ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለትን ሲተረጉም የሰበከው ስብከት
የክርስቶስ የተአምራቱ/የምልክቱ ሥራዎች እንዲህ ያሉ ናቸው ። ተአምራቱ/ምልክቱ በተፈጥሮ ከሚሆኑት ነገሮች በበለጠ የተሟሉና የተሻሉ ናቸው ። ይህ ነገር በሌሎች አጋጣሚዎችም ታይቷል ። እርሱ የታመመን የሰውነት ክፍል ሲፈውስ ቀድሞ ከነበረው በላይ የተሻለ ያደርገዋል ። የተለወጠው ወይን ምርጥ ወይን ነበር ። ይህንንም አገልጋዮቹ ብቻ ሳይሆኑ ሙሽራውና አሳዳሪውም መስክረዋል ፣ ይህም በክርስቶስ የሆነ ነበር ።
ኢየሱስ በዚያ ጊዜ ውኃውን ወይን እንዳደረገው ያን ጊዜም ዛሬም ድካማችንን የማይረጋውን ፈቃዳችንን መቀየርን አላቋረጠም ። ከውኃ የማይለዩ (ከውኃ የተለየ ማንነት የሌላቸው) ቀዝቃዛ ፣ ደካማ የሆኑ ያልተረጋጉም ብዙዎች አሉ ። እንዲህ ያለ ፀባይ/ማንነት ያላቸውን ፈቃዳቸውን ወደ ወይን ይቀይረው ዘንድ ወደ ጌታ እናቅርባቸው ። እነርሱም ከዚህ በኋላ ጥንካሬ የጎደላቸው ፣ ልፍስፍስ ፣ ደካማ ፣ ሰነፍ እንዳይሆኑ ነገር ግን ጠንካራ ሆነው በመቆም ለራሳቸውና ለሌሎች የደስታ ምንጭ ይሆናሉ ። ነገር ግን እነዚህ ቀዝቃዛዎች ማን ሊሆኑ ይችላሉ ? እነርሱ ልባቸውን ለዚህ ለሚያልፈው ዓለም አብለጭላጭ ነገር የሰጡ ፣ የዚህን ዓለም ሀብት ያልናቁ ፣ የክብርና የሥልጣን ወዳጆች የሆኑ ናቸው ። እነዚህ ነገሮች ሁሉ (አንድ ቦታ) የማይረጉ እንደሚወርድ ውኃ ወደ ገደል በኃይል የሚፋጠኑ ናቸው ። ዛሬ ሀብታም/ባለ ጸጋ የሆነው ነገ ድሃ ይሆናል ። አንድ ቀን መልካም ዜናን ፣ ሰረገላና ብዙ ተከታዮች የነበረው (ሰው) በቀጣዩ ቀን ጨለማ ቤት ይኖራል ። እንደገና ሆዳምና ብኩን የሆነው ሰውም ራሱን እስኪፈነዳ ድረስ ከሞላ በኋላ ለአንድም ቀን በጣፋጩ ምግብ ያገኘውን ጣዕም ማቆየት አይችልም ። ነገር ግን ይህ ካለቀ በኋላ ይህንን ለማደስ ተጨማሪ ምግብ ለመብላት ይገደዳል ። በዚህም ከጎርፍ/ከወራጅ ውኃ በአንዳችም ነገር አይለይም ። ጎርፍ/ወራጅ ውኃ ላይ የመጀመሪያው ከሄደ በኋላ በተራው ሌላው ይከተላል ።
ሆዳምነት ላይም እንዲሁ ነው ። አንዱ ገበታ ካለቀ በኋላ ሌላ እንድንፈልግ ግድ ይለናል ። የምድራዊ ነገሮች ጠባይና ዕድልም/ዕጣም እንዲሁ ነው ። ፈጽሞ አይረጋጋም ነገር ግን ሁልጊዜ ይፈሳል ይፋጠናል/ይቻኮላል ። ነገር ግን ሀብት ላይ መፍሰሱና መጣደፉ ብቻ ሳይሆን ሌላም ብዙ የሚያስቸግሩ የሚያደክሙ ነገሮች አሉ ። በሚፈጥረውም ሁከት የሰውነትን ጥንካሬ ይሸረሽራል ፣ ነፍስንም ከመልካምነቷ ይለያታል ። ሀብትና የማያቋርጥ ምኞትም የጤናችንን ድንበር ጠራርገው እንደሚወስዱት የባሕሮች ኃይለኛ ሞገድ እንኳን ዳርቻዎቻቸውን በቀላሉ ሸርሽረው እንዲሰምጡ አያደርጉም ።
ወደ ሐኪም ቤት ሄዳችሁ ብትጠይቁት አብዛኛዎቹ በሽታዎች በዚህ ምክንያት እንደሚመጡ ይነግሯችኋል ። በልክ የሆነ ሕይወትና የተመጠነ ማዕድ የጤናዎች ሁሉ እናት ነች ። ስለዚህ ሐኪሞች ፡- አለመጥገብን ጤንነት ብለውታል ። ምክንያቱም በምግብ አለመጥገብ ጤንነት ስለሆነ ነው። የተመጣጠነ ማዕድንም የጤንነት እናት ብለዋታል ። አሁን የተመጠነ ፍላጎት የጤናዎች እናት ከሆነች ጥጋብ ደግሞ የበሽታና የዝለት እናት እንደሆነች ግልጽ ነው ። ይህም ከሐኪሙ የመፈወስ በላይ የሆነ ጉዳትን ያመጣል ። እግር ላይ የሚከሰት ሪህ ፣ አንጎል ውስጥ የሚገኙ የደም ሥሮች ጉዳት ፣ የዓይን መጥፋት ፣ እጅ ላይ የሚሰማ ሕመም ፣ የድምፅና የሰውነት መንቀጥቀጥ ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ መገታት (ሽባነት) ፣ ውስጣዊና የሚያነድ ትኩሳት ጊዜ ስለሌለን ልንዘረዝራቸውን የማንችላቸው ከዚህ በላይ ሌላ ብዙ በሽታዎች የጾምና የተመጣጠነ አመጋገብ ተፈጥሮአዊ ውጤቶች ሳይሆኑ የጥጋብና አብዝቶ የመመገብ ውጤቶች ናቸው ። ከእነዚህ የሚመጡትን የነፍስ ሕመሞች ብትመረምሩ እነዚህን ታገኛላችሁ ምኞት ፣ ስንፍና ፣ ኀዘን ፣ ድንዛዜ ፣ ከንጽሕና መራቅ/በኃጢአት መቆሸሸ ፣ በሁሉም ነገር ውስጥ መሳሳትንና ከንቱ መሆንን ።
የእነዚህ ነገሮች ምንጭ ጥጋብና ለክቶ አለመብላት እንደሆነ ታውቃላችሁ ። እንዲህ ካለ ግብዣ በኋላ እንዲህ ያለ ሰው ነፍስ በእነዚህ ምኞቶች ተቆራርጦ በዱር አራዊት ከተቦጫጨቀ አህያ እንኳን ያልተሻለ ይሆናል ። ሀብት ላይም ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች ምን ያህል ሕመም እንደሚያጋጥማቸውም ምን ያህል ከደስታ የራቁ እንደሆኑ ልናገር ? እነዚህን ቆጥሬ እንኳን አልጨርሳቸውም ። ነገር ግን በአንድ ነጥብ ሁሉንም ግልጽ ላድርግ ። አስቀድሜ እንደተናገርሁት ዓይነት ያለ ማዕድ ላይ ማለትም በጣም ድሎት የበዛበትና ዋጋውም ከፍ ያለ ማዕድ ላይ ሰዎች በደስታ አይመገቡም ። ጥጋብ የሁሉም በሽታዎች ምንጭና ሥር እንደሆነ መቆጠብ/ጾም የደስታና የጤንነት እናት ነች ። ጥጋብ ካለ ፍላጎት ሊኖር አይችልም ፣ ፍላጎትም ከሌለ ደስታ እንዴት ሊኖር ይችላል? ስለዚህ ድሀዎች ከሀብታሞች የተሻለ መረዳት ያላቸውና ጤናሞች እንደሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሀብታሞችም የበለጠ ደስተኛዎች እንደሆኑ ልንረዳ ይገባል ።
ስለዚህ ነገር ስንወያይ ከስካርና ከሀብት እንሽሽ ። ነገር ግን በማዕድ ካለው (ስካርና ሀብት) ብቻ ሳይሆን በሕይወት ላይ ካለው (ስካርና ጥጋብም) ጭምር እንጂ ። በዚህ ፈንታ በመንፈሳዊ ነገር የሚገኘውን ደስታ እንያዝ ። ነቢዩም፡- “በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።” (መዝ 97፥4) እንዳለው መልካም የሆኑትን ነገሮች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ቸርነት እዚህና በሚመጣው ሕይወት እንድናገኝ ። በእርሱና ከእርሱ ጋር ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ። ለዘላለሙ አሜን !