የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቦታችንን መያዝ

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት ስለ ሦስቱ መባልዕት ይናገራል ብለናል ። የበረከተው እንጀራ ፣ የበረሃው መና ፣ የዘላለም ኅብስት በዚህ ምዕራፍ ተጠቅሰዋል ። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ምግቦች ሟቾችን ከሞት አላዳኑም ። አንድ መብል ግን ሕይወት ይሰጣል ። እርሱም የጌታ ሥጋና ደም ነው ። ሁለቱ ሥጋዊ ናቸው ። ሦስተኛው ግን መንፈሳዊ እንጀራ ነው ። ሁለቱ ምግቦች ቢበሏቸው በቃኝ ያሰኛሉ ። ሦስተኛው ግን ተበልቶ የማይጠገብ ነው ። ሁለቱ መባልዕት የሆድን ፍላጎት ይሞላሉ ። ሦስተኛው ግን የመንፈስን ፍላጎት ይሞላል ። የሦስቱም መባልዕት ምንጩ እግዚአብሔር ነው ። ሦስተኛው ግን ዘላለማዊ ነው ። የመጀመሪያው መብል የተሰጠው ጌታን እንዲሁ ለማድነቅ ብቻ ሲከተሉ ለነበሩት የርኅራኄ ምግብ ነው ። የበረሃው መና ደግሞ ለከነዓን መንገደኞች የተሰጠ ነው ። ሦስተኛው መብል ግን ለጽዮን መንገደኞች የተሰጠ ነው ። ሁለቱ መባልዕት ታላቅ ኃይልና ፍቅር የተገለጠባቸው ናቸው ። ሦስተኛው መብል ግን ፍቅርና መሥዋዕትነት የተገለጠበት ነው ። ሁለቱ መባልዕት የእግዚአብሔርን ኃይል ይተርካሉ ። ሦስተኛው መብል ግን የእግዚአብሔር ልጅ ለቤዛ ዓለም መሞቱን ያስረዳል ።
ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን አድርገው “እንግዲህ ሥጋዬን አትበሉት ?” ይላሉ ። ለሰዎች የመጨረሻውና የማይፈጽሙት ደግነት ሥጋን መስጠት ነው ። ጌታችን ግን ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ አለ ። የሰዎች የመጨረሻ ደግነት እንኳ ያልሆነው የእርሱ የመጀመሪያው ደግነት ነው ። ወላጆቻችንን ስናያቸው እኛ እንኳ ስናውቅ ጠውልገዋል ። መልካቸውን የበላነው እኛ ነን ። ዝምተኛው ተናጋሪ የሚሆነው ሲወልድ ነው ። ስለዚህ ጠባያቸውንም ለውጠነዋል ። ገንዘባቸውን ብቻ ሳይሆን ጠባያቸውን ፣ መልካቸውንም በልተነዋል ። ይህን መሥዋዕትነት የሚገባን በትምህርት ሳይሆን እኛም በወለድን ጊዜ ነው ። ጌታችንም ማስተማሩ ፣ በረከት መስጠቱ ሳያንስ ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ብሏል ። የታላቁ መሥዋዕትነቱ ማሳያ ነው ፣ ሥጋና ደሙ ። ልጆቻችን ሲያደክሙን ስናይ አንድ ነገር ወደ ውስጣችን ይመጣል ፡- “እኔም ለካ ወላጆቼን ያደከምኩት እንደዚህ ነበር ?” ጌታ ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ሲል ጥልቅ ፍቅሩንና አባትነቱን እናያለን ። አንድ መብል ልንበላ ስንል መዓዛና ውበት አለው ። መዓዛው ለአፍንጫችን ፣ ውበቱ ለዓይናችን ፣ ጣዕሙ ለምላሳችን ነው ። ከበላነው በኋላ ግን ሕይወት አለው ። የሕይወት እንጀራ የሆነው ክርስቶስ የዓይን ማረፊያ ፣ የጣዕም ዳርቻ ፣ የሕይወት መፍለቂያ ነው ።
     የጌታ ሥጋና ደም ሞቱንና ትንሣኤውን የሚናገርና የሚያናግር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ የሚናገር መብል የለ ይሆናል ፣ የሚያናግር መብል ግን በግድ አለ ። ዝም ያለ ሁሉ ሲጠግብ ይናገራልና ። የጌታና ሥጋና ደም የሚናገርና የሚያናግር መብል ነው ። በርግጥ ሥጋው ፣ በርግጥ ደሙ ካልሆነ ሞቱን እንዴት ይናገራል ? ሥጋወደሙ ተአምራዊ መብል አይደለም ። በሃይማኖት የምንቀበለው እውነተኛው ማዕድ ነው ። የቃና ዘገሊላ ውኃ ወደ ወይን ጠጅ ተቀይሯል ። ጣዕሙም መልኩም ተለውጧል ። የጌታ ሥጋና ደም ግን ጣዕሙና መልኩ ሳይለወጥ በሃይማኖት የምንቀበለው ነው ። በቃና የተለወጠውን ውኃ ሁሉም ጠጥተዋል ። የጌታና ሥጋና ደም ግን ላመኑ ብቻ የታዘዘ ነው ። የቃና ዘገሊላ ተአምር ከሐፍረት ያዳነ ነው ። ከሞት ግን የሚያድነው የጌታ ሥጋና ደም ነው ። ጌታችን ሥጋዬን በበላችሁ ጊዜ ሞቴን ትናገራላችሁ አለ እንጂ የቃናውን ወይን በጠጣችሁ ጊዜ ሞቴን ትናገራላችሁ አላለም ። ለመብላት መታጠብ ግድ ነው ፣ የጌታን ሥጋና ደም ለመቀበልም ንስሐና ይቅር መባባል አስፈላጊ ነው ። የሚታየው ኅብስት ከማይታየው ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ፍጹም አንድነት አለው ፣ የሚታየው ወይን ከማይታየው የክርስቶስ ደም ጋር ፍጹም አንድነት አለው ። አንድ ፈላስፋ “እንዴት ኅብስቱን የክርስቶስ ሥጋ ትላለችሁ ?” ብሎ ይዘብታል ። አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አምናለሁ የሚልም እንዲህ ካለ ፍልስፍና እንጂ እምነት ላይ አለመሆኑን እንረዳለን ። እምነት ከ “እንዴት ?” የሚያድን ሞኝነት ነው ።
ምዕራፍ ስድስት ስለ መብል የሚናገር ነው ብለናል ። አበርክቶ ቢያበላቸው እናንግሥህ አሉት ። የንጉሥ ፈተና የኑሮ ዋስትና ነውና ። የሕይወት እንጀራ የሆነውን ጌታ ስንበላ ግን ላንግሥህ ሳይሆን ንገሥብኝ እንላለን ። ሁሉም ሰው በአገሬ ላይ ንገሥ ይላል ። ችግሩ ያለው በልቤ ላይ ንገሥ የሚል መጥፋቱ ነው ። ክርስቶስ የሚገዛው አገር ብዙ ዜጎች ይፈልጋሉ። ልባቸውን ለእርሱ መስጠት ግን ይቸገራሉ ። ልጆቻቸውን እንዲማርክ ይጸልያሉ ፣ እነርሱ ግን አይፈልጉትም ። ጥሩ መሪዎችን እንዲያስነሣ ይጸልያሉ ፣ መልካም ተመሪ ለመሆን ግን አይለምኑም ። የመንፈስ ጠኔ ከባድ ነው ። ያንን የሚያስታግሠው ክርስቶስ ብቻ ነው ። ዛሬ ብዙ ሕዝቦች ደግ ንጉሥ ይፈልጋሉ ። የሚያረካቸው ሳይሆን የሚያጠግባቸው ነው ። ክርስቶስ ግን የሕይወት ጥጋብ ነው ። ብዙ የሰለጠኑ አገራት መሪዎች ሕዝባቸውን በሥጋ ደግፈውት በመንፈስ ግን ጥለውታል ። ሆዱን ሞልተው ክብሩን ግን አስጥለውታል ። ቤት ሠርተውለት ፣ ከሕይወት መርሕ ግን አውጥተውታል ። የጌታችን ሥጋና ደም ግን በእውቀት በፍቅርና በእምነት ለሚቀበሉት ከመንፈስ ጠኔ ያድናል ። ይህን የምንናገረው ለአማኝ ነው ። ሰው ገላን እንጂ ነፍስን ማቀፍና ማሞቅ አይችልም ። ብዙዎች ታቅፈዋል ፣ ውስጣቸው ግን በብርድ ይንዘፈዘፋል ። ክርስቶስ ግን ውስጥን ያቅፋል ።
ከተቀደሱት ምሥጢራት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቊርባን በዚህ ምዕራፍ ይገለጻል ። በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቊርባን አልተመሠረተም ነበርና የሚናገረው ሰለ ቅዱስ ቊርባን አይደለም የሚሉ ሰዎች አሉ ። የጥምቀት ምሥጢር ሳይጀመር ለኒቆዲሞስ ጥምቀትን አስተምሯል ። ስለ ዳግም ምጽአትም በሰፊው ተናግሯል ። ከዓመት በኋላ የሚሆነውን ቀድሞ ቢናገር ለጌታችን እንግዳ ነው ወይ ? የምናገረው ቃል መንፈስም ነው ሕይወትም ነው ብሏልና ስለ ቊርባን እየተናገረ አይደለም የሚሉ አሉ ። አዎ ምሥጢራት በሚታይ መንገድ የማይታየውን ጸጋ የምንቀበልባቸው ናቸው ። ለበሽተኛ የሚቀባው ዘይት ወይም ቅብዐ ቅዱስ በዓይን ስናየው ዘይት ነው ፣ ያንንም ፈውስ ማምጣት አይችልም ። ነገር ግን የማይታየውን የጌታን እጅ የምናገኝበት ነው። ቅዱስ ቊርባንን የቅብዐ ቅዱስ ያህል እንኳ ክብር አለመስጠት ከክርስቲያን የሚጠበቅ አይደለም ። ቅዱስ ቊርባንን ለአንድ ሙት እንደሚደረግ ተዝካር ወይም መታሰቢያ ብቻ የሚመለከቱም አሉ ። ጌታችን ግን ሕያው ነውና ቅዱስ ቊርባን ከመታሰቢያም በላይ ነው ። መታሰቢያነቱም ስላለፈው ሳይሆን ሕያው የሆነውን ሞትና ትንሣኤውን የምንመሰክርበት ነው ።
አዳም አትብላ ተብሎ የበለስ ፍሬ በላ ። መብል የፈለገውን ሰው እግዚአብሔር ብላ በማለት ሥጋና ደሙን ሰጠው ። አትብላ ሲባል የበላው ሰው ብላ ሲባል ደግሞ እየበላ አይደለም ። አዳም የሕይወትን ፍሬ እንዳይበላ ከገነት ተባርሮ ነበር ። ጌታ ግን የሕይወትን ፍሬ ሥጋውንና ደሙን እንደገና ሰጠን ።  በመብል የጠፋው ዓለም በመብል ተባረከ ።  
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻ ስለተከናወነው ተአምር በመናገር የሚጀምር ነው ። ጥብርያዶስ ሦስት ስሞች ያሉት አንድ ባሕር ነው ። የኬኔሬት ፣ የገሊላና የጥብርያዶስ ባሕር ይባላል ። ጥብርያዶስ ብዙ አምላካዊ ተአምራት የተደረጉበት ባሕር ነው ። ስለዚህ መንፈሳዊ ትዝታን የተሸከመ ባሕር ነው ። ዛሬ በጥብርያስ ላይ ተአምር አይፈጸምም ። ባሕር በሆነው ኑሮአችን ላይ ግን ተአምር ይፈጸማል ። ባሕሩ ልዩ ልዩ ነው፣ ተአምር አድራጊው ግን አንድ ነው ። በጥብርያዶስ ላይ የጌታን ክንድ ያዩት ጥብርያዶስ በመመቸቱ ሳይሆን ባለ መመቸቱ ነው ። የማይመቹ ነገሮች የጌታ ክብር መገለጫዎች ናቸው ። ምስጋና እናብዛ ። እጥረት ከሆነ በጀት ፣ ዳገት ከሆነ ጉልበት ይለቀቃል ። እንደ ተለመደው ለመኖር ምቾት ፣ በተአምር ለመኖር ተግዳሮት ያስፈልጋል ።
“ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ባሕር ማዶ ተሻገረ ፤ እርሱም የጥብርያዶስ ባሕር ነው ።” /ዮሐ. 6 ፥ 1/ ። በእስራኤል ምድር ላይ የሙት ባሕርም አለ ። የሙት ባሕር ፣ የሙት ባሕር የተባለው አንዱ ምክንያት ውጦ ዝም የሚል የተቀበለውን የማይለቅ ስለሆነ ነው ። ለእስራኤል ወንዞች መቃብር ነው ። የሙት ባሕር የእስራኤል ወንዞች የሚገቡበት ነገር ግን የማይወጡበት ነው ። ጥብርያዶስ ግን አስደናቂውን የእስራኤል እርሻ የሚያለማ ፣ የእስራኤላውያንን ጥም የሚያረካ ባሕር ነው ። ጥብርያዶስ ለእስራኤል አንድ ለእናቱ የሆነ ባሕር ነው ። ገሊላ ሰሜናዊ አውራጃ ነው ። ጥብርያዶስ አንዱ ከተማ ነው ። ጌታችን በዚህ ባሕር ላይ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቷል ። ዓሣዎችን በተአምራት እንዲጠመዱ አድርጓል ። አሁንም የማያልቅበት ጌታ ሌላ ተአምራት ሊያደርግ ነው ። ከተአምራት የሚበልጠው ተአምራት ግን ተፈጽሟል ። እርሱም የደቀ መዛሙርቱ ሕይወት መለወጥ ነው ። የሚደረገው ከተደረገው አይበልጥም ። እርሱም ውሉደ እግዚአብሔር /የእግዚአብሔር ልጆች/ መሆናችን ነው ። በባሕር ዳርቻ ላይ መመገብ ብዙ የሚዝናኑ ሰዎች የሚያደርጉት ነው ። ጌታም በተአምራት ያበረከተውን በባሕር ዳርቻ ላይ አድርጎ እየመገበ ነው ። ምናልባት መንፈሳዊነት ተጭኖን መዝናናት ወይም የዕረፍት ጊዜ ማድረግ ኃጢአት መስሎ ይሰማን ይሆናል ። ነገር ግን እግዚአብሔር የፈጠረውን ማድነቅ በራሱ ዝማሬ ነው ። እግዚአብሔር እንድናርፍ ይፈልጋል ። ማለትም ከአገልግሎት ዘወር ብለን በመልካም ስፍራዎች ለራሳችን ጊዜ እንድንሰጥ ይፈልጋል ። ጌታችን ያስተማረው በታንኳ ላይ ፣ በአበባ እርሻዎች ውስጥ ፣ በከፍታ ቦታዎችና በባሕር ዳርቻ ውስጥ ነው ። ሕዝቡን አስጨንቆ አላስተማረም ። ንጹሕ አየር እንዲተነፍሱ ፣ ውብ ነገር እንዲያዩ እያደረገ አስተምሯል ።
“በበሽተኞችም ያደረገውን ምልክቶች ስላዩ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።” /ዮሐ. 6 ፥ 2 /። የምንደርስበት ሲጠፋን ምልክቱን ንገሩኝ እንላለን ። ምልክት መዳረሻ እንጂ መድረሻ አይደለም ። በዮሐንስ ወንጌል ከመዳናችን ውጭ ያሉት መለኮታዊ ተአምራት ሁሉ “ምልክት” ተብለዋል ። ምልክትነታቸውም ለነፍሳችን መዳን ነው ። ወንጌላዊው ዮሐንስ ድንቅና ተአምራትን በጥንቃቄ ነው የጻፈው ። የጠራውም “ምልክት” ብሎ መሆኑን አስተውሉ ። የቃናው ውኃ መለወጥ ምልክት ነው ። ዋናው የእኔም ሕይወት ይለወጣል ብሎ ለማመን ነው ። እግዚአብሔር ሌላ ድንቅ ስላለው ተአምራቱን ምልክት ነው የሚለው ። ሰይጣን ግን ሌላ ድንቅ ስለሌለው ተአምራቱን ፣ ተአምራት ነው የሚለው ። ዛሬ ከወንጌል ይልቅ ተአምራቶች የከበሩባቸውን አገልግሎቶች ስታዩ ችግራቸው እንደ ዮሐንስ ከዘላለም አለመጀመራቸው ነው ። ዮሐንስ ሲጀምር “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” ነው ያለው ። ደጋግመን እንደምንናገረው ተአምር ስላየ እግዚአብሔርን የሚከተል የበለጠ ካሳየው ሰይጣንንም ይከተላል ። አሕዛብን የሚያስደነግጠው ተአምር ነው ፣ አማኝን የሚያስደነግጠው ፍቅር ነው ። ተአምር ለማያምኑት ነው ፣ ዛሬ ግን የሚያምን ይወዳደርበታል ። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ስብከት ተንቆ ተአምራት ወይም ልሳን ገንኖ ነበር ። ትንቢት የተባለው ስብከት በአማኞች መናቁን ሐዋርያው ይገስጻል ፡- “እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም ፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም ።”/1ቆሮ. 14፥22/።
ጌታችን በመጻጒዕና በሌሎች በሽተኞች ላይ ያደረገውን ተአምራት አይተው ብዙ ሕዝብ ተከተሉት ። ያዩት ትልልቅ ተአምራት ቢሆንም አልረኩም ። ዓመት ሙሉ የሚያመሰግኑበት ክስተት ቢሆንም ለእኔስ ለምን አይደረግልኝም በሚል ስሜት እያሰሱት ነው ። በአጭር ቃል ጌታን ሳይሆን የእጁን ተአምራት ፈልገው ይከተሉት ነበር ። እነዚህ ሰዎች የሚከተሉት ሌላ ምልክት ነው ። ምልክትን አይቶ የሚከተል ሌላ ምልክት እየፈለገ ነው ። ምልክት የጨው ውኃ ነው ፣ መልሶ ያስጠማል ። ፍቅር የሕይወት ውኃ ነው፣ እንዳረካ ይኖራል ። ምልክት አያስፈልግም ወይ ? ያስፈልጋል ። አጠገባችን ያሉ በሽተኞች እንዲፈወሱ መጸለይ አለብን ። ተስፋቸው የጨለመባቸው ጉዳተኞች ኃይል እንዲያገኙ ማልቀስ አለብን ። በምናየው ተአምር ግን ክብር ለእኔ ሳይሆን ክብር ለጌታ ማለት አለብን ። ዛሬ ተአምራቶች የሱቅ ማስታወቂያ ነው የሆኑት ።
“ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጣና በዚያ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተቀመጠ ። የአይሁድ በዓልም ፋሲካ ቀርቦ ነበር ።” /ዮሐ. 6፥4/ ። ጌታችን ልዑለ ባሕርይ ነውና ከፍ ያለ ቦታ ይቀመጥ ነበር ። በርግጥ ተራራ ልዕልናውን ፣ ጥልቁም የጥበቡ መግለጫ ባይሆንም እርሱ ግን በተራራ ላይ ያስተምር ነበር። ብዙ ጊዜም በተራራ ላይ ይቀመጥ ነበር ። ተራራ ሁሉን ያሳያል ። በጠላትም ቶሎ አይያዝም ። በክርስትናም ሁሉን ማየት እግዚአብሔር ከሚፈልገው ብስለት አንዱ ነው ። በጠላትም ስልትና ወጥመድ እንዳንገባ በጥንቃቄ መኖር ይገባል ። ጌታችን የፋሲካ በዓል እንደ ቀረበ አይቶ አንድ ቀን እኔ እተካዋለሁ በማለት አላጣጣለውም ። ምሳሌውም ፍጻሜውም ከእርሱ የተገኘ ነውና አከበረው ። አንድ ቀን እንደሚተካው እያወቀ አከበረው ። አንድ ቀን እንደምንተካቸው እርግጠኛ የሆንባቸውን እያከበርናቸው ይሆን ? የሚያልፈውም በጊዜው ፣ የሚተካውም በጊዜው ካልሆነ አደጋ አለው ። ያለ ጊዜው የተነቀለ ጥርስ ፣ ሥር ይበጥሳል ። ያልጊዜውም ቦታ የያዘ ያበላሻል ። ጥሪ የጊዜ ሰሌዳውን ካላከበረ አደጋ አለው ። በነቢያትና በሐዋርያት መካከል መሸጋገሪያ ዮሐንስ መጥምቅ ነበረ ። የሚያረካክቡ አስፈላጊ ናቸው ። ነቢያትን ነቢያት ፣ ሐዋርያትን ሐዋርያት ያደረጋቸው ጥሪና ጊዜ ነው ። የሁሉም ጥሪ አንድ ዓይነት ቢሆንም ጊዜ ቢለዋወጥ ሐዋርያት ነቢያት ይሆኑ ነበር ። ስለዚህ ጥሪ ፣ ጊዜና መልእክት አስፈላጊ ናቸው ። ጥሪ አለኝ ? ጊዜው ነውን ? የማስተላልፈው መልእክትስ ምንድነው ? ነቢያት ጊዜ ቢለዋወጡ ክርስቶስ በመጣበት ዘመን ክርስቶስ ይመጣል እያሉ ይሰብኩ ነበር። ጌታ ይቀመጥ የነበረው ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነው ። ብዙ ሺህ ሕዝብ ቢከተለውም ዋነኛ ተልእኮው ደቀ መዛሙርቱ ነበሩ ። ከአምስት ሺህ ሕዝብ 12 ደቀ መዛሙርትን አቀረበ ። ከ12ቱ ደግሞ ሦስቱን ጴጥሮስ ፣ ያዕቆብና ዮሐንስን የምሥጢር ደቀ መዛሙርት አደረጋቸው ።
ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በተራራ መቀመጡ ትክክለኛ ቦታችንን መያዝ እንዳለብን ለማስተማር ነው ። አገልጋዮች የአገልጋይነት ቦታቸውን ሲይዙ ምእመናን ቦታቸውን ይይዛሉ ። መሪዎች ትክክለኛ ቦታቸው ላይ ሲሆኑ ተመሪዎች መሆን ያለባቸውን ይረዳሉ ። ብዙ ጊዜ የሚነገር ነገር አለ ፡- “እኛ የእናንተ አገልጋይ ነን ።” በትሕትና ከሆነ መልካም ነው ። ቀሳውስትና ዲያቆናት ግን የእግዚአብሔር አገልጋይ ናቸው ። አንድ ሰው በድፍረት ሲናገር የሰማሁት ነገር አለ ፡- “አሥራታችንን የምናወጣው እንደምንፈልገው ለመገልገል ነው።” ምእመናን አሥራታቸውን እንደ ክፍያ እንጂ እንደ ግዴታቸው አልቆጠሩትምና ይህ አስተሳሰብ ከባድ ነው ። ልክ ነው የከፈለ ያዝዛል ። ባንድ አቁሞ የሚያዘፍነው የሚፈልገውን ያዘፍናል ። የከፈለ ያዝዛልና ። አገልጋዮች ግን ባንድ አይደሉም ። አፈ ክርስቶስ ናቸው። መንበሩን ማስደፈር አይገባንም ። እኛ ክብር አይወድብን ይሆናል ። ከእኛ በኋላ ለሚመጣው የተደፈረ መንበር ማስረከብ አይገባንም ። ወንጌላዊነት ፣ አስተማሪነት ፣ እረኝነት መንበር ነው ። የመንበሩን ክብር ካልጠበቅን አገልግሎታችንም እየተዋረደ ይመጣል ። ጅብ አፍንጫውን የሚያስገባበት ቀዳዳ ካገኘ ቤትን መገልበጥና መግባት ይችላል ። ዘመናዊ ትውልድም ትንሽ ክፍተት ካገኘ ለመዳፈር ይቸኩላል ። በትክክለኛው ቦታችን ካልሆንን ትክክለኛ ዕይታ አይኖረንም ። ብዙ ትልልቅ ኃላፊነት ላይ ያሉ አባቶች፡- “ሰው አሳስቶኝ ነው” እያሉ ሲናገሩ ይሰማል ። ያ ማለት እነርሱ በሌሎች ወንበር ላይ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በእነርሱ ወንበር ላይ ስለ ተቀመጡ ነው ። እገሌን ያባርሩት ፣ እገሌን ይሹሙት የሚሉ ምእመናን ስፍራችንን ባለማወቅ ያሰለጠናቸው እንደሆኑ መገንዘብ አለብን ። ጥሩ የሂሳብ ሹም ጥሩ ካህን መሆን አይችልም ። ሁሉም ቦታ ቦታውን ካልያዘ አደጋ ይከሰታል ። ይልቁንም የእኛ ዘመን አፈኛ የበዛበት ሁሉም የማያውቀውን እንደሚያውቅ አድርጎ የሚናገርበት ዘመን ነው ። የመሥሪያ ቤት ሥራ ፣ የዳኝነት ሥራ መጠጥ ቤት የገባበት ፣ በቀን የሚያናግር ኃላፊ ጠፍቶ ማታ በውድቅት ሌሊት በየሆቴሉ የሚያወራበት ነው ። የተከበሩ ወንበሮች ባዶ ሁነው የባለጌ ወንበር ላይ ሥራ ይሠራል ፣ ዳኝነት ይካሄዳል ። አንድ ሰው ጨረታን በሚመለከት ፡- “ማምሸት ስለማልወድ አላገኘሁም” ብሎ ሲናገር ሰምቻለሁ ። ይህ ሰው ከሃያ ዓመታት በላይ ሠርቶ እየከሰረ ያለ ነው ። ወንበሮች ባዶ ስለሆኑ መፍትሔዎች ሊገኙ አልቻሉም ። ሐኪሙ ሲፈለግ አይገኝም ፣ ቤታቸው ነው የሚያክሙት ይባላል። ያለፋበትን ሲከፈለው ግን አይፈራም ። እንዴት ሰው በድህነት ያስተማረውን ሕዝብ ለመዝረፍ ይማራል?
የአይሁድ ፋሲካ ቀርቦ ነበር ። ለደቀ መዛሙርቱ በዓል ብቻ ነው ። ጌታ ግን ፋሲካችን ሁኖ የሚታረድበትን ቀን ያስብባታል ። አጠገባችን ያሉት ስለ በዓል ሲያስቡ እኛ ግን የበዓሉ በግ ሁነን ራሳችንን አስበነው ይሆን ? እኛ የምናስበውና ልጆቻችን የሚያስቡት ለየራስ ነው ። አንድ ሰው አደጋ ደርሶበት በዚያም ላይ ታስሮ “ሚስቴ እንዳትሰማ” ብሎ ተጨነቀ ። ከሰማች ልጆቹን ምን አድርጋ ትመጣለች ? ብሎ ነው ። ከወጣ ስለ ዘገየ ገንዘብ መላክ ብቻ ሳይሆን ፖሊሶቹን እየለመነ ስልክ ደውሎ “እመጣለሁ” ይላል ። እርሷ ግን ተጣላችው ። አንተ ደልቶህ ትንቀባረራለህ ብላ ሰደበችው ። “እንደ እናቴ ሳይሆን እንደ ሚስቴ አውለኝ” የሚባለው እውነት ይሆን ? ያለንበት ሁኔታና ሰዎቹ የሚያስቡት ለየቅል ነው ። የሚታየንና የሚታያቸው ቢለያይም ልናዝን አይገባም ። ስለ ባሎቻቸው በመጨነቅ በሽተኛ የሆኑ ብዙ ሴቶችን አውቃለሁ ። “ሁሉን አሟልቼ ምን ሆነሽ ነው ?” ይሏቸዋል ። ሁሉን ማሟላት ሲባል ሰላምን ይጨምራል ወይ ? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። እንደውም ሁሉም ካልተሟላ የማትገባ የቤት ሠራተኛ ናት ። ሁሉን የምንለው ሆድን ብቻ ነው ። ሕይወት ግን ከሆድ ያለፈ ጥያቄ አላት ። አዎ የምናስበውና የሚያስቡት ቢለያይ ለማስረዳት ብዙ መጣር አያስፈልገን ይሆናል ። ጌታችንን ስናስብ ደስ ሊለን ይገባል ። ዐፄ ቴዎድሮስ ሰው እያስገቡ በእሳት ሲያቃጥሉ ውለው ዝናብ መጣና ጥለው ሄዱ ። ሌሊቴን በሙሉ ከእናቱ ጋር ብርድ ሲያንጠረጥረው ያደረ ሕጻን ወደ ማቃጠያው ቤት ካልገባን እያለ እናቱን ይጎትታል ። እናቱ ሞትን እያየች ወደ ኋላ ትመለሳለች ። ሕጻኑ ደግሞ ብርዱን ፈርቶ ካልገባን ይላል ። ዐፄ ቴዎድሮስም የሕጻኑን ልቅሶና የእናቲቱን ሁኔታ አይተው፡- “ምንድነው ?” ብለው ይጠይቃሉ ። “ሕጻኑ ብርዱ ስለ ጸናበት ወደ ቤት እንግባ ይላል ፣ እናቲቱ ደግሞ ሞትን ፈርታ እንቢ እያለችው ነው” አሏቸው ። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ፡- “ወይ እኔን ግደለኝ ፣ ወይ ሕዝብህን አሳርፍ” ብለው አለቀሱ ። የዚያን ቀን የሚሞቱ ሰዎች በዚህ ሕጻን ዳኑ ። እናቲቱ የሚታያትና ሕጻኑ የሚታየው ለየራስ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ስለ በዓሉ ሲያስቡ ጌታ ግን ፋሲካ ሁኖ ስለሚሞትባት ቀን ያስባል ።
ደግመን እንናገር ። ቦታችንን መያዝ አለብን ። የአገልግሎቱንና የአገልጋዮችን ክብር መመለስ ያስፈልገናል ።
ዝንጀሮን በባሕር ፣
በገደል ላይ ዓሳ ፣
መስቀል ለዛር ፈረስ ፣
ከበሮን ላንካሳ ፣
ጌታዬ ብይንህ ተወላገደሳ ።    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ