የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ልጅህ በሕይወት አለ

“ኢየሱስም፦ ሂድ፤ ልጅህ በሕይወት አለ አለው። ሰውዬውም ኢየሱስ የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ” /ዮሐ. 4፥50/።
በሞት ድንበር ላይ ቆሞ ሕይወትን የሚያውጅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ያ የንጉሥ ቤት ሹም ከጭንቀት የተነሣ ዓይኖቹ ፈዝዘው ፣ ጆሮዎቹ ደንቊረው ነበር ። የሚታየው ችግሩ ፣ የሚሰማውም የልጁ የጣር ድምፅ ብቻ ነበር ። የቤቱ ችግር እስከ አደባባይ ተከትሎት ነበር ። ነህምያ በባቢሎን ምድር የንጉሥ ጠጅ አሳላፊ ነበር ። የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስ ፣ የሕዝቡም መላገጫ መሆን ልቡን ሰብሮት ነበርና በኀዘን ፊት የቀደመ ሥራውን በንጉሥ ፊት ሲሠራ ንጉሡ አንድ ነገር ጠረጠረ ። “ንጉሡም፡- ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኀዘን ነው እንጂ ሌላ ነገር አይደለም” አለው /ነህ. 2፥2/ ። ይህም የቅፍርናሆም ሹም በንጉሡ ፊት ሲቀርብ እንዲህ ተብሎ ይሆናል ። ሊደብቀው የማይችለው የልብ መሰበር ገጥሞት ነበር ። እንዲህ በተጨነቀ ሰዓት ጌታችን ደረሰ ። እርሱ ብቻ ትክክለኛውን ሰዓት ያውቃል ። አልፈለጉኝም ብሎ አይቀርም ፣ አስፈልጋቸዋለሁ ብሎ ይመጣል ። ዛሬ ካልፈለጉን አንፈልግም ። አስፈልጋቸው ይሆናል ብለን መሄድን መለማመድ አለብን ። በዚህ ዓለም ላይ የምኖረው ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ነውና ። እውነተኛ ደስታን የሚሰጠን ለሌሎች የኖርነው እንጂ ለራሳችን ያደረግነው አይደለም ።
ጌታችን ግን ከነገሩ ተቃራኒ የሆነ ነገር ነገረው ። ሰውዬው ስለ ሞት ያወራል ። ጌታችን ግን ስለ ሕይወት ነገረው ። ሞትን በሕይወት መለወጥ የእርሱ ሥልጣን ነው ። ልጅህ በሕይወት አለ ። ጌታችን ሳይዳስስ ፣ ሳይቀባ በቃሉ ሥልጣን ፣ ምሉእ በኩለሄ በሆነው ጠባዩ ነገረው ። ሹሙም ጌታችን የነገረውን ቃል አምኖ ሄደ ። ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ አብዛኛዎቹ የሚያጣጥር ነገር በቤታቸው አጋድመው የመጡ ናቸው ። የሚወዱት ከሞት ጋር ተፋጦባቸው በጭንቀት እያለከለኩ የሚደርሱ ናቸው ። እግዚአብሔር በቃሉ አበርትቶ ፣ እንደ ጀንበር የጠለቀውን ፈገግታቸውን አብርቶ ፣ የዛለውን ጉልበታቸውን አድሶ በሰላም ይመልሳቸዋል ። የበላይ በመሰላቸው ችግር ላይ እግዚአብሔር የበላይ መሆኑን አውጀው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ ። የእግዚአብሔር ቃል ከነገሩ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ይናገራል ። ዛሬን ሳይሆን ነገን ያያል ። ችግሩን ሳይሆን እግዚአብሔርን ያገንናል ። ጉዳዩን ብቻ ሳይሆን ሰውዬውንም ይለውጣል ። የሚለመንለትን ሰው ብቻ ሳይሆን ማላጁንም ይባርካል ። ስለ ሌሎች መጸለይ ለራስ እጥፍ መቀበል ነው ። በሌሎችም መፍረድ በራስ ላይ ድርብ ፈተና ማምጣት ነው ።
ይህ ሰው እንደ መጣበት ስሜት አልተመለሰም ። ሌላ ሰው ሁኖ ተመለሰ ። የልጁን መዳን በእምነት ተቀበለ ። ጌታችን የእሳት ላንቃ ነው ። በምን ይያዛል ? መያዣው ቃሉ ነው ። ጌታችን የነገረውን ቃል እንደ ተፈጸመ አድርጎ ተመለሰ ። ቃሉ ቀብድ አይደለም ። ሙሉ ዋስትና ነው ። እግዚአብሔር ያጽናናል ። የኀዘንን ማቅ ይቀድዳል ። የጠቆረውን ፊት የደስታ ዘይት ይቀባል ። ከአመድ አንሥቶ ክብር ያለብሳል ። በምንም መንገድ ወደ እግዚአብሔር የመጣ በመጣበት ስሜት አይመለስም ።
“እርሱም ሲወርድ ሳለ ባሮቹ ተገናኙትና ። ብላቴናህ በሕይወት አለ ብለው ነገሩት” /ዮሐ. 4፥51/። እግዚአብሔር እንደ ቃሉ ነው ። ስፍራ ሳይርቀው የሚረዳ ፣ ዘመን ሳያልፍበት የሚያጽናና ነው ። የዚህ ሹም እምነቱ አደገ ። ጌታን ውረድና አድንልኝ ብሎት ነበር ። አሁን ግን ጌታችን በቃሉ ሥልጣን እንደሚሠራ አመነ ። ጌታችን በሩቅ ሁኖ ቃል ይናገራል ፣ ሹሙም ቃሉን በእምነት ይቀበላል ። በሽተኛውን የከበቡት ወዳጆች ደግሞ ሲድን ያያሉ ። እነርሱ በሽታው በራሱ እንደ ለቀቀው ያስቡ ይሆናል ። ሹሙ ግን የጌታ ቃል የቤቱን ጨለማ እንዳበራ ያውቃል ። እነርሱ የልጁን መዳን በዓይናቸው አይተዋል ፣ እርሱ ግን በእምነት አይቷል ። ያላወቀ ፣ ያልሰማ ፣ ያልተቀበለ መስሏቸው በሩቅ ሲያዩት የልጁን በሕይወት መኖር ሊያበስሩት መጡ ። እርሱ ሊያበስራቸው ይመጣል ፣ እነርሱም ሊያበስሩት ይመጣሉ ። እርሱ በማን እንደ ዳነ ያውቃል ፣ እነርሱ መዳኑን እንጂ በማን ሥልጣን እንደ ዳነ አያውቁም ። ብላቴናህ በሕይወት አለ ሲሉት ከመደሰት በላይ ያዳነለትን አምላክ ማሰብ ጀመረ ። ከመዳን እሴቶች በላይ ያዳነንን ማሰብ ያስደስታል ። ለዚህ ነው ጌታችን አጋንንት በስምህ ተገዙልን ብለው ሲደሰቱ “መናፍስት ስለ ተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፥ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ” ያለው /ሉቃ. 10፥20/ ። በሰማያት መጻፍ ማለት በልበ ሥላሴ መታወቅ ማለት ነው ።
“እርሱም በጎ የሆነበትን ሰዓት ጠየቃቸው፤ እነርሱም፦ ትናንት በሰባት ሰዓት ንዳዱ ለቀቀው አሉት” /ዮሐ. 4፥52/። ይህ ሰው ልጅህ በሕይወት አለ ሲሉት በደስታ ከመፈንጠዝ የአዳኙን ውለታ እንዳይጠፋ ፈለገ ። በጎ የሆነበት ሰዓት አይጠየቅም ። እርሱ ግን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥልጣናዊ ቃሎች ለመመስከርና በልቡም ለማክበር ሰዓቱን ጠየቀ ። የማዳኑን ምስጋና ለባለቤቱ ለመስጠት ጥንቃቄ አደረገ ። መዳንን ከአዳኙ መነጠል ቀማኛ መሆን ነው ።
“አባቱም ኢየሱስ፦ ልጅህ በሕይወት አለ ባለው በዚያ ሰዓት እንደ ሆነ አወቀ፤ እርሱም ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር አመነ” /ዮሐ. 4፥53/። ይህ ሰው ሰዓቱን ከጠየቀ በኋላ ይህ የሆነው የሥልጣን ቃሉን ክርስቶስ በተናገረበት ቅጽበት ነው ። ጊዜና ቦታ ሳይገድበው የሚሠራ ኃይለኛ ነው በማለት መስበክ ቀጠለ ። ልጄን ልመልከት ከማለት ያዳነውን አምላክ እንዲመለከቱ መናገር ጀመረ ። እርሱ የልጁን ፈውስ በእምነት ተቀብሎ መጥቷል ። እነርሱም ያዳነውን ጌታ በእምነት ማየት ጀመሩ ። አዳኙንም መዳንንም የምንቀበለው በእምነት ነው ። በእምነት ካልተቀበልን ያንስብናል ። የታመመው ልጅ ምክንያት ሁኖ ከክርስቶስ ጋር አገናኘ ። የታመሙብን ነገሮች ከእግዚአብሔር ጋር የማገናኘት አቅማቸው ሰፊ ነው ። እግዚአብሔር ነገርን ሁሉ ለበጎ ይለውጣል ። በሥጋ የታመመው ልጅ የነፍስን ሕመም ማስታወሻ ሆነ ። እርሱ ድኖ አልቀረም ፣ መላው ቤተሰብ ደግሞ ከደዌ ነፍስ ዳነ ። ካለማመን ተላቀቀ ። ጌታችን ግዛትን ያሰፋል ። ከቤተሰቡ አንዱን በፍቅር ይነካል ። መላ ቤተሰቡን ይወርሳል ።
“ይህም ደግሞ ኢየሱስ ከይሁዳ ወደ ገሊላ መጥቶ ያደረገው ሁለተኛ ምልክት ነው” /ዮሐ. 4፥54/ ። ወንጌላዊው ጠንቃቃ ነው ። ይህን ተአምራት ምልክት ይለዋል ። የመጀመሪያው ምልክት የቃና ዘገሊላው ተአምር ሲሆን ሁለተኛው ምልክት ደግሞ የዚህ ብላቴና መፈወስ ነው ። ምልክት ዓላማው ወደ ዋናው ማድረስ እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም ። እውነተኛውንና በጌታችን የተፈጸመውን ተአምራት እንኳ ምልክት አለው ። ዛሬ ሐሰተኛ ተአምራትን የሚያመልኩትን ሰዎች ምን ይላቸው ይሆን ? እውነተኛ ተአምር ቢፈጸም እንኳ እርሱም ትልቅ መዳን እንዳለ ምልክት ነው ። ሰጪውን የማያሳይ ስጦታ መባከኑ አይቀርም ። አንድ ውድ ስጦታ እቤታችን ተቀምጦ ብናገኘው ከመጠቀም ማን ነው ያመጣው እንላለን ? ያመጣውን ካላወቅነው ደስታችን ሙሉ አይደለም ። የዚያን ሰው ፍቅር ስናስብ ስጦታው እያስደሰተን ይመጣል ። ከሰጪው የተነጠለ ስጦታ የሰረቁት ያህል ያሳቅቃል።
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ትርጓሜ ተፈጸመ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ