እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ 2009 ዓ.ም የልደት በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችሁ!
ፍጹም ክብር ካለበት ዓለም ፍጹም ውርደት ወዳለበት ምድር ለእኛ ሲል ተወለደ ፤ ባለ ወግ ሊያደርገን ባለ በረት ሆነልን ። ባለ ሰማይ ሊያደርገን ባለ መስቀል ተባለልን ። የኪዳን ቀለበት ሊያደርግልን በችንካር ቆሰለልን ። ነገሥታት ሊያደርገን የእሾህ አክሊል ደፋልን ፣ ካህናተ ጽድቅ ሊያደርገን ሐሰተኛ ተባለልን ። ሰማይና ምድር የማይችሉት በድንግል ማኅጸን አደረ ፤ በኪሩቤል ጀርባ የነገሠው በንጽሕት ድንግል እቅፍ ውስጥ አረፈ ። በዙፋኑ የሚጠብቀን እንደ ትንሽ ሕጻን ተሯሯጠ ። ሁሉ እንዲሆንልን ሁሉ የሌለው ሆነ ። የጌታችን እግሮች በረገጧት ምድር ላይ ስላላችሁ ደስ ይበላችሁ ። እርሱ ባለፈበት ሕይወት ስለምታልፉ እልል በሉ ። ኑሮ እንዳያሰጋችሁ ሕይወት ሆኖ ተወለደላችሁ ። በጊዜያዊው ነገር እጅ እንዳትሰጡ የዘላለሙን ፍስሐ አወረሳችሁ ። በእውነት እንኳን አደረሳችሁ!