ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
የኑፋቄው ማዕበል
“እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም” ኤፌ. 4፡14 ።
ጊዜው ከሃያ ሦስት ዓመት በላይ ይሆነዋል ። አንድ ወጣትን አሁንም ድረስ አስታውሰዋለሁ ። ይህ ወጣት ልዩ የሚያደርገው የሄደበትን መዳረሻ ሁሉ ያሳውቀኝ ነበር ። ከማሳወቅ ውጭ ግን ምክር አይቀበልም ነበር ። በእርሱ አእምሮ ያለው ለመንፈሳዊ መምህር ያሉበትን ሁኔታ ማሳወቅ ይገባል የሚል መርህ ነው ። በደወለልኝ ጊዜ ሁሉ አንድ ቦታ ደግሞ ገብቷል ብዬ እገምታለሁ ፣ ተገናኝተንም ሪፖርት አዳምጬ እመለሳለሁ ። መልካም ምክር የምትጠቅመው ሲፈጽሟት ነው ። ይህ ወጣት ዲያቆን ሁኖ የሚቀድስ ነው ። በመቅደሱ አገልግሎት ያልተወሰነ ዐውደ ምሕረቱንም የሚወድድ ነበር ። ቴዎሎጂ መማር አለብኝ ብሎ ኮሌጅ ገባ ። ከወጣ በኋላ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ጀመረ ። ነገር ግን አልተረጋጋም ነበር ። ራሱ ተቃዋሚ ራሱ መልስ ሰጪ ሆኖ ተሐድሶ ሆንኩኝ አለ ። በተሐድሶም ትኩስ አገልጋይ ሁኖ እንደ ሰነበተ ነገረኝ ። ከዚያም ወጣና ወደ ፕሮቴስታንት እምነት ገባ ። ከፕሮቴስታንት እምነት ወጥቶ ወደ ይሖዋ ምስክሮች ገባ ። የሚገርመው ላለፈው ነገር ፍጹም ይቅርታ ለራሱ እየሰጠ ባለበት ቦታ ደስተኛነቱን ይገልጥልኛል ። እኔም ካላዳመጠ ብዬ መምከሬን አቁሜ ነበር ። ታዲያ ጂሖቫ ዊትነስ እንደ ገባ ሲነግረኝ፡- “ሌላ ጊዜ እንዳያምርህ ወደ ባሃኢ እምነት ለምን አትገባም?” አልኩት ። እርሱ ግን የሰጠኝ መልስ፡- “ወደዚያ ከምገባ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ብገባ ይሻለኛል” አለ ። እንዲህ ማለቱ የባሃኢ እምነት ይሁዲንም ፣ ቡድሃንም ፣ እስልምናንም ፣ ክርስትናንም ፣ ሳይንስንም ስለሚቀበል ነው ። ይህ ወጣት ከዚያ ጊዜ በኋላ አልተገናኘንም ። ቀጥለው ያሉት ሁለት ነገሮች ውስጥ እንደሚገባ እርግጠኛ ነኝ ። ክህደትና ዘረኝነት ውስጥ መግባቱ የማይቀር ነው ።
ሰይጣን ሰዎችን ከሚዋጋበት ከፍተኛ ውጊያ የመጀመሪያው፡- አማኞች ለመንፈሳዊ አባት ያሉበትን አድራሻ እንዲደብቁ በማድረግ ነው ። ልጆች ወላጆቻቸውን ሲደብቁ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ የታወቀ ነው ። ለመንፈሳዊ አባቱም መደበቅ የጀመረ አማኝ ውድቀቱ ከፍ ያለ ነው ። ለመንፈሳዊ አባት ራሱን ሲገልጥና ሲያማክር ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል ። ምክር መስማት ፣ የጸሎት እርዳታ መጠየቅና ውሳኔ ግድ ይሉታል ። ሰይጣን ሰዎችን የሚዋጋባት ትልቁ ፈተና አቃቂር አውጪ በማድረግ ነው ። ሰው አቃቂር ማውጣት ከጀመረ ራሱን አያይም ፣ ጉድለትን ብቻ ስለሚፈልግም ቀና ዓይን አይኖረውም ። ፍጹምነት መፈለግ ዘዋሪ ፣ ቀማሽ ፣ ተቺ ያደርጋል ። ይህ ሰው ዓለሙ ሁሉ ጠፍቶ እኔ ብቻ ንጹሑ ቀረሁ ይላል ። እርካታ ማጣት አዳምን ከገነት ያወጣ ነው ። ብዙ የተፈቀደ ፍሬ እያለ የተከለከለ አንድ ነገርን በአጉሊ መነጽር አሳየው ። ብዙ ሰዎችን ሰይጣን ከኅብረትና ከቤተ ክርስቲያን የሚያወጣቸው አቃቂር እንዲያወጡ በማድረግ ነው ። ለእግዚአብሔር የቀኑለት ይመስላቸውና ራሳቸው ጠያቂ ራሳቸው መልስ ሰጪ ሁነው ይሄዳሉ ። በመሄዳቸው አገልግሎት የቆመና የተጎዳ ይመስላቸዋል ። በመጨረሻ የሚጎዱት ግን ራሳቸው ናቸው ። ሰይጣን የሚዋጋበት ሌላው ትልቅ ፈተና ተስፋ መቍረጥ ነው ። ሁሉንም አየሁት ፣ ደኅና ነገር የለም በማለት ወደ ክህደት ዓለም ይገባል ። የሃይማኖት ነገር ሲወራም ብስጩና ተበቃይ ይሆናል ። ይህ ሰው የሚደመድመው በሰይጣን የመጨረሻ ክፋት በዘረኝነት ላይ ነው ። ብዙ ዘረኞች በሃይማኖት የጀመሩ ፣ በጎሠኝነት የፈጸሙ ናቸው ።
ሐዋርያው እንደ ሕጻናት መሆን የለብንም የሚለው ሲነቀሉ ሲተከሉ መኖርን ነው ። በዚህ ክፍል ላይ የትምህርት ነፋስ ይለዋል ። የትምህርት ነፋስ የተባለው ኑፋቄ ወይም የስህተት ትምህርት ነው ። የስህተት ትምህርት የሚፈበረከው በቀጥታ ከሰይጣን ነው ። ሰይጣን የካደው በመታለል ሳይሆን በአእምሮ ነው ። እግዚአብሔር አዳምን የፈለገው በመታለል ስለወደቀ ነው ። ኑፋቄ በውስጡ ማታለል ያለበት ነው ። ኑፋቄ እግዚአብሔርን አይክድም ፣ እግዚአብሔርን ሌላ መልክ ይሰጠዋል እንጂ ። ኑፋቄ መጽሐፍ ቅዱስን አይጥልም ፣ ለግላዊ አሳብ ይጠቅሰዋል እንጂ ። ከሙሉ ውሸት ከፊል እውነት የሰይጣን ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ። ሁላችንም በቂ የሆነ የሃይማኖት እውቀት ላይኖረን ይችላል ። ባለንበት ሃይማኖት በመጽናት ፣ ከመምህራን በትዕግሥት በመማር ወደ ሃይማኖት መረዳት እንደርሳለን ።
ነፋስ የሚግለበለብ ነው ፣ ኑፋቄም መዋከብ ያለበት ነው ። ነፋስ ትልቁን ያቀላል ፣ ኑፋቄ ውስጥም ክብር የለም ። ሽበትም ፣ ቅድስናም ፣ ሽማግሌም አባቶችም አይከበሩም ። የልጆች ዕድር ነው ። እርስ በርስ በመሆኑ የተሻለ እውቀትና መረዳት ያለው ስለማይገኝ መናናቅ ያለበት ነው ። በኑፋቄ የተያዙ ሰዎች የሚጠሉት ተቋም ካልፈጠሩ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ይገባል ። ያኛው ትክክል አይደለም በማለት የራሳቸውን ትክክለኛነት ለማስረዳት ይሞክራሉ ። በኑፋቄ ውስጥ ያለ ሰው ጤናማ ትምህርት ፣ አዎንታዊ ስብከት አይወድም ። አብዛኛው መጽሐፍ ቅዱስን ይዣለሁ የሚለው ወጣት እንደ አውቶብስ መጠበቂያ ጎሣውን እየጠበቀ ያለ ነው ። ብዙዎቹ የጎሣቸው አውቶብስ ስለመጣ ተሳፍረው ሄደዋል ። ከማያልቀ ርእስ ወደሚያልቅ ርእስ ገብተዋል ። እኛንም ይጠብቀን ።
ነፋስ ጣራን ይነቅላል ፣ የትምህርት ማዕበልም የመጨረሻውን ሕይወት ያበላሻል ። ነፋስ ካባን ነጥቄ ካልሄድሁ ይላል ። ኑፋቄም መከበርም ማክበርም አይፈልግም ። ነፋስ ይነጥቃል ፣ የትምህርት ነፋስም ብዙ ሞኞችንና ሕጻናተ አእምሮን ይወስዳል ። የሚባንኑት ሁሉንም ነገር ካጡ በኋላ ነው ። ኑፋቄ ውስጥ የተሳሳተ ትምህርት ስላለ የተሳሳተ ኑሮ አለ ። ሽንገላም ድሩን ያደራው በኑፋቄ ስፍራ ነው ። ወንድሜ ፣ እኅቴ መባባል አለ ፣ ፍቅር ግን የለም ። ተካስሰው ፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ ሲደርሱ ዳኛው እስኪገባ እየተመራረቁ ይቆያሉ ። አብዛኛው የመናፍቃን ጎራ ከስለላ ተቋማት ጋር ግንኙነት ያለው ነው ። ከሀብትና ከዝና ውጭ መንግሥተ ሰማያት ጉዳያቸው አይደለም ። የአፍ ጮማ እንጂ ለተራበ የሚሆን ቁራሽ ለመስጠት ይፈተናሉ ። ያደጉባትንና እንጀራ የበሉባትን ቤተ ክርስቲያን ሲሳደቡ መጠን የላቸውም ። ሄደውም ካልረሱአት አላረፉም ማለት ነው ። መሳደብ የመናደድና ያለማረፍ ምልክት ነው ። ሐዋርያው ተንኮልም አለ ይላል ። እርስ በርስ በሴራ ሲጠላለፉ መኖር የኑፋቄው ዓለም መገለጫ ነው ። ሥራ ከሌለ ሴራ ሥራ ይሆናል ። ማታለልም እንዳለ ሐዋርያው ይናገራል ። በሐሰተኛ ፈውስና ትንቢት ሕዝቡን አስፈቅደው ይዘርፉታል ። ወዶ ተድፍቷልና ቢረግጡት አይከፋውም ። የዚህ ሁሉ ምንጩ የትምህርት ነፋስ ነው ። ድንገት የሚመጣ ፣ ጠራርጎ የሚወስድ የትምህርት ነፋስ አለ ። መምህራን በሌሉበት የሚደረጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ሁሉም የመሰለውን ትርጉም ስለሚሰጥበት መጨረሻ ላይ አዲስ ኑፋቄ ይወለድበታል ። ኑፋቄ የቤተ ክርስቲያንን ብቻ ሳይሆን የአገርን አንድነትም አደጋ ላይ ይጥላል ።
ወጣቶች ረጋ በሉ ። ለማመኑም ለመካዱም አትቸኩሉ ። በትንሽ እውቀት ብዙ ስህተት እንደምትሠሩ እወቁ ። ለመማርና ለመመከር ፈቃደኛ ሁኑ ። በወጣትነታችሁ ያበላሻችሁትን እስከ ዕድሜ ልካችሁ ላታስተካክሉት ትችላላችሁ ። ነፋስ ይወስዳል ግን ወደ ትክክለኛ ግብ አይደለም ፣ ኑፋቄም ግብ የሌለው ጉዞ ነው ። ሰይጣን በሃይማኖት ጥሎ በምግባር ሊያቆነጅ ይችላልና አስተውሉ ።
እግዚአብሔር ሆይ ፣ እኛም ቆመናል ብለን አንመካም ። እስከ መጨረሻ ድረስ አንተን በማመን አጽናን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 25 ቀን 2014 ዓ.ም.