የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወርቅ ላበደረ

“ሰውዬው ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገረ”
/ዮሐ. 5፡15/፡፡
ሠላሳ ስምንት ዓመት በደዌ የደቀቀ ፣ ጥሩ ኑሮን አጥቶ ጥሩ ሞትን የተመኘ፣ በቀን ጨልሞበት በቁሙ ገደል የወደቀ ፣ ልቡ የተስፋ ጭላንጭል አጥቶ የሞትና የሕይወት ድንበሩ የጠፋበት ፣ … ያ ሰው ፤ የጥዋት ሬሣ የከሰዓት አንበሳ ፣ ብርቱው ጌታ ያበረታው ፣ ሕያው ጌታ የደረቀ አጥንቱን ያለመለመው … ያ እግዚአብሔር ይማርህ የሚባለው ፣ ምርቃቱ ደርሶ እግዚአብሔር ዛሬ የማረው ፣ ከደዌ እስር ቤት የወጣው ሰው … ፡፡ ጌታን ሊገድሉ ለሚፈልጉ አይሁድ ያዳነው ኢየሱስ መሆኑን ነገረ ፡፡ ያምኑበት ዘንድ አይደለም ፡፡ የገዳዮችን ወዳጅነት ላለማጣት ብሎ ይህን አደረገ ፡፡ ይህ የመስቀሉ አካል ነው ፡፡ የተፈወሱት አቁሳይ ፣ የዳኑት ገዳይ ፣ እጁን ያዩ የችንካር ምስማር አቀባይ መሆናቸው ይህ የመስቀል መንገድ ነው ፡፡ ይህ ሰው ያዳነውን ለአይሁድ አሳልፎ ሰጠ ፡፡ ወዳጅ ላይሆኑት ወዳጁን አጣ ፡፡ ፈውሱን ላይነጥቁት በከንቱ ፈራ ፡፡ በጌታ ድኖ እንደ አይሁድ ለመኖር ወሰነ፡፡
ጌታችን በተአምራት ከደዌው ሲያድነው የልቡ ዓመፃ ግን በተአምራት የሚድን አልነበረም ፡፡ የልብ ጠማማነት በንስሐ ብቻ ይቃናል ፡፡ ጌታችን የባሰ እንዳይገጥመው ከዚህ የበለጠ ኃጢአት አትሥራ ብሎት ነበር፡፡ የበለጠው ኃጢአት ድኖ እንዳልዳነ መኖር ፣ ተቀብሎ እንዳልተቀበለ ማማረር ፣  ሕመምን ከጌታ ጋር ፈውስን ከዓለም ጋር ማሳለፍ ነው ፡፡ ይህ ሰው ያዳነው ኢየሱስ መሆኑን የተናገረው በምስክርነት መንፈስ አይደለም ፡፡ ዛሬ ድኖ ዛሬውኑ ያዳነውን ረሳ ፡፡ ሰው ለመርሳት በጣም ቅርብ ነው ፡፡ የዛሬው ፈውስ ዘላለማዊ ፈውስ መሰለው ፡፡ ሰው ሲረሳ ይሉኝታና ኅሊና እንኳ የለውም ፡፡ “ታሞ የተነሣ እግዚአብሔርን ረሳ” የሚባለው እውነት ነው ፡፡
ጠላቶችን ለማስደሰት ወዳጆቻቸውን የሚገፉ የመጻጉዕ ወገኖች ናቸው፡፡ አይሁድን ለማትረፍ ኢየሱስን ማጣት የሚሰቅቅ ነው ፡፡ ፈዋሹ ትቶ አቁሳዩን ፣ ኢየሱስን ትቶ በርባንን መምረጥ ማስመሰል የሚያመጣው ጦስ ነው ፡፡አምላኩን የወጋ እኔን ይምረኛል ብሎ ማሰብ ፣ ከትልቁ የጀመረ እኔን ያፍረኛል ማለት ታሪክ አለማወቅ ነው ፡፡ ወዳጅነት ዘላቂ የሚሆነው በእውነት ላይ ሲመሠረት ነው ፡፡ ወዳጅ ለማትረፍ ወዳጅን ማጣት ከንቱ ስሌት ነው ፡፡ አዲስ ፍቅር የቆየውን ሲያስነሣ እንጂ ሲያስረሳ አደገኛ ነው ፡፡ ይህ በሽተኛ ከሠላሳ ስምንት ዓመት በሽታው ይልቅ የባሰ በሽታ በውስጡ ነበረ ፡፡ ክዳት ትልቅ በሽታ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ያጥፋህ እንጂ ይማርህ ያልተባለ በሽተኛ ቢኖር ከዳተኛ ነው ፡፡ እንኳን ከሰው ከእንስሳም ክዳት ያስወቅሳል ፡፡ ውሻና ድመትን የሚያነጻጽራቸው ታማኝነትና ክዳት ነው ፡፡ ያሸነፉ ለሚመስሉ ሲዘፍኑ መዋል አለመታደል ነው ፡፡ ሲገለባበጡ መኖር ክብረትን የሚያሳጣ ነው ፡፡ ከወዳጅ እየጎረሱ ጠላት ቤት መዋጥ የሚገርም ነው ፡፡ ሚስታቸው ያጠበችውን ጨርቅ ለብሰው ዝሙት ቤት የሚሄዱ ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለመናፍቃን መሳለቂያ የሚሰጡ ፣ ያጎረሳቸውን እጅ የሚነክሱ ፣ እነዚህ በርግጥም ታማሚ ናቸው ፡፡ የምንቀየማቸው በሽተኛ መሆናቸውን ስለማናውቅ ነው ፡፡ በተአምራት የሚድኑ በሽተኞች ግን አይደሉም ፡፡ ኃጢአት በንስሐና በረድኤተ መንፈስ ቅዱስ ብቻ ይድናል ፡፡
“ወርቅ ላበደረ ጠጠር ፣ እህል ላበደረ አፈር” የሚመልሱ ያልታደሉ ናቸው ፡፡ ቢቻል ከወርቁም ከእህሉም አትርፎ መመለስ ይገባል ፡፡ ወርቁም አጊጠውበታል ፣ ምስኪን ሁነው እንዳይታዩ ደምቀውበታል ፡፡ እህሉም ክፉ ቀንን አልፈውበታል ፡፡ እንግዳ ሸኝተውበታል ፡፡ በወርቁም በእህሉም ከማፈር ድነውበታል ፡፡ ስለዚህ ወርቅ ላበደረ ፣ ጠጠር እህልም ላበደረ አፈር ምላሹ አይደለም ፡፡ ውድ ለሰፈረ ርካሽ መስፈር ፣ ላከበረ ውርደት መመለስ ፣ ጠፍተው ለፈለገ መደበቅ ተገቢ አይደለም ፡፡ ፍቅርን ለሰጠ ፍቅርን መስጠት እንዴት ትልቅነት ነው ፡፡ ሆዳም ሰው ግን ፍቅር አያውቅም ፡፡ “ፍቅር አለቦታው አባ ጨጓሬ ነው” ይኮሰኩሰዋል ፣ ምቾት ያሳጣዋል ፡፡ ባርነትን ለለመደ ነጻነት ባርነት ነው ፡፡ ውርደትን ለለመደ ስድብ ቅቤ ነው፡፡
ማትረፍ ባይቻል ራሱኑ መመለስ አለመቻል ከሰውነት ክብር የሚያሳንስ ነው ፡፡ እንስሳ እንኳ ሲወዱት ይወዳል ፡፡ አንገት የተፈጠረው ጭንቅላትን ለመሸከም ብቻ ሳይሆን ዞሮ ለማየትም ነው ፡፡ በዚህ ዓለም ያጎረሱት መንከሱ አዲስ አይደለም ፡፡ ጌታችንን መጻጉዕና ይሁዳ ለአይሁድ አሳልፈው ሰጡት፡፡ ሆሳዕና ያለውም ሕዝብ ይሰቀል አለው ፡፡ ሆሳዕናና ይሰቀል ሩቅ ቢመስሉም ለብዙዎች ግን ቅርብ ናቸው ፡፡ ይህ መጻጉዕነት ይህ ይሁዳነት ይህ አይሁድነት በዛሬው ዘመን ዙፋን ዘርግቶ እየገዛን ነው ፡፡ በጠላቱ ከተጎዳ በወዳጁ የተጎዳ እየበዛ ነው ፡፡ ነገር ግን መልካም ማድረግ አያከስርም ፡፡ ያጽናኑትን ሰው ከጠላት ሰልፍ ውስጥ ማየት ያስደነግጣል ፡፡ ዳቦ የሰጡት የግዢ ተሳዳቢ ሲሆን ያሳዝናል ፡፡ ይሁዳ ጌታችን ያለበትን እንዳሳየ እንዲሁም ያለንበትን የሕይወት ውጣውረድ አውቀው ደክመዋል አሁን ያዟቸው ብለው የሚያስተኩሱ ሰዎችን ማሰብ ያስለቅሳል ፡፡ እንደ ባንዳ ወራሪን አገር እየመሩ የሚመጡ ፣ ለጠላት ተገዙ እያሉ የሚሰብኩትን ማሰብ ይከብዳል ፡፡ ይህ ሁሉ በክርስቶስ ሁኗል ፡፡ ጌታችን ይህን ሰው በማየት ፈውሱን አላቆመም ፡፡ ብዙዎችን ከዚህ በኋላ ሲፈውስ እናነባለን ፡፡ እርሱ ሰዎችን ወደ ንስሐ የሚመልሰው ቸርነቱን በማቆም ሳይሆን በመጨመር ነው ፡፡ ቸርነቱን ስላቆመ ቢመለሱ የተመለሱት ለጥቅማቸው ነው ፡፡ ቸርነቱን ስለጨመረ የሚመለሱ ግን የፍቅር ምርኮኞች ናቸው ፡፡
ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ አይሁድን ይሞግታል ፡- እነሆ ድንግል ትፀንሳለች አልክ ፤ አንተ አይሁዳዊ እስኪ ንገረኝ ?! ድንግል የወለደችው ይህ ማነው ? ለሄሮድስ እንዳስረዳኸው ለእኔም አስረዳኝ ፤ ለእኔስ አትነግረኝምን ይገድለው ዘንድ ለእርሱ ነገርከው እንጂ፤ እሰግድለት ዘንድ ለእኔ ለምን አትነግረኝም?…” ይላል /ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ ምዕ. 66፡25/፡፡ መጻጉዕም ያዳነው ኢየሱስ መሆኑን የተናገረው ያምኑት ዘንድ ሳይሆን ይገድሉት ዘንድ ነው ፡፡ ፈውስን ጨብጦ ፈዋሹን አሳልፎ መስጠት ፣ ጥቅሙን ይዞ ጠቃሚውን ማስገደል ምን ይባላል ? ፈዋሹ ካለ ፈውሱ ፣ ጠቃሚው ካለ ጥቅሙ ይቀጥላል ፡፡ ሰው አንድ ጊዜ በልቶ ዳግመኛ የሚራብ አይመስለውም ፡፡ በራሱ ላይ በሩን ይዘጋል ፡፡ የአገርን በረከት እየበሉ አገርን መጥላት ፣ በሕዝብ ላይ ነግሦ ሕዝብን ማጥላላት ፣ በሊቃውንት ተጠቅሞ ሊቃውንትን ማሳደድ ምን ይባላል ? የመጻጉዕ ልጅ መሆን ነው ፡፡
አባቶች ይህን የመጻጉዕ ጎዳና በክርስቶስ ላይ ከደረሱ የመስቀል ትግሎች አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ ፡፡ ይጸልያሉ ፡፡  ይህ ሰው ለምን እንዲህ አደረገ ? የፈወሰውን ፣ ሳያገግም አልጋ ተሸክመህ ሂድ ያለውን ፣ ለዘመናት ያመጸበትን እግሩን ታዛዥ ያደረገውን ፣ የገዛ አካሉ ከድቶት የተዛመደውን ጌታ ለምን አሳልፎ ሰጠ ? ሠላሳ ስምንት ዓመት በሰዎች ላይ ትልቅ ጥላቻ የያዘበት ፣ በአቅሙ ባይችልም በልቡ የተበቀለበት ፣ ለማንም ላለማዘን የወሰነበት ፣ ለእኔ ማን አዘነ ? ብሎ በሌሎች ሞት የሳቀበት ነው ፡፡ ሰዎች ላይ ያዳበረውን ማንነቱን አምላኩ ላይ አደረገው ፡፡ አምላክ ቢመጣ የተለየ አቀባበል እንደሚያደርጉ የሚያስቡ ሰዎች አሉ ፡፡ አቀባበሉ ግን ሰዎችን እንደሚቀበሉት ያለ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የሚመጣው በሰዎችም ተመስሎ ነውና ፡፡ ኃያልነቱን ለመግለጥ እንደ ጎልማሳ ፣ ጠቢብነቱን ለመግለጽ እንደ ሽማግሌ ይመጣል ፡፡ ስንት ዘመን አልፎን እንደሆነ አላውቅም ፡፡ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለማወቅ በድሃ መልክ ይመጣል ፡፡ ቤተ መንግሥት ሳይሆን በረት ተወልዷልና እርሱ በየት በኩል እንደሚመጣ የታወቀ ነው ፡፡
በክፉዎች ከመናደድ ይልቅ ለምን ክፉ ሆኑ ? ብለን ብናጠና መልካም ነው ፡፡ ምናልባት ክፉ ያደረግናቸው እኛ ልንሆን እንችላለን ፡፡ አስተዳደግ ፣ በልጅነት ዘመን የሚደርሱ ክፉ ገጠመኞች ፣ ፍቅርን ዘርቶ ጥላቻን ማጨድ ብዙዎችን ጨካኝ አድርጎ ይቀርጻዋል ፡፡ በዓለም ላይ ሁለት ዓይነት ከሃዲዎች አሉ ፡፡ አስተማሪ አጥተው የካዱና የአንዳንድ ክርስቲያኖችን ክፋት አይተው የካዱ ናቸው ፡፡ አስተማሪ አጥተው የካዱ ቅኖች ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ እኛን አይተው የካዱ ግን በቀለኞች ናቸው ፡፡ ዲዮቅልጢያኖስ በጭካኔው የታወቀ ንጉሥ ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከነ ተከታዮቻቸው የደመሰሰ ነው ፡፡ ይህ ሰው ግን ታማኝና ቅን የቤተ ክርስቲያን ሰው ነበረ ፡፡ ከአንድ መነኩሴ ታማኝነትን ቢያጣ እንዲህ ክፉ ሆነ ፡፡ የሚነገረው ግን ስለ ዲዮቅልጢያኖስ እንጂ ዲዮቅልጢያኖስን ስላከፋው ሰው አይደለም ፡፡ በሰዎች ምላሽ ምክንያት ክፉ ስንሆን አምላክን እንገፋዋለን ፡፡ “ክፉዎች ይጉዱህ እንጂ ክፉ አያድርጉህ” የሚባለውን የትግርኛ አባባል አስቡ ፡፡ መልኩን አጥቶ ከሞተ ከነመልኩ የሞተ ኀዘንን ይቀንሳል ፡፡
ወርቅ ላበደረ ጠጠር መመለስ በእውነት አይገባም ፡፡ ያ ወርቅ ያጌጡበት ፣ የደመቁበት፣ በሰርግ በግብዣ አንቱ የተባሉበት ነው ፡፡ ይህንን ወርቅ ላበደረ ጠጠር ፣ ማጌጫ ለሰጠ መፈንከቻ ድንጋይ አይሰጥም ፡፡ ይህ የመንፈሳዊነት ጥያቄ ሳይሆን የሰብአዊነት ጥያቄ ነው ፡፡ የበላንበትን ያበላንበትን ወዳጅ ፣ ያወቅንበትን የታወቅንበትን መምህር ፣ የተፈወስንበትን የፈወስንበትን ረቡኒ አሳልፎ መስጠት ራስን እንደ መግደል ይቆጠራል ፡፡ “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኰነነኝ” ይባላል ፡፡ ለእግዚአብሔር የተነገረ ሳይሆን ለሰው የተነገረ ነው ፡፡ ጥቅሙ ቀርቶ ባልጎዳኝ ፣ ክብሩ ቀርቶ ባላዋረደኝ ማለት ነው ፡፡ ከወደቀው የሰው ባሕርይ ውስጥ መልካም ነገር ሳይሆን የተሻለ ክፉ እየተፈለገ ነው ፡፡ ይህ ባሕርይ ግን በክርስቶስ ተነሥቷና ወርቅ ላበደረን ጠጠር ፣ እህል ላበደረ አፈር መመለስ አይገባንም ፡፡ እኛስ እንዴት ነን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ