የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድብቅ በረከት አለው

ድብቅ በረከት አለው
“ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ሊፈትነው ይህን ተናገረ።”  /ዮሐ. 6፥6/ ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፊልጶስን፡- “እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ?” በማለት ጠይቆታል ። ከተራራው ግርጌ ያሉትና ወደ እርሱ እየተመሙ የሚመጡትን ሕዝብ ጌታ እያየ የተናገረው ነው ። ሳያዩት የሚያይ ፣ ሳይሰሙት የሚሰማ ፣ ለእያንዳንዱ ሰው እቅድ ያለው አምላክ ነው። ጌታ አስቦ እንዲያስብላቸው ፣ አዝኖ እንዲያዝንላቸው ፊልጶስን እየቀሰቀሰው ነው ። ወዳጅ የሚሰጠን ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር ነው ። አባት የሚሰጠን አባትነት የሚሰየምበት እርሱ አማኑኤል ነው ። ጌታ እርሱ ብቻ አስቦ መቅረት አልወደደም ፣ ፊልጶስም እንዲያስብ ቀሰቀሰው ። የምንወዳቸውን ሰዎች ውደዷቸው ተብለን በጌታ ታዝዘን ነው ። የሚወዱንም የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው ። በርግጠም ፊልጶስ የእርሱ የጌታው ደቀ መዝሙር ነው ። እነዚህን ሁሉ ሕዝብ የመመገብ ግዴታ የለብንም አላለውም። ማስላት ጀመረ ። እግዚአብሔር ርኅሩኅ ልብ ይወዳል ። ሰው በልቡ ሲራራ እግዚአብሔር ተአምራትን ያደርጋል ። ቀና ልብ ሲኖረን እምነትን እናገኛለን ፣ እምነትም ተአምራትን ያለማምደናል ። የቀድሞው ሳኦል የኋላው ጳውሎስ ተግባሩ ክፉ ነበረ ፣ ልቡ ግን ቀና ነበረ ። ምንም ይሁን በእውነት አምላክን የሚፈልጉ ፣ ለአምላክም የሚቀኑ ወደ እውነቱ መድረሳቸው አይቀርም ። እግዚአብሔር በራድ ከሆኑ ሃይማኖተኞች ይልቅ ትኩስ የሆኑትን ቀናተኞች ከሁሉ ስፍራ ለመንግሥቱ ይሰበስባል ። እኛ የሚሰሙንን ብቻ እንወዳለን ፣ የሚቃወሙን ምናልባት እውነትን የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ ።

ለማናውቃቸውና ለሚበዙት ሕዝብ ያለንን አመለካከት እግዚአብሔር ያያል ። የእኔ በምንላቸው አጥር ውስጥ ብቻ መሆናችንን አይወደውም ። እግዚአብሔር ለፈጠረው ሰው በሙሉ አዘኔታ እንዲኖረን ይፈልጋል ። ከአምስት ጣት የትኛው ይበልጣል ? እናት ዘጠኝ ወልዳ ለማን ታዳላለች ? እግዚአብሔር ፍጥረቱን በእኩል ዓይን የሚያይ አምላክ ነው ። የእግዚአብሔር ዓይን ያስፈልገናል ። ጌታችን ወደ ተራራው እየወጡ ያሉቱን ወገኖች ውስጣቸውን እንዳየ እርግጠኛ ነን ። እርሱ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ነውና ። በበሽታ እንደ ዛሉ ፣ ራብ እንዳጠቃቸው ፣ ተስፋቸው እንደላላባቸው ፣ ወዴት ልሂድ ብለው ግራ እንደ ገባቸው እያየ ነው ። የቸርነቱንና የፍቅሩን ሥራ ሊሠራላቸው ፈለገ ። እርሱ ብቻ የልብ አዋቂ ነው ። የልባችንን እርሱ ብቻ በማወቁም ልናመሰግን ይገባናል ። በሰላም የምንኖረው የልባችንን ስለማንተዋወቅ ነው ። እግዚአብሔር ገና ያልታጨደውን አሳባችንን ከልባችን ማሳ ላይ ያየዋል ። ገና ያልተወቃውን ምኞታችንን ከነፍሳችን ውድማ ላይ ያየዋል ። ገና እንክርዳድና ገለባው ያልተለየውን ማንነታችንን ያየዋል ። እንደ ገለባ የምንቀልበት ፣ እንደ እንክርዳድ የምናሰክርበት አሳባችንን ፣ ልብ በሚባል ጽኑ በር ስለቆለፈልን ስሙ የተመሰገነ ይሁን ።
ዛሬም እየመጣ ያለው ሕዝብ በነፍስ በሥጋ የዛለ ሕዝብ ነው ። የነፍሱ አለማረፍ ሥጋውን እያዛለበትም ነው ። ይህ ሁሉ የሚጮኸው ወገን ተጨንቆ ነው ። እነ ማይክል ጃክሰን ሲዘፍኑ ብዙ ሰው የሚወድቀው ድምፅና የሙዚቃ ስልት አብሮ ስለሚጨመር ነው ። ድምፅ ከባድና ለመቋቋም አቅም ይጠይቃል ። በድምፅ ጥበብ ሰውን የሚያስጮኹ አሉ ፣ ይህ ስልት እንጂ እምነት አይደለም ። ጌታ እንዴት ላሳርፈው የሚለውን ሕዝብ እኛ እንዴት ላውከው ካልን አስቸጋሪ ነው ። እየመጣ ያለው ሕዝብ ጥላቻን አይደለም ከባድ ድምፅም መቋቋም የማይችል ፣ ምስጥ እንደ በላው ዛፍ ተገዝግዞ የቆመ ነው ። ልንራራለት ይገባል።
እግዚአብሔር በተአምራቱ የሚያስደንቅ አምላክ ነው ። ፊልጶስን ሊያስገርመው ፈልጓል ። እርሱ በምድረ በዳ ላይ ማዕድን ማሰናዳት የሚችል አምላክ ነው ። ጌታ ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበር ። ብቻውን ሊያደርግ ያለውን ፊልጶስ አላወቀም ነበር ። ጌታ ሳምራዊቷን ሴት ሲያናግር ምግብ እንዲገዙ ልኳቸው ነበር ። ዛሬ ግን ምግብ እንዲገዙ አይልካቸውም ። በጥንት ዘመን የተደረገውን ሊደግምላቸውና ሕያውነቱን ሊያረጋግጥላቸው ይፈልጋል። እርሱ ተአምራቱን የሚያደርገው እኛን ለመርዳት እንጂ ችሎታውን ለማሳየት አይደለም ። እግዚአብሔር በክብሩ ስጋት የለበትምና ። የሚያደርገውን ያውቃልና አይታወክም ። የትኛውም ስፍራና ጊዜ ምቹ ባይሆንም እርሱ መሥራት ይችላል ። ከጊዜና ከቦታ ክልል ውጭ ነው ። ምቹ ቦታ አያግዘውም ፣ መጥፎ ጊዜም አይመልሰውም ። እግዚአብሔር ሲባል ከሦስት ተጽእኖዎች ያለፈ ነው ። ከቦታ ፣ ከጊዜና ከሁኔታ ።
የምናደርገውን አውቀን መፈተን በጣም ደስ የሚል ነገር ነው ። የሰውዬውን ምላሽ መስማት በጣም የሚያጓጓ ነው ። በዘመናዊው ዓለም ሰርፕራይዝ የሚባለው በደስታ ድርቅ የሚያደርግ ነው ። አይሆንም የሚባለውን ነገር ጨርሶ ጌታ ይጠይቀናል ። ምላሻችንን ሳንጨርስ መጋረጃውን ሲገልጠው ተስፋ የቆረጥንበት ጸሎት አካል ነሥቶ ፊት ለፊታችን ቆሟል ። በዚህ አስገራሚነቱ ብዙዎችን ሲያፍነከንክ የኖረው እግዚአብሔር ዛሬም ሕያው ነው ። የምናደርገውን አውቀን መፈተን በጣም የምንወደው ሰው ላይ የምንፈጽመው ነው ። ጌታ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን በፍቅር የሚሰጥ ነው ። ያለ ፍቅርም ሰጥቶ አያውቅም ። የጌታ ስጦታ በፍቅር የረጠበ ስጦታ ነው ። ተአምራት በእግዚአብሔር ችሎታና ፍቅር ብቻ የሚፈጸም ነው ። የእኛ እገዛ ካለበት ተአምራት መሆኑ ይቀራል ። እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ ነው ። ሌሊቱን ቀን ፣ ቀኑን ሌሊት የሚያደርገው ተአምራቱ በየቀኑ ለሰው ሁሉ የሚደረግ ነው ። ሲመሽና ሲነጋ ያለውን የጌታችንን ተአምራት ማድነቅ ካልቻልን በምንም መደነቅ አንችልም።
የሚያደርገውን የሚያውቀው ጌታ እየፈተነን ይሆን ? በእምነት ወይስ በስሌት እንደምንኖር እያየን ይሆን ? እየመጣ ላለው ሕዝብ ፣ እየመጣ ላለው ትውልድ ያለንን ልብ ማየት ይፈልጋል ። አቅሙ የእርሱ ነው ። አንዳንድ ጉዳዮች ፈተናዎች ሊሆኑ ይችላሉ ።
እግዚአብሔር በከፍታ ላይ የሚያስቀምጠን እየመጣ ያለውን ትውልድ ማየት እንድንችል እንጂ የድንጋይ ናዳ እንድንለቅበት አይደለም ። እየመጣ ያለውን ትውልድ በሚመለከት የተለያዩ ዝግጅቶች በተለያዩ ተቋማት ይደረጋሉ ። እየመጣ ያለውን ትውልድ እንደ በረከት እንጂ እንደ አደገኛ ክስተት ማየት በራሱ ችግር አለው ። እየመጣ ያለው ትውልድ የራሱን አገር ቋንቋ የማያውቅ ፣ ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ የሆነ ፣ ሁሉን ነገር በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጥ የሚፈልግ ፣ ራስ ተኮር የሆነ ፣ ጥያቄ የሚያበዛ ፣ ያለ አመክንዮ የማይቀበል ፣ እሺ ብሎ ተደልሎ የማያልፍ ፣ ገደቡን ሲነኩበት የማይወድ ፣ ስለ ዓለም አቀፋዊነት የሚያቀነቅን ፣ በአገሩ ተቀምጦ በልቡ ግን የሄደ ፣ በባዕድ ምድር ላይ በሰው ባሕል የተዋጠ ፣ በመልካምና በስህተት መካከል ያለውን ድንበር መለየት ያልቻለ ፣ ኃጢአትን የሚፈታበት መዝገበ ቃላት እንኳ የሌለው ፣ እውነት አንጻራዊ ነው ብሎ የሚያምን ፣ … ሊሆን ይችላል ። ይህን ትውልድ በሚመለከት የሚያስፈልጉን ነገሮች በዓለም አቀፋዊ ቋንቋዎች ትምህርት ማዘጋጀት ፣ ዘመናዊ ቀሳውስትን ማሰልጠን ፣ ፍልስፍናን የሚያውቁ ተማሪዎችን ማብቃት … በማለት እየተዘጋጀን ይሆናል። ይህ መጠነኛ መልካምነት ሊኖረው ይችላል ። ለዘለቄታው ግን መፍትሔ መሆን የሚችል አይደለም ። ለዘለቄታው መፍትሔ የሚሆነው መንፈሳዊነትና ጸሎት እንዲሁም የስብከተ ወንጌል ጠንካራ አቅም ነው ።
እየመጣ ያለውን ትውልድ በሚመለከት የምድር ገዥዎች ፍጥነቱን ለተልእኮ ፣ ወጣትነቱን ለአገር ዕድገት ከመጠቀም ይልቅ በልዩ ልዩ ሱስ እንዲጠመድ እያደረጉት ነው ። ፊልሙ ፣ ኳሱ ፣ ፈቃድ እያገኙ የመጡት አደንዛዥ ዕፆች ነገሥታት ሬሳ ለመምራት የሚሄዱበት መንገድ ነው ። እነርሱን የማያይ ትውልድ ለመፍጠር በሱስ የተወጠረ ማኅበረሰብ እየገነቡ ነው ። ዙፋናቸውን የሚያመልኩ የጥንት ነገሥታት ሲወቀሱ ነበር ። የኮንትራት ዙፋን የሆነው የዛሬው ንግሥና ግን ከቀድሞ ይልቅ አየተመለከ ነው ። ወጣቱ ትውልድ በጨከኑ ነገሥታት ብቻ ሳይሆን በጨከኑ የሃይማኖት መሪዎችም እየተጎሳቆለ ነው ። የክርስቶስ በጎች የሆኑትን ምእመናን ሥጋቸውን ለመብል ፣ አጥንታቸውን ለጥንካሬ ፣ ቆዳቸውን ለልብስ የሚፈልጉ ብዙ የሃይማኖት ሰዎች እየተፈጠሩ ነው ። በጉን በቅጡ ሳይሆን በቁሙ ቆዳውን የሚገሸልጡ ፣ በቁሙ ሥጋውን የሚያወራርዱ አንዳንዴም በክፉ መንፈስ በመታገዝ የሚያጎሳቁሉት እየበዙ ነው ። እየመጣ ያለው ትውልድ ፈጽሞ በሃይማኖት ተስፋ ቆርጦ ከሃዲ እንዳናደርገው ማሰብ ያስፈልጋል ። ፈላስፎች ካስካዱት የእኛ ክፋት ያራቀው ትውልድ ይበዛል ። ዛሬ ያላመኑትን ለማሳመን ስናስብ ያመኑትን የሚያስክዱ ጨካኝ አገልጋዮች እየፈሉ ነው ። በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች ብዙ ጸጋ ያላቸው ወንድሞችና አባቶች ሳይቀር ተገፍተዋል ። ባለቤቱ እየወጣም ደባሉ ተቀምጧል ። እንደ ትውልዱ በመናገር ትውልዱን ለመማረክ አስበን ከሆነ በጣም እየተናቅን እንመጣለን ። ትውልዱን የምንማርከው በአባታዊ ፍቅር ብቻ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ከዘመናዊነት ጋር ትግል ውስጥ አይደለችም ፣ ዘላለማዊውን ይዛለች ። እየጎዳንና እያፈረሰን ያለው ትውልድን ሳይሆን ገንዘብ የመሰብሰብ ፍላጎታችን ፣ ሰው እየፈረሰ ሕንፃ ለማቆም መሮጣችን ነው ። ከአንድ ነጋዴ የተሻለ ካላሰበ አገልጋይ ሊማርክ እንዴት ይችላል ? ከመንግሥት የተሻለ ካላየች ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ እንደራሴነቷን ልታስጠብቅ እንዴት ትችላለች ?
ጌታ ሊያደርገው ያለውን እያወቀ ጠይቆን ይሆን ? ምናልባት ወደ መንግሥቱ ሥራ ፣ ወደ ወይኑ እርሻ ሲጠራን አቅማችንን ሳይሆን አቅሙን አይቶ ነውና አንጨነቅ ። እኛ እሺታችንን እናቅርብ ፣ እርሱ መንፈሱን ይልካል ። ዋናው የሰማነው ድምፅ የእግዚአብሔር ለመሆኑ እርግጠኛ እንሁን። እርሱ ድካማችንን ለብርታቱ ፣ ትንሽነታችንን ለልዑልነቱ መገለጫ ያደርገዋል ። እግዚአብሔር ቀድሞ እንዳንዘገይ ፣ እግዚአብሔር በሌለበትም እንዳንፈጥን ማስተዋል ያስፈልጋል ። አዎ የሚያደርገውን ያውቃል ። በነቢዩ፡- “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” ይለናል /ኤር. 29 ፥ 11/ ።
ነገ በእግዚአብሔር እጅ ከሆነች በእግዚአብሔር እጅ ያለ ክፉ ነገር የለም ። የሚያደርገውን እርሱ ያውቃል ። ከእኛ የሚጠበቀው መቀደስ ነው ። እኛ ስንቀደስ ነገ ድንቅ ነው ። “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ አለ ” /ኢያ. 3፥5/ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ