October 9, 2021 by ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
እውነትን በፍቅር እንያዝ
“ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤” ኤፌ. 4፡15።
“ስትጣሉ ለእርቅ ፣ ስትበሉ ለውኃ ቦታ ትታችሁ” ይባላል ። እስከ መጨረሻው መነጋገር ፣ እንዳይድን አድርጎ ማቍሰል ፣ እንዳይነሣ አድርጎ መግደል ዘመን የወለደው የእልህ ጠባያችን ሆኗል ። አሳብን ስላላዳበርን ፣ አሳብን ለማዳበር የሚረዱ መጻሕፍትን እንደ ደመኞቻችን ስለቆጠርን ፣ ሊያስተምሩ የሚችሉ መምህራንን ስም ሰጥተን ስላባረርን ጠብና ጦር ሥራችን ሆኗል ። አሳብና አሳብ ቢፋጩ ትውልድ ብርሃን ያይ ፣ አገርም ያድግ ነበረ ። አገርም የግል ሳይሆን የጋራ መሆንዋ ይታመንና ሌላውም ይምራ ፣ ይናገር ተብሎ ይፈቀድለት ነበር ። አሳብ የሌለው ሰው ድንጋይ የድል መሣሪያው ነው ። በአሳብ ሁሉን ማትረፍ ሲቻል በድንጋይ ግን ደጉ አቤልን ማጣት ፣ ተቅበዝባዥ ቃየንን ማትረፍ ይመጣል ። መጻሕፍት የሚቃጠሉበት ዘመን አገርም ይቃጠላል ። መምህራን የሚናቁበት ዘመን ትውልድ ፍሬኑ የተበጠሰ መኪና ይሆናል ። አዋቂዎች ዱዳ ሲደረጉ ጮሌዎች በመሃይም ቃሌ እያሉ ብዙዎችን ከኋላቸው ያስከትታሉ ። ጋኖች ሲያልቁ ምንቸቶች ጋን ይሆናሉ ። አገር ሲያረጅ ጃርት እያበቀለ ይመጣል ። መናገር መቻል ቁምነገር ማውራት አይደለም ። መጻፍ መቻልም የእውነት ደራሲ አያሰኝም ። ብዙ ተከታይም ዝንጀሮ አመለካከታችንን አያቆነጅም ። እንደ ጦጣ ታስሮ መዝፈን ራስን ከማታለል ውጭ አይሆንም ። ጊዜ እስኪያገኝ ሁሉም ጨዋ ይመስላል ። “የእንጦጦ መምህር ቢናገር ባመት ፣ ያውም እሬት” እንዲሉ ከርመው መናገር የጀመሩ እሬታቸው አገርን እያንገሸገሸ መሆኑን ስናይ ያሳዝናል ።
“የማይደርሱበትን አያኩም” የሚባለው ተረስቶ ሊሰሙን የማይችሉትን ሰዎች ስንሳደብ መዋል ፣ የጻፍነውን መልሰን መልሰን ራሳችን ስናነበው ፣ የተናገርነውን መልሰን መልሰን ራሳችን ስንሰማው መዋላችን አስደናቂ ነው ። “ተንጋለው ቢተፉ ፣ መልሶ ባፉ” እንዲሉ ያስተማሩንን ፣ የክህነት አባቶቻችንን መስደብ ራስን ከማርከስ ውጭ ምንም ትርፍ የለውም ። ደግ መናገር ቢያቅተን ዝምታን ገንዘብ ብናደርግ መልካም ነበር ። ወደ ላይ እያዳጠን ብልሹ ወላጆቻችንን ደብቀን የመንፈስ አባቶቻችንን እያዋረድን መሆኑ ይገርማል ። የዕድሜም የእውቀትም ድኁር/ቅንጭር መሆናችንን ከማስገመት ውጭ ምንም ለውጥ አናመጣም ።
ምድራችንን እየጎዳት ያለው ሁሉን እናውቃለን የሚሉ ሰዎች መፈጠራቸው ፣ አለመናገር አለመኖር የሚመስላቸው ሰዎች መከሰታቸው ፣ ሁሉም ተንታኝ ሁኖ ባለሙያዎችን ማስደንገጣቸው ፣ ያወቁ ሰዎች ያላወቁ ሰዎች የማይሠሩትን ስህተት መፈጸማቸው ፣ ጆሮ ተቆርጦ መላ ሰውነት አፍ ብቻ መሆኑ ነው ። ቦታ ተለዋውጦ ምሁር መሃይም ፣ መሃይም ምሁር መባሉ ፣ ፖለቲከኛ ዕጣን ዕጣን ፣ ካህን ፖለቲካ ፖለቲካ መሽተቱ ፣ ወንበሮች ባዶ ሆነው ውሳኔ የሚሰጥ መታጣቱ ዘመኑን እያከፋው መሆኑ በግልጽ ይታያል ። አንድ ሰው መምራት ትቶ ሚሊየኖች መሪ ሲሆኑ አሟሟት እንኳ ክብር እያጣ ይመጣል ። ሰዎቹ የማይገቡ/የማይመጥኑ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል ፣ የያዙት ሥልጣን ግን ሐዋርያዊና ክርስቶሳዊ ነውና መንበርን መዳፈር ዋጋ ያስከፍላል ። የስድብ ዕድርተኞች መጨረሻ እርስ በርስ ይጠፋፋሉ ። ዛሬ እሰይ የእኔ ሽታ ፣ እሰይ የእኔ ሽታ እየተባባሉ በመጥፎ ጠረን ይወዳደራሉ ፣ በስድብ ቁመት ይለካካሉ ። ተቃቅፈው የሚሄዱ ሁለት ያልታጠቡ ሰዎች እሰይ የእኔ ሽታ እሰይ የእኔ ሽታ ይባባላሉ ይባላል ። አንዳችን ለአንዳችን ክፋት እውቅና የምንሰጠው እስከ ጊዜው ነው ። ክፉ ነገር ያልቃልና በቅርቡ እናፍራለን ። ትላንት ለውሸት ያጥኑ የነበሩ ዛሬ መግቢያ ሲያጡ ፣ ነግ ለእኔም ይህ መለኮታዊ ብይን ይሠራል ብለን መጠንቀቅ ይገባን ነበር ።
እውነት መነገር አለበት ። ሊነገር የሚገባው እውነት ምንድነው ? ማለት አለብን ። ሰይጣን እውነትን ሊናገር ይችላል ። ክርስቶስን ከአይሁድ ይልቅ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ያለው ሰይጣን ነው ። ምስክርነቱ ግን መገዛት የለበትምና እንደ እውነተኛ አይጠቀስም ። ሰይጣን ኃጢአት ስንሠራ ይህን ኃጢአት ሠርተሃል ይለናል ። ዓላማው ግን በክስ ተስፋ ማስቆረጥ በመሆኑ ከእውነት አይቆጠርም ። በዚህ ዓለም ላይ ያለው ትልቅ እውነት ፣ ሰው ሁሉ ሊቀበለው የሚገባው ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች መሞቱ ነው ። “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው ፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ ፤” 1ጢሞ. 1፡15 ። ካም የአባቱን ሐፍረት ማየቱና መናገሩ እውነት ነበር ። ነገር ግን በልጅነቱ የእርሱን ዕራቁትነት የሰወረውን አባቱን ዛሬ ሊሰውረው ይገባ ነበር ። በዚህ ምክንያት ተረገመ ። ኖኅ ጠጥቶ መስከሩም ፣ መራቆቱም እውነት ነው ። ካም ግን ሐቀኛ አልተባለም ። የካም ጠባይ ዛሬም አልለቅቅ ብሎን የማጋለጥ እውነት እንጂ የመሰወር ጻድቅነት አልተገኘብንምና ወዮልን ። ዘፍ. 9 ፡ 22 ፤ ማቴ. 1 ፡ 19 ።
ሌሎችን ያዋረዱ ፣ መንፈሳዊ መምህራንን የነኩ ሁሉ በክብር አልኖሩም ፣ አልሞቱም ። የአንድ ሚኒስትር ውርደት እውነት ቢሆንም የመንግሥቱ ውርደት ነው ። የአንድ አገልጋይ ውርደትም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚሰደብበት ፣ ሊድኑ ያላቸው ወደ ኋላ የሚጋልቡበት መሰናክል ነውና በልባችን ይዘን ፣ በአፋችን ልንጸልይበት ይገባል ። የማይጸልዩ አፎች ምልክታቸው መሳደብ ነው ። እውነትን በፍቅር መያዝ ይገባል ። ክፍሉን የምናነበረው እውነትን በፍቅር መናገር ብለን ነው ። ነገር ግን እውነትን በፍቅር ራሳችን መያዝ ይገባናል ። የሰውዬው ውድቀቱ እውነት ነው ። በፍቅር የምንይዘው ግን፡- “ጌታ ሆይ ከእኔ ይልቅ የሚሻለው ወንድሜ ወድቋልና የእኔን ፍጻሜ አሳምርልኝ” ብለን ነው ። ካወራወራችን ጋር ሳይሆን ካያያዛችን ጋር መታገል አለብን ። የምንወረውረው በያዝንበት መጠን ነውና ። ያለ ፍቅር መገሠጽም ፣ ማስተማርም ተገቢ አይደለም ። ፍቅር የሌለው ነገር ሕይወት የማይሰጥ ደረቅ ነውና ። ለአንድ ሰው አንድ እውነት ከመናገራችን በፊት እንደምንወደው እርግጠኛ መሆን አለብን ። ለማይወዱት ሰው ክርስቶስን መስበክ አምላክን እንደ መሳደብ ነው ።
እውነት ያለ ፍቅር ከተያዘች ኃጢአት በምድር ላይ እንዲጨምር ታደርጋለች ። ፍቅርም ያለ እውነት ከተያዘች ዘላኖችን ታፈራለች ። እውነት ያለ ፍቅር ብስጭት ናት ፣ ፍቅርም ያለ እውነት ግዴለሽ ናት ። እውነት ያለ ፍቅር ደረቅ ዱላ ነው ፣ ፍቅርም ያለ እውነት የማይቆም እንግጫ /ቄጠማ/ ነው ። እውነትን በፍቅር ስንይዝ ለማነጽ እንናገራለን ፣ ለማዳን እንሮጣለን ፣ ኅብረትን ለመመሥረት እንተጋለን ። “እንጨት ካልነሡት እሳት አይጠፋምና ከማጋጋል ማስታረቅ ፣ ከጠብ ቃላት የፍቅር ድምፆች ያስፈልጋሉ ። እውነትን ያለ ፍቅር መያዝ መራርነትን ፣ እውነትን ያለ ፍቅር መናገር ሰባሪነትን ፣ እውነትን ያለ ፍቅር መኖር ገዳይነትን ያመጣል ።
እውነትን ፍቅር እንያዝ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 29 ቀን 2014 ዓ.ም.