የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰው እንዳንተ ነው

ዛሬ ላይ ቁሞ ትላንትን በትዝታ ፣ ነገን በስጋት የሚኖር ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። ዛሬን ለመኖር የማይደፍር ፣ በሰንጣቃ ዓለት እንዳለ በትላንትናና በነገ መካከል የሚተክዝ ነው ። ሰው ማለት እንደ አንተ ነው ። እውነቴን ነው ፣ የቅዱሳን አምላክ ምስክሬ ነው ፤ የተሰማህን ያ ሰው ተሰምቶታል ፣ ያመመህ ሕመም እዚያ ሰውዬ ጋ እየጀመረ ነው ። ሰው ማለት እንደ አንተ ነውና ኅሊናው ሳይወቀስ አይቀርም ። ክፋት ሲያበዛ ፣ በበደል ላይ በደል ሲጨምር ፣ ዝምታህን ሰብሮ ክፉ ሊያናግርህ ሲሻ ውስጡ እየተሰቃየ ነው ፣ ባንተ ስህተት ውስጥ ለመደበቅና እፎይታ ለማግኘት እየፈለገ ነው ። አንተም ብትሆን እየበደልካቸው ዝም ሲሉህ ያምሃልና ። በጣም ክፉ ስትሆን የሚተፋህ ፣ በጣም ደግ ስትሆን ሰስቶ የሚርቅህ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። እንደ አንተም ስለሆነ መሸነፍን የማይፈልግ ይቅርታ ማለትን እንደ ተራራ የሚያይ ነው ። ሰው ማለት እንደ አንተ ነው ፣ ሲያጠፋ ትክክል የነበረ ትንሽ ቆይቶ ግን ኅሊናው የሚቆስልበት ነው ። ሰው እኮ እንደ አንተ ነው ፣ እየራበው በልቻለሁ የሚልህ ፣ ተበድሮ ድግስ የሚደግስልህ ባለ ይሉኝታ ነው ። ሰው ማለት እንደ አንተ ነው ። መልካሙን ቀን ፣ የትላንትን ጥሩ ጊዜ መመለስ ቢያቅተው እውቅና እንኳ ለመስጠት ረጋ ያላለ ነው ። አዎ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። ቀስት ሁሉ ወደ እርሱ የተነጣጠረ የሚመስለው ፣ አማርኛ የሚቆረጥመው ፣ ፀጉር የሚሰነጥቀው ፣ “እንዲህ ያለው ምን ለማለት ፈልጎ ነው ?” የሚለው ሰው እንዳንተ ነው ። 
 
አንተ እርሱን ትፈራዋለህ ፣ እርሱ አንተን ይፈራሃል ፤ በግልጽ ያላወራችሁ መንጋ ፈሪዎች ናችሁ ። ምክንያቱም ሰው ማለት እንዳንተ ነውና ። በጠጅ ጀምሮ በቅራሪ የሚጨርስ ፣ በጉዳትህ በአንድ ዓይኑ እያለቀሰ በአንድ ዓይኑ የሚስቅ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። ሬሳ አስቀምጦ የሚስቅ ፣ ሲደነግጥ “ጥርስ ባዳ ነው” የሚል ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። ትላንት ስንዴ ዘርቶ ስንዴ ያጭድ ነበር ፣ ዛሬ ገብስ ቀጥሎም እንክርዳድ በማጨዱ ግራ የተጋባ ፣ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። ፊትህን እያየ ጀርባህን የሚያጠና ፣ ሳሎን አስቀምጠኸው ጓዳ የሚገባ ፣ ለነገ አስበኸው ማምሻ የማይገኝ ፣ ለዓመት ሰፍረኸው ለዕለት የሚያልቅ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። በከመርከው ቊጥር የሚወርድ “የተልባ ስፍር” ሰው ማለት እንዳንተ ነው ፣ መንሸራተት የማይደክመው ።
አዎ አምላከ አበው ምስክሬ ነው ፣ ሰው ማለት ልክ እንዳንተ ነው ። ራስህን ፊት ለፊትህ ማየት ስላቃተህ እንጂ ያ ሰው ማለት አንተ ነህ ። አንተ ማለትም ያ ሰው ነህ ። ስልክህ ተጠልፎ ሲያስተጋባ የገዛ ድምፅህን መስማት እንደሚያስደነግጥህ ሁሉ ፣ የሰውዬውን ድምፅ ስትሰማ የደነገጥኸው ራስህን ስለሰማኸው ነው ። ሰውዬው ያደረገው አንተ የምታደርገውን ነው ። ዛሬ ባታደርገው ነገ የምታደርገውን ነው ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ እነዚያ የወደቁትን ትወድቀዋለህ ፣ እነዚያ የወጡትን ትወጣዋለህ ። ምናልባት በዚያ ሰውዬና ባንተ መካከል ያለው ልዩነት እርሱ በመናገሩ አንተ ዝም በማለትህ ነው ። የሁለታችሁም ኅሊና ግን ያው አረም ያለበት ማሳ ነው ። ጠዋት ስትነሣ ያለው ማንነትህ ቀን ላይ እንደ ገጠመህ የቆሸሸ ሰውዬ ነው ። ሰውዬው ዋለበት አንተ አረፈድክበት እንጂ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። የአንድ ቀን ውኃ ሲያጣ ራሱን መቀበል የሚያቅተው ማንነት የተሸከምህ ነህ ። በውስጥህ የሚበቅሉት ነገሮች ከደጅ የመጡ አይደሉም። ጊዜ የገለጣቸው አዳማዊነትህ ነው ። ሰው ማለት እንዳንተ ነው ራራ ። ሰው ማለት እንዳንተ ነውና አትደንብር ።
ከተወለድክበት ጊዜ ጀምሮ እየሞትህ ነው ። ጥርስህ ይሰበራል ፣ ድድህ ይደማል። ሲቆይ እግርህ ያነክሳል ፣ ጨጋራህ ያጓራል … ። አንተ አካሉ በሸተተው በሽተኛ ለመደነቅ መልአክ አይደለህም ። ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። እርሱ እንዳንተ ያስብ ነበር ። ዳሩ መሐል ሁኖ ነካው  ። ሩቅ ያዩት ሩቅ አይቀርምና ይኸው ሲይዘው ከበደው ። “እንዴት ያማርራል ?” ባለበት ነገር ይኸው የበለጠ እያለቀሰ ነው ። ሰው ሲታበይ እግዚአብሔር ይስቃል ። ጠዋት ጠግበሃል እንደገና ምግብ የሚያምርህ እስከማይመስልህ ተንገፍግፈሃል ። ሆድ ግን እጅግ ከሃዲ ነውና ይኸው ምሳ ላይ ርቦሃል ። ከበሽታ ብትድን ፣ ከድህነት ብታመልጥ ለመጨረሻ ጊዜ አይደለምና ተጠንቀቅ ። እዚያ ማዶ የምታየው ሰው እንዳንተ ነበረ ። ይህችን ከሃዲ ዓለም አትመናት ።   
አንተ ድራማውን በመቻልህ በድብቅ በማድረግህ ፣ እርሱ አላውቅበት ብሎ በግልጽ በማድረጉ እንጂ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። አዎ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ልቡን አስቀምጦ በአፉ የሚያወራህ ፣ እንዳላስቀይመው ብሎ የሚዋሽህ ፣ በአሳቡ ሂዶ በድኑን ያስታቀፈህ ሰው ማለት እንዳንተ ነው ። አንተን የሚፈትንህ የኃጢአት ስሜት እርሱንም ይፈትነዋል ። አንተ በወደቅህበት ብዙ ጊዜ ወድቋል። መዐርጉ ፣ ያለበት ሥልጣን ሳይረዳው ሰው በጣም ይደክማል ። ምክንያቱም ሰው እንዳንተ ነው ። ሰው እንዳንተ ነውና አትፍራው ። ሰው እንዳንተ ነውና አክብረው ። እግዚአብሔር ግን እንዳንተ አይደለምና ፍራው፡፡      
      
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ