የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የይሁዳ ሰው ስትሆን

“ስለዚህ ሳምራዊቲቱ፡- አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና” /ዮሐ. 4፥9/ ።
     ቀላሉ ነገር ከከበደ ከባዱ ነገር እንዴት ይከብደን ይሆን ? ቀላሉ ነገር ውኃ መስጠት ነው ። ቀላሉ ነገር ለሰዎች ፍቅርን መስጠት ነው ። ቀላሉ ነገር ሰዎችን በደማቅ ሰላምታ ሰላም ማለት ነው ። ቀላሉ ነገር ሲቀበሉ አመሰግናለሁ ማለት ፣ ሲወስዱ ማስፈቀድ ነው ። ቀላሉ ነገር ዛሬ ልንግባባ ካልቻልን እስከ ቀኑ በትዕግሥት መጠበቅ ነው ። ቀላሉ ነገር በእጃችን ያለውን የሌሎችን ድርሻ በደስታ መስጠት ነው ። ቀላሉ ነገር ያለፈውን መልካም ጊዜ ማሰብ ነው ። ቀላሉ ነገር መግባባት ካልቻሉ ላለመግባባት መግባባት ነው ። ቀላሉ ነገር እኛ ከተቀየምን ሌሎችን የጠብ ደቦኛ አለማድረግ ነው ። ቀላሉ ነገር እዚህ መኖር ካልቻልን እልፍ ማለት ነው ። ቀላሉ ነገር ማመስገን ቢያቅተን አለመራገም ነው ። ቀላሉ ነገር የሚወዱንን መውደድ መቻል ነው ። ቀላሉ ነገር ከብዶን ይሆን ? ሣንቲም የማይሞላ የውኃ ልመና ታሪካዊና እልፍ ገንዘብ የሚያስወጣ ጉዳይን ቀስቅሶ ይሆን ? ቀላል ነገሮች ካልተደረጉ ትልቅ ጉዳት ይዘው ይመጣሉ ። ቀላሉ ነገር ዛሬን መኖር ነው ። ዛሬን ለመኖር ከዐፄ ምንሊክ ጀምረን ለምን ቂም እንቆጥራለን? ስለ ሞቱት ወገኖች ያሉትን ለምን ዋጋ እናስከፍላለን ? ዛሬን ጥሩ ለማለት የሺህ ዓመት ታሪክን ለምን እንደመስሳለን ? ሁሉም ነገር እኔ ከመጣሁ ጀመረ ለማለት ለምን እንደፍራለን ? ለትላንት ዛሬን ከነሣነው ለዛሬ ነገን እንነሣዋለን ። ዛሬን ለመፋቀር የዘር ምክንያት ለምን እንፈልጋለን ? ዘረኝነት ቀላሉን ፍቅር ከባድ ፣ ከባዱን መግደል ቀላል ያደርገዋል ። ቀላሉ ከከበደን ፣ ከባዱ ይቀልብናል ። ዛሬ ህልውና የጀመረ ዘር አለ ወይ ? ዛሬ እንደ ተፈጠረ ግን ያንን ዘር ለምን ጠላነው ? ዘረኝነት አጥብቀው ካልተከላከሉት እያወገዙትም ይይዛል ። አንድ ሰው “ዘሮች ይለምልሙ ፣ ዘረኝነት ይውደም” ብሏል ።
ቀላሉ ነገር ለለማኝ ሣንቲም መስጠት ወይም እግዜር ይስጥልኝ ብሎ መሸኘት ነው ። ሆድ ዘርና ሃይማኖት የለውም ። ቁራሽ ለመስጠት ዘር መጠየቅ ለምንድነው ? እኛ የምናየው ወገኔ የምንለውን ሰው ነው ፤እግዚአብሔር ግን የሚያየው የፈጠረውን ሰው ነው ። እግዚአብሔር ጽንፈ ዓለሙን ያያል እኛ ቀበሌአችንን ብቻ እናያለን ። ዘረኝነትን በቤተ ክርስቲያን ለማውገዝ እንኳ ዘረኝነታችን ይይዘናል ። ከእኛ ጋር እየተጎሳቆሉ በዘራቸው ያገኙ ፣ የተደላደሉ የሚመስሉን ሰዎች አሉ ? በካንሰር እየማቀቁ ካንሰር ዘር ለይቶ በትንሹ የሚያምም የመሰሉን ሰዎች አሉ ። ከዓይናችን ግምታችንን እንዴት እናምናለን ? ቀላል ነገር ከብዶብናል ። ከባዱ ቀን ቢመጣ ምን ልንሆን ነው? ዘረኝነት ምክንያት የሌለው ጠብ መነሻ ፣ እጅግ አረመኔ የሚያደርግ ፣ ሰብእናን የሚነጥቅ ነው ። ዘረኝነትን ባራመድን ቊጥር ብዙ ዘረኞችን እናፈራለን ። ሌሎች ራስን መከላከል በሚመስል ስሜት ዘረኝነትን ይፈጽማሉ ።
“ምክንያቱ ትንሽ በሆነ መጠን ጠቡ ትልቅ ነው” ይባላል ። የማይበርድ ጠብ ፣ የተጋጋለ ጉዳይ ፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ትርምስ ከገጠማችሁ ምክንያቱ ትንሽ ነው ። ቢያወሩትና ቢደረስበት የሚያሳፍር ነው ። ስለዚህ በትልቅ ጠብ ምክንያቱን ለመሸፈን ሙከራ ይደረጋል ።
ቀላል አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ከባድ ችግር ያመጣሉ ። ትልቅ የሆኑ የሚመስላቸው ጠባቸውን ትልቅ ባደረጉት መጠን ነው ። አንድ እናት ፡- “ልጄ ከጅል ጠብ ይጠብቅህ ፣ የጅል ጠብ ማለቂያ የለውም” ብለው መርቀውኛል ። በጣም አከበርኳቸው ። እኒህ እናት ለምነው አዳሪ ናቸው ። ጥበብ ግን በዝቶላቸዋል ። የጅል ጠብን እኔ በኑሮዬ በብዛት አይቻለሁ ። የማይረሱ ፣ እኔ ጠልቼሃለሁ ዓለም ሁሉ ይጥላህ የሚሉ ፣ ለእኔ ካልሆነ ይሙት በቃ ብለው በአሳብ የሚበይኑ ጅሎች ሞልተዋል ። ያልተማረ ሰውን ተንኮል የሚፈታው የለም ። አእምሮአቸው ልማት የራቀው ሰዎች ምንም የሚከለክላቸው ሕግ የለምና ተንኮላቸው ገደብ የለውም ። “እንዴት እኔ ይህን አደርጋለሁ ?” ለማለት እውቀት ፣ አስተዳደግና መንፈሳዊነት ይጠይቃል ። የሰው ልጅ አራት ቀንዶች አሉት ። አራተኛ ከባድ ነው ። እነዚህን ቀንዶች የሚቆርጥለት አንደኛ፡- ቤተሰቡ ፣ ሁለተኛ፡- ትምህርት ቤት ፣ ሦስተኛ፡- ኑሮው ነው ። አራተኛውን ቀንድ የሚቆርጥለት የእግዚአብሔር ቃል ነው ። አራተኛው ቀንድ የአስተሳሰብ ብልሹነት ነው ።
ሥራ ያጣ ሰው ነገር ሥራው ይሆናል ። ስለ ራሱ ያለው ግምት የወረደበት ሰው ሌላውን ሲያንቋሽሽ ይኖራል ። ምንም ቢሆን ጠብን ከትልቅ ሰው ጋር ማድረግ ያሻላል ። ለክብሩ ሲል ክብራችንን ይጠብቃል ።
ዘረኝነት
   “ስለዚህ ሳምራዊቲቱ፡- አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና” /ዮሐ. 4፥9/ ። ስለ ሰው እየተናገረች ቢሆን ምንም አይደለም ። የምትናገረው ስለ ይሁዳ ሰውና ስለ ሳምራዊ ሰው ነው ። ቀላል የሆነው የውኃ ጥያቄ ከባድ የሆነውን የ700 ዓመታት ግጭት ቀሰቀሰ ። ሳምራውያንና አይሁዳውያን የተከፋፉበት የዘመን ልክ ይህን ያህል ነው ። ዘረኝነቱ መቅደስ ከመለየት ፣ በአንድ መንገድ ካለመሄድ ፣ ሳምራዊ አታሳየኝ ከማለት ፣ ውኃ ከመከልከል ደረሰ ። በእርግጥ ይህች ሴት ያቀረበችው ስስ የሆነ የዘረኝነት ጥያቄ ቢሆንም አሳቧ መደነቅ ነው ። ክፉውን ጠግባ ስለነበረ  መልካምነት ያስደነግጣት ጀመረ ።
መጽሐፍ ቅዱስ ዘረኝነትን የሚዋጋ መጽሐፍ ነው ። ዘረኝነትን የሚዋጋው ቢያንስ በአራት አሳቦች ነው ፡-
1-  ሁላችንም በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥረናል /ዘፍ. 1፥26/።
2-  ሁላችንም ክርስቶስ ሞቶልናል /ዮሐ. 3፥16/ ።
3-  ሁላችንም አንድ አባት አብ አለን /1ቆሮ. 8፥6፤ ሚል .2፥10/ ።
4-  ከአንድ ኅብስትና ጽዋ ማለት ከጌታ ሥጋና ደም ተካፍለናል /1ቆሮ .10፥17/።
እግዚአብሔር በመልኩ የፈጠረው ምዕራባውያንን ወይም ምሥራቃውያንን አይደለም ። መላውን የሰው ዘር ነው ። አውሮፓውያን በቅኝ ግዛት አፍሪካን እንዲወርሩ ያደረገው አንዱ ነገር የዘር የበላይነትን ያረጋገጠ ሳይንሳዊ መረጃ አለን የሚል አስተሳሰብ ነበር ። ሰው ከዝንጀሮ መጣ የሚለው አስተሳሰብም አፍሪካን እንዲወርሩ መነሻ ሁኗል ። እኛ አሰልጥነን ሰው እናደርጋቸዋለን ወደሚል አስተሳሰብ መርቷቸዋል ። ይህንን ክርስቲያን ነን የሚሉ አገሮች መፈጸማቸው ያሳዝናል ። ዘረኝነት የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት ከማያምን አስተሳሰብ እንደ መጣ በዚህ ማየት እንችላለን ። ጣሊያንም ኢትዮጵያን ሲወርር አንድ የተደበቀ ፍላጎቱ የአውሮፓውያን ስሜት ነበረ ። አይሁዳውያንን ከአውሮፓ ምድር ጠራርጎ ለማስወጣትና ለእነርሱ በሁሉም ነገር ከኢትዮጵያ የተሻለ ምቹ አገር የለም በማለት ኢትዮጵያ ለማስፈር ነበር ።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፣ የሳይንስና ፣ የባሕል ድርጅት /ዩኒስኮ/ “ሁሉም የሰው ልጆች ዝርያቸው አንድ ሲሆን ሁሉም ከአንድ ግንድ የመጡ ናቸው” በማለት ግጭትን በሚያወግዘው አንቀጹ ይገልጻል ። የእግዚአብሔር ቃልም ፡- “…እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” ይላል /የሐዋ. 17፥26/። እኛ የአዳም ዘሮች በኋላም የኖኅ የልጅ ልጆች ነን ። የሰው ዘር መነሻ አዳም ነው ። ያ የአዳም ትውልድ በኖኅ ዘመን በኃጢአት ምክንያት ከተደመሰሰ በኋላ ከሦስቱ ልጆቹ ከሴም ፣ ከካምና ከያፌት የሰው ዘር እንደገና ተስፋፋ ። ከእነዚህ ሦስት ነገዶች የወጣ ወገን የለም ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አድራሻ አድርጎ የመጣው መላውን የሰው ዘር ነው ። እርሱ ዘረኝነትን በጽንሰቱ ፣ በትምህርቱ ፣ በኑሮውና በሞቱ ተቃወመ። ደቀ መዛሙርቱን ወደ ዓለም ሁሉ በመላክም የሰው ዘር አንድ መሆኑን መሰከረ ።
አንድ እጅ እንደ ፈጠረን ራሳችን ምስክሮች ነን ። ምሥራቅና ምዕራብ ብለን እንናናቃለን ። ምሥራቃውያንና ምዕራባውያንን የፈጠረ ሁለት አምላክ ቢሆን ኑሮ አማልክት ይፎካከራሉና የምሥራቁ ዓይንን ከፊት ሲሠራ የምዕራቡ አምላክ ከጎን ይሠራ ነበር ። አንድ እጅ እንዳበጀን በእውነት ራሳችን ምስክር ነን ። የአንድ አባት ልጆች ከሆንን በርግጥም ወንድማማች ነን ። ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ “አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፡- አባት ብላችሁ አትጥሩ” ያለው ወንድማማች መሆናችንን ለመግለጥ ነው ። የበላይና የበታች አስተሳሰብ ምንጩ ወንድማማችነትን አለመቀበል ደግሞም በእግዚአብሔር አባትነት ያለማመን ውጤት መሆኑን እየተናገረ ነው /ማቴ. 23፥9/። ዛሬ አባ ብለን አባቶችን ስለምንጠራ ይህን ጥቅስ የሚጠቅሱ አሉ ። ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን  “እውነተኛ ልጄ”እንዳለው ይዘነጋሉ /1ጢሞ. 1፥1/። ዳግመኛም ሐዋርያው ፡- “እንደምወዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልገሥጻችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ይህን አልጽፍም። በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና” ያለውን ማየት መልካም ነው /1ቆሮ . 4፥14-15/።
የጌታ ሥጋና ደምም ከአንድ ኅብስትና ከአንድ ጽዋ በየዕለቱ የሚፈተተው ኅብረትን ለመግለጥ ነው ። ይልቁንም የጌታን ሥጋና ደም የወሰዱ ምእመናን ከዘረኝነት መዳን በጣም ያስፈልጋቸዋል ።
የዘረኝነት አንዱ ምንጭ አስተዳደግ ነው ። የቀደሙት ናዚዎች የአስተዳደጋቸው ውጤት ነበሩ ። ዛሬም በጀርመን ዘረኝነትን የሚያሳፋፉ ወጣቶች ናቸው ። የቀድሞቹ ዘረኞች ለልጆቻቸው ይህን ስላወረሱ ነው ። በአንድ እስራኤላዊ ቤት ልጃቸውን ምግብ አሳይተው ይደብቁበትና “ማን ወሰደው?” ሲል “ፍልስጤማዊው” ይሉታል ። በአንድ ፍልስጤማዊ ቤትም የአይሁዳዊ ፎቶ ተሰቅሎ በውኃ ሽጉጥ ሕጻኑ እንዲተኩስ ይደረጋል ይባላል ። በእኛም አገር በዘረኝነት መጋደል ፣ ትዳር መፍታት ታይቷል ።
አንበሳ ከአንበሳ ጋር የሚያብረው በአንበሳነቱ እንጂ ሰሜንና ደቡብ በመሆኑ አይደለም ። የላም መንጋ አብሮ የሚጓዘው በቀለሙ ሳይሆን በላምነቱ ነው ። እኛንም የሚያስተሳስረን ሰውነታችን ሊሆን ይገባዋል ። አንድ ሥዕል ላይ አይጥና ድመት ተቃቅፈው ይታያሉ ። ከሥር እንዲህ የሚል ጽሑፍ ሰፍሯል፡- “እኛስ ተስማምተን መኖር ቻልን እናንተስ?”
 ዘረኝነት በመጨረሻው ዘመን ላይ በጣም ይገንናል ። ምክንያቱም አውሬው አንዱ ተግባሩ የሰውን ልጅ በዘር ፣ በቋንቋ መለያየት ነው /ራእ. 13፥7/ ። ዘረኝነት መሰልጠን ሳይሆን ወደ ፈርዖን ዘመን መመለስ ነው ። ፈርዖን የዘር ማጥፋት ወንጀል በእስራኤል ላይ ፈጽሟል ። ዘረኝነት ሰዎችን በውሻ እንዳስበላ በደቡብ አፍሪካ አይተናል ። ዛሬም ዘረኝነትን አሸንፌአለሁ የምትለዋና ነጻነትን ካወጅሁ ሁለት አሥርት ዓመታትን አሳለፍኩ በምትለው ደቡብ አፍሪካ ዘረኝነት አለ ። በፈረንጆቹ 2016 በፕሪቶሪያ በሚገኝ በአንድ የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ፀጉራቸውን ከማጎፈር እንዲያለሰልሱ ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይናገሩ የትምህርት ቤቱ ዘረኛ ፖሊስ በማዘዙ ተቃውሞ ተነሥቷል ። በአውሮፓ በኳስ ተጫዋቾች ላይ የሚደርሰው የዘረኝነት ስድብ ብዙ ነው ። ሁሉም ነገር ከእኛ በቀለ ለማለት ፀረ ሴማዊነትን የሚያራምዱ አውሮፓውያን የዚህ በሽታ ተጠቂ ናቸው ። በአገራችንም ይህን ዘረኝነት እየወሰደን እንደ ፈረንጆቹ መዘመር ፣ ማመን ፣ መልበስ ፣ መናገር ፣ እኔ ሁሉም ነገሬ እንደ ፈረንጅ ነው የሚል አስተሳሰብ እየተስፋፋ ነው ። የእኛ ደግሞ ወዴት እንደምንሄድ አቅጣጫ የለውም ። ዘረኝነት የሌላውን ዘር በመጥላት የተመሠረተ እንጂ የራስን ዘር መውደድ አይደለም ። ዘረኞች ሁሉ ፣ አገሬ ለሚሉት ዛፍ እንኳ አልተከሉም ። የራስን እናት ለመውደድ የሌላውን እናት መጥላት ተገቢ አይደለም ። በራሴ በኩል ያስተማሩኝና ያሳደጉኝን ኦርቶዶክሳውያን አባቶቼን አመሰግናለሁ ። በልጅነቴ ያደግሁት ፡-
ጥያቄ ፡- ዘርህ ምንድነው ? መልስ ፡- ክርስቲያን ።
ጥያቄ ፡- አገርህ የት ነው ? መልስ ፡- መንግሥተ ሰማያት ።
ጥያቄ ፡- ንጉሥህ ማነው ? መልስ ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ።
በሚል መፈክር ነው ። ንጉሤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆንም አገሬንና ዘሬን አውቃለሁ ። ይህ ማንነትን መጣል ሳይሆን ይበልጥ እንድቀበለው ያደረገኝ ነው ። እነዚህን መምህሮቼን አመሰግናለሁ ። እባክዎ ቅንነትዎን ልለምንና ይህን አሳብ ለሌሎች ያካፍሉ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ