የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንዴት ሊሆን ይችላል?

“ኒቆዲሞስ መልሶ፦ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” /ዮሐ. 3፡9-10/ ፡፡
     ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ የእግዚአብሔር መልስ ይህ እንዴት ሊሆን አይችልም? የሚል ነው ፡፡ ከመሆኑ በላይ እንዴት መሆኑ ለሰዎች አሳሳቢ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ግን ስለ መሆኑ ይናገራል እንጂ በእንዴት አይገደብም ፡፡ ሁሉ መንገዱ ፣ ሁሉ ሎሌው፣ ሁሉ የእጁ ሥራ ፣ ሁሉ ገንዘቡ ነው ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ችሎታ ሲናገር ፡- “የእግዚአብሔርባለጠግነትናጥበብእውቀቱምእንዴትጥልቅነው፤ ፍርዱእንዴትየማይመረመርነው፥ ለመንገዱምፍለጋየለውም” ብሏል /ሮሜ. 11፡33/፡፡ ይህን ቃል የተናገረበት ምክንያት ምንድነው ? ስንል ከሮሜ 9 ጀምሮ የሚናገረው ስለ እስራኤል ነው ፡፡ ሮሜ 9 ስለ እስራኤል መመረጥ ፣ ሮሜ 10 ስለ እስራኤል አለመታዘዝ ፣ ሮሜ 11 ስለ እስራኤል መዳን ይናገራል ፡፡ ከአሕዛብ ወደ ክርስትና የመጡት እስራኤልን እንዳይንቁ በምዕራፍ 9 ያስጠነቅቃል ፣ በዓመጻቸው እንጂ እግዚአብሔር እንዳልጣላቸው ምዕራፍ 10 ይዘረዝራል ፣ እንግዲህ ተስፋ የላቸውም እንዳይባል ምዕራፍ 11 እስራኤል እንደሚድኑ ያበስራል ፡፡ እንዴት ይድናሉ ? ሰቃልያነ ክርስቶስ አይደሉም? ገናስ መሢሕ ይወለዳል እያሉ ይጠባበቁ የለም ወይ ? ቢባል በሮሜ 11፡33 “የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም” በማለትይመልሳል ፡፡ ይህማ እግዚአብሔር እያዳላ አይደለም ወይ ? ቢባል እስራኤልን የሚምረው አሕዛብን በማረበት መንገድ ነው ፡፡ አሕዛብ በጸጋው የማይገባቸውን ካገኙ እስራኤልም በጸጋው የማይገባቸውን ያገኛሉ ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የጠላናቸው ቶሎ ለምን አልተቀጡም ? ብለን እግዚአብሔርን እንቀየማለን፡፡ እግዚአብሔር ለእነዚያ ሰዎች ያሳየው ትዕግሥት ለእኛ ያሳየውን ትዕግሥት ነው ፡፡ ሌላ አዲስ ነገር አላደረገም ፡፡
“የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም” የሚለው ቃል እስራኤል እንዴት ይድናሉ ? ለሚለው ጥያቄ መልስ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የሰዎች አለመቻል የእንቢታቸው ብዛት ሳይከለክለው በድንቅ ይሠራል ፡፡ ለእንዴት ጥያቄ መልሱ ፡-
    የእግዚአብሔር የማይተመን ባለጠግነት
    የእግዚአብሔር የማይኮረጅ ጥበብ
    የእግዚአብሔር የማይመረመር እውቀት
    የእግዚአብሔር ይግባኝ የሌለበት ፍርድ
    የእግዚአብሔር ያልተሰመረለት መንገድ
    የእግዚአብሔር ከተፈጥሮ ድንጋጌና ከሰዎች ሕግጋት በላይ መሥራት፤ እንዴት የሚለውን የሰው አቅመ ቢስ ጥያቄ ድል ይነሣል ፡፡
የአይሁድ መምህር የነበረው ኒቆዲሞስም ስለ ዳግም ልደትና ስለ መገለጫው ሲሰማ፡- “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” /ዮሐ. 3፡9-10/ ፡፡ መወለድ የመጀመሪያ ተግባር እንጂ የመጨረሻ ተግባር አይደለም ፡፡ ለመጨረሻ ግን መጀመሪያ ነው ፡፡ መወለድ አንድ ጊዜ ሲሆን ማደግ ግን ሁልጊዜ ነው ፡፡ ኒቆዲሞ ስለጠየቀው ጥያቄ ጌታችን< /span> የሰጠው መልስ “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” የሚል ነው፡፡ አይሁዳውያን የአይሁድን እምነት የተቀበለ አንድ ሰው ዳግም እንደ ተወለደ ያምኑ ነበር ፡፡ ኒቆዲሞ ስለ ማወቅ ያውም ጥቂት እውቀት ለማወቅ መጣ እንጂ ለማመን አልመጣም ፡፡ ለማወቅ የመጣ ሰው ለማመን ሲቃረብ መሸነፍ ይመስለዋል ፡፡ ለማወቅ የመጣ ሰው ባለው ላይ ለመጨመር የመጣ እንጂ ከመጀመሪያ ለመጀመር ፈቃደኛ አይደለም ፡፡ ኒቆዲሞስ ዳግም ልደትን ከነአፈጻጸሙ ሰማ ፡፡ እንደገናም ስለ አኗኗሩ አደመጠ ፡፡ ይህ ጥያቄ ያልመጣበት በመሆኑ ዳር ዳሩን በመሄድ ሊያልፈው ፈለገ ፡፡ በዚህ ጌታችን አዎ አንተ ጥያቄህ ባይሆንም ምስክርነት ግን ሰውየው አያስፈልገኝም የሚለውን ነገር ያስፈልግሃል ብሎ ከደሙ ነጻ ለመሆን የሚነገር አዋጅ ነው የማለት ያህል እንዲህ አለው፡- “እውነትእውነትእልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም” አለው /ዮሐ. 3፡11/፡፡ ጌታ ስለ ዳግም ልደት በብዙ ቁጥር እንናገራለን ፣ እንመሰክራለን አለ፡፡ ከእርሱ በኋላ በሚሊየን የሚቆጠሩ አገልጋዮች ምስክርነት ነውና ፡፡ ጌታችን ለእውቀት ለመጣው ኒቆዲሞስ የምናውቀውን አለ ፡፡ የምናውቀውን ያለው ዳግም ልደትን ነው ፡፡ ይህ ምስክርነት ነው ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በክርስቶስ ያመኑትን በልጅ ወግ ሊቀበል ዘመኑ ደርሷል ፡፡ ኒቆዲሞስ ብቻ ሳይሆን መላው አይሁድ ይህን መቀበል አልፈለጉም ፡፡ ሰው አንድ ጊዜ የሰማውን እንዳልሰማ ማድረግ አይችልም ፡፡ ስለዚህ ኒቆዲሞስ በኋላ በክርስቶስ አመነ ፡፡ የተዘራ ዘር መብቀሉ አይቀርም ፡፡ እንኳን እውነት ሐሰትም በጊዜው ይበቅላል ፡፡ መጨነቅ ያለብን ምን እንደምንናገር እንጂ የምናገረውን ሰው አይቀበልም ብለን ሊሆን አይገባም ፡፡ ማንኛውም ንግግርና ራእይ ተቀባይ አለው ፡፡ 
ጌታችን ስለ ኒቆዲሞስ ብዙ ያውቃል ፡፡ እናውቃለን በማለት የተናገረው ግን የእግዚአብሔር ፍቅር ስለሚገለጥበት ስለ ዳግም ልደት ነው፡፡ እውቀት ምንድነው ? እውቀት  ካልተለየ ባለቤቱን ያታልላል ፡፡ ማኅበረሰብን ያሰናክላል ፡፡ ያወቅነው ምንድነው ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል ፡፡ የተባረከ እውቀት ራስንም ሰዎችንም በእግዚአብሔር ማወቅ ብቻ ነው ፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው እውቀት ለባለቤቱ ሰላም ለሰዎችም ህንጸት አይጠቅምም፡፡  
ጌታችን በመቀጠል በፍቅር ወቀሳ ፡-“ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?” አለ /ዮሐ. 3፡12/ ፡፡ ዳግም ልደት ምድራዊ ነገር ነው ወይ? ዳግም ልደት ሰማያዊ ነው ፡፡ የሚከናወነው ግን በምድር ላይ በሚታይ ሥርዓትና በማይታይ ምሥጢር ነው ፡፡ ሰው በእምነት ወይም በመንፈስ ብቻ የሚያከናውነው አይደለም ፡፡ በሰማይ ያለው ግን እጅግ ረቂቅና በቃላት ለመግለጽም የሚያስቸግር ነው ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- “ወደገነትተነጠቀ፥ ሰውምሊናገርየማይገባውንየማይነገረውንቃልሰማ”በማለት ስለ ራሱ ይናገራል፡፡ /2ቆሮ .12፡4/፡፡ በሌላ ሰው ምስል የሚናገረው ስለ ራሱ ነው ፡፡ የሚናገረውም ከ14 ዓመታት በኋላ ነው ፡፡ ወደ ሰማይ ተነጥቆ የሰማይን ጓዳ በጨረፍታ አየ ፡፡ ያንንም ለመግለጽ ቀርቶ ለመስማትም ከባድ መሆኑን ተናገረ ፡፡ እንኳን መነጠቅ ይቅርና ደህና ሕልም ቢታይ ዛሬ 14 ዓመት አይደለም 14 ቀን የሚሸከም መቋጠሪያ ያለው ሰው ይገኝ ይሆን ? ምሥጢር የሌለው ሰው የእግዚአብሔር ባለሟል መሆን አይችልም ፡፡ እኛም ብንሆን የቅርብ ረዳታችን ምሥጢረኛ ካልሆነ አንፈልገውም ፡፡ ያዩት ሁሉ አይነገርም ፡፡
ጌታችን ለኒቆዲሞስ በምድር ላይ ስለሚከናወነውና ብዙ አጀብ ስላለው በአዋጅ ስለሚከናወነው ስለ ዳግም ልደት ካልገባችሁ ስለ ሰማይ ብነግራችሁ አይገባችሁም እያለ ነው ፡፡ “ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?”
የጥንት ክርስቲያኖች ጥምቀትን ይፈጽሙ የነበረው በሸለቆ ውስጥ በሚገኝ ወንዝ ነው ፡፡ በሸለቆው መነሻ ላይ የሥጋ ቤተሰባቸውን ያቆሙና ወደ ውኃው ይወርዳሉ ፡፡ ከሸለቆው ማዶ ክርስቲያኖች ተሰባስበው ይጠብቃሉ ፡፡ ተጠምቆ የወጣው የሥጋ ቤተሰቦቹን በክርስቶስ ካልሆነ ላንገናኝ ተለያየን በማለት ይሰናበትና አዲሱን ቤተሰብ ይቀላቀላል ፡፡ ጥምቀት አዲስ ቤተሰብ የምናገኝበት ከሆነ ከውኃውና ከመንፈሱ ስለምንወለድ ነው ፡፡
“ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” /ዮሐ. 3፡13/፡፡ ጌታችን ስለ ሰማይ ሊነግረን የሰማይ ባላባት ነው ፡፡ ከሰማይ ወረደ በማለት መጠቀሱ ሥጋ መልበሱን ያሳያል ፡፡ ምክንያቱም በመለኮቱ መውጣትና መውረድ ፣ መገኘትና መታጣት የሌለበት አምላክ ነው ፡፡ በለበሰው ሥጋ ግን ወረደ ተብሏል ፡፡ ወደ ምድር ሲወርድም በሰማይ አልታጣም ፡፡ ወደ ምድር ቢወርድም በሰማይ የሚኖር ነው ፡፡ በሰማይ ያለውን የምናውቀው ወደ ሰማይ ስንሄድ ነው ፡፡ በምድር ሁነን በሰማይ ምን እንደሚከናወን አናውቅም ፡፡ በሰማይ ሄደንም ያየነውን በምድር ላሉት መናገር አንችልም ፡፡ ወደ ሰማይ ብንሄድ በምድር ስለ ነበርን ነው ፡፡ ሰማይ አዲስ አገራችን ነው ፡፡ ወደ ሰማይ ያረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከሰማይ የመጣ ነው ፡፡ በቤተልሔም ሲወለድ ህልውናው የጀመረ አይደለም ፡፡ እርሱ ሰማይን ሳይከስር ወደ ምድር የወረደ ነው ፡፡ አጣዋለሁ ብሎ የማይሰጋ የባለጠጎች ባለጠጋ ነው ፡፡ አልተቀበለምና የሚነጥቀው የለም ፡፡ የሰማይን ጓዳ በማወቅ ሳይሆን በማበጀት በማደራጀት በባለቤትነት የሚነግረን እርሱ ብቻ ነው ፡፡ ግን የሰማዩን ሊነግረን ይቅርና በምድር ላይ የሚከናወነውን ነገር ማለት ምሥጢራትን ወይም ጥምቀትን መገንዘብ ገና አልቻልንም ፡፡ ስለ ዳግም ልደትም ምድራዊና ሰማያዊ መልክ የሚነግረን በሰማይም በምድርም ያለው ጌታችን ነው ፡፡ ጌታችን በመቀጠል ስለ ናሱ እባብ ምሳሌነትይናገራል ፡፡ እግዚአብሔርይመስገን ፡፡ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ