት የበታች መሆን ከባድ ውድቀት ነው ። አንድ በጎጃም የሚኖሩ የልጅ ልጃቸውን የሚያሳድጉ አያት “ልጅቱ የት ሄደች ?” ሲሏቸው “ላይበራሪ ትላለች ፣ እንደማያት ግን ታችበራሪ ሁናለች” አሉ ይባላል ። እነዚህ ሰዎች የበላይ ለመሆንና ላለመረታት ብቻ ይናገራሉ ። ልባቸውና አፋቸው ፣ ምኞታቸውና ተግባራቸው ተለያይቷል ።
ጌታችን ጥርት ባለ ቋንቋ፡- ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና ።”ብሏቸዋል ። ጌታችን እየተናገረ ያለው ፡-
1-  ስለሚጠፋው መብል ብቻ ሳይሆን ስለማያልፈው ሕይወት አስቡ ።
2-  የዘላለም ሕይወት የወልድ ስጦታ ነው ። የመጣሁት መንግሥትን ሳይሆን ሕይወትን ልሰጣችሁ ነው ፣ ሕይወት የሌለበት መንግሥነት ከንቱ ነው ።
3-  የዘላለም ሕይወት በእግዚአብሔር ስጦታና በሰው ፍላጎት የሚገኝ ነው ። ያ ባይሆንማ ለጌታ የቀረበው ይሁዳ ፣ ለጳውሎስ የቀረበው ዴማስ ከዘላለም ሕይወት አይወጡም ነበር ።
ለዚህ አዋጁ እነርሱ መልስ ያገኙ መስሏቸው፡- እንግዲህ፡- የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ ምን እናድርግ ? አሉት ።” እነዚህ ሰዎች በድርጊት ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት መፈጸም ፈልገዋል ።ልብ የሌለበት ብዙ ድርጊት አለ ። እግዚአብሔር ግን የሚፈልገው ከልብ የሚነሣ ፣ ከመዳን የሚጀምረውን መልካምነት ነው ። የክርስትና እምነት በአንድ አምላክ ማመን ነው ሲባል እንደ አይሁድ በአንድ ገጽ ማመን ማለት አይደለም ። በሦስት አካላት ማመን ነው ስንል እንደ አሕዛብ ብዙ አማልክት ማለት አይደለም ። በአንድ አምላክ ብቻ ሳይሆን በአንድ አዳኝ ማመን ነው።በዙፋኑ ባለው ብቻ ሳይሆን በቀራንዮ በተሰቀለው አምላክ ማመን ነው ። እነዚህ ሰዎች ይህ ሁሉ እምነት በሌለበት ድርጊት ፣ ልብ የሌለበት ሥራ ማቅረብ እንችላለን አሉ ። ከባዱ መሥራት ሳይሆን ማመን ነው ። መሥራት አቅምን ፣ ማመን ሕይወትን መስጠት ነውና ። ጌታ ሥሩ ሲላቸው ጣሩ ማለት አልነበረም ። በሥራ ውስጥ ምኞት ፣ ዓላማ ፣ ጊዜ … አለ ። እንዲሁም የማያልፈውን ለማግኘት ምኞት ፣ ዓላማ ፣ ጊዜ ይኑራችሁ እያለ ነው ።
“ኢየሱስ መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው አላቸው ።” ቊ. 29 ።
እግዚአብሔር አብ ላኪ ፣ ወልድ ተላኪ ነው ። እግዚአብሔር አብ ልብ ነውና ቃሉን ይልካል ፣ ወልድም ቃል ነውና ለልብ ይላካል ። ላኪው የሦስቱ አካላት ልብ ነውና አንድ ፈቃድ ነው ። ተላኪው የሦስቱ አካላት ቃል ነውና አንድ መለኮታዊ ግብር ነው ። የላከው ፍረድ ፣ ቅጣ ብሎ ሳይሆን አድን ብሎ ነው ። በአብ ስምረት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ጌታ መጥቷልና አንድ አዳኝ ይባላል ። ወልድ በተለየ አካሉ ፣ በተለየ ግብሩ ፣ ሥጋ ለብሷልና ሥላሴ ሰው ሆኑ አንልም ። በመለኮት ሞተ ሳይሆን በሥጋ ሞተ የምንለውም ሥላሴ ሞቱ እንዳንል ነው ። ሥጋ መልበስና መሞት ለወልድ የራሱ ግብር ሲሆን ማዳን ግን አንድ ነውና የመለኮት ግብር ነው ። ስለዚህ በወልድ ቤዛነት ሥላሴ አዳኝ ይባላሉ ።
ጌታችን ሥራ ያለው ጥረትን አይደለም ። በጎ ምግባርም አያስፈልግም ማለት አይደለም ። ሥራ ያለው በወልድ ማመንን ነው ። የላከ አብን ፣ የተላከ ወልድን ፣ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ማመን ሥላሴን ማመን ነው ። መዳናችንን ሥላሴያዊ ማድረግ መጽሐፋዊ ምክንያት ነው ። አንዳንድ ሰዎች ሥላሴ በምስጋና አንድ መሆናቸውን ይዘነጉና እግዚአብሔር የሚለውን ምስጋና ሁሉ ኢየሱስ ብለው ይተካሉ ። ይህ አካሄድ ወደ አንድ ገጽ ትምህርት ወደ ሰባልዮስ ባሕል እንዳይወስደን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ጌታችን መዳንን በተናገረበት አንቀጽ ሁሉ አባቱን የሚያነሣው ከዚህ ስህተት ሊጠብቀን ነው ።
የላከ አብ ማኅየዊ ነው ፣ የተላከ ወልድም ማኅየዊ ነው ፣ መንፈስ ቅዱስም ማኅየዊ /አዳኝ/ ነው ብሎ ማመን እርሱ የዘላለም ሕይወት ነው ። እግዚአብሔር ከሰዎች የጠበቀው ትልቁ ነገር ይህ ነው ። በላከው ማመን ማለት በተላከው ማመን ነው ። በላከው ማመን ማለት በላከውና በተላከው መካከል ያልተቋረጠ ግንኙነት አለ ብሎ ማመን ነው ። የሠራልንን ስናውቅ ለመሥራት አቅም ይኖረናል ። ከአሌፍ በፊት ፊደል እንደሌለ ከእምነት በፊት ምግባር የለም ። ሕንፃ በመሠረቱ ላይ እንዲያርፍ ምግባርም በሃይማኖት ላይ ይመሠረታል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ