አርምሞ ወይም ዝምታ ከሕይወት ክፍሎች አንዱ ነው ። ሰው የሚናገርበት ዘመንና ዝም የሚልበት ዘመን አለው ። ለሁሉም መናገር ፥ ለሁሉም ዝም ማለት ሁለቱም አደጋ አለው ። ሰዎች ዝምታን የሚመርጡበት የተለያየ ምክንያት አላቸው ። በተጨቆነ አስተዳደግ ዝምታን የሚመርጡ አሉ። በመስማትና በማንበብ አሳብን ማበልጸግ ያልቻሉ ዝም ይላሉ ። እውነት ሲናገሩ ሰውን እያጡ ፥ ሐሰትን ሲናገሩ ከኅሊናቸው እየተጋጩ ዝምታን የመረጡ አሉ ። ሕይወታቸው ብዙ ስለሚናገርም ዝምታን የመረጡ አሉ ። ሕይወት ከቃል በላይ ይናገራልና ወይም ቃል በሕይወት ይገዝፋልና በዚህ ዝምታን የመረጡ አሉ ። የሰው ልጅ ከብክነት መልስ ፥ ከሩጫም ማግሥት የዝምታና የጽሞና ጊዜ ያስፈልገዋል ። ረጅም መንገድ ለመጓዝ ጽሞና አስፈላጊ ነው ። ጽሞና ወይም ዝምታ ውጫዊ የሆኑትን ስሜቶች ድል ነሥቶ ወደ ውስጥ መሆን ነው ። ውጫዊ የስሜት ሕዋሳት ማየት ፥ መስማት ፥ ማሽተት ፥ መዳሰስ ፥ መቅመስ ናቸው ። እነዚህ የስሜት ሕዋሳት ያለ ውስጠኛው ስሜት ሕዋስ አይሠሩም ። ሰው እያየ ያልፋል ፥ ሲወቀስም ልቤ አላየም ወይም ልብ አላልኩም ይላል ። ዓይን ብቻ እንደማያይ እየገለጠ ነው። በጆሮው ቢሰማም በውስጡ ማዳመጥ አለበት ። ስለዚህ የሕሊና ጆሮ አለው ማለት ነው ። ውሳጣዊ ሕዋሳት ንቁ የሚሆኑት በጽሞና ወይም በዝምታ ነው ።
የጽሞና ሕይወት ካለፉት ዘመናት ይልቅ አሁን በጣም እየተፈለጉ ነው። ሰዎች በሚመስል ነገር እየባከኑ ነው ። በድንገትም ሲወድቁ የችግሩ መንስኤ የጽሞና ሕይወት ማጣት ነው ። እግዚአብሔር ለሰውም ለምድርም ሰንበትን ሰጥቷል ። ይህ ሰንበት ዕረፍት ነው ። የማገገም ፥ ኃይልን የማጠራቀም ምሥጢር ነው ። ሁልጊዜ መናገር ፥ ሁልጊዜ መሮጥ ፥ ሁልጊዜ ሌሎችን ለማስደሰት መሞከር …ቀጣይነት የሚኖረው በጽሞና ነው ። ጽሞና መቆም አይደለም ። የሠሩትን ሥራ ለመገምገም ጊዜ ማግኘት ነው ። ከውጫዊ ሙገሳና ወቀሳ ይልቅ በጽሞና ራስን ማየት ይቻላል ። ንሥር ኃይሉን የሚያድሰው በጽሞና ነው ። አርባ ዓመት ሲሞላው ጭው ባለ ሸለቆ ላይ ያረጁ አካላቱን በማስወገድ ፀጉሩን መድምዶ ጥፍሩን ነቅሎ ለአርባ ቀናት በጽሞና ይቆያል ። ይህን ባያደርግ አሥር ዓመት መኖር ይችላል ። ጽሞና በማድረጉ ግን አርባ ዘመን መኖር ይችላል ። ያረጁ ነገሮች ምንድናቸው ? የተለመዱ ንግግሮች ፥ እውቀት አልባ አሳቦች ፥ ተቺነትና ንቀቶች እነዚህ ሁሉ የጽሞና እጦት የወለዳቸው ናቸው ። እነዚህን ማስወገድ የሚቻለው በጽሞና ሕይወት ነው ። በጽሞና ውስጥ ቃሉን ማሰላሰል ዋነኛው ክፍል ነው ። በቃሉ ራስን ማየትና ለንስሐ መብቃት ይቻላል ። በዚህም ከአሮጌው ማንነት መላቀቅ ይቻላል ። ጽሞና ከሰዎች ራቅ ማለትን ይጠይቃል ። ከሰዎች ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም መገናኛ ማጥፋት ግድ ይላል ። የአሳብ ጉዞንም መግታት ያስፈልገዋል ። ሰው ሰው የሚሸቱ ነገሮችን ወይም የሰው እጅ ያለባቸውን ነገሮች ማራቅ ያስፈልጋል ። ቴሌቪዥኑም ሬድዮም የጽሞና ፀር ናቸው ። ጽሞና ይዣለሁ እያሉ በስልክ ግን የሚታወኩ አያሌ ናቸው ። ይህ ቀልድ ነው ። የጽሞና ሕይወት ካልመረጥን እንደ ንሥር ጥቂት ዘመን መኖር እንችላለን ። ረጅም ዘመን መጓዝ ግን ይከብደናል ።
ሁለት ሰዎች እኩል መጠን ያላቸውን ዛፎች ለመቊረጥ ተነሡ ። አንደኛው ያለ ዕረፍት ይገዘግዛል ፥ አንደኛው ግን እያረፈ ሲቆርጥ በቶሎ ሥራውን ጨረሰ ። በዚህ ጊዜ ሰዎች ፡- “ጓደኛህ ያለ ዕረፍት ሠራ ፥ አልጨረሰም ፥ አንተ ግን እያረፍህ ሠርተህ ሥራህን የጨረስከው ምሥጢሩ ምንድነው ?” አሉት ። እርሱም ሲመለስ ፡- “እኔ ባረፍኩ ቊጥር መጥረቢያዬን እስለው ስለነበር ለዚህ ነው ቶሎ የጨረስኩት” አለ ይባላል ። ድል ያለው ያለ ዕረፍት በመሮጥ ውስጥ አይደለም ። ተቀምጦ መጥረቢያውን በመሳል ውስጥ ነው ። እርሱም ጽሞና ነው ።
ዘመናችን ራስን ማየት የሚያስፈራበት ዘመን ነው ። ሰዎች በሰዎች ሐሜት ተጠምደው በስድብ ሲወዳደሩ የሚውሉት ራስን ማየት አስፈሪ ስለሆነ ነው ። በርግጥ ራስን ያለ ክርስቶስ ማየት አስፈሪ ነው ። በጽሞና ውስጥ ራስን በክርስቶስ ማየት ግን ደስታንና ነጻነትን የሚያጎናጽፍ ነው ። ኩልል ያሉ ውኃዎች መልክን ያሳያሉ ፥ ቀጥሎ ያረካሉ ። ኩልል ያሉ የጽሞና ሰዓቶችም ራስን ያሳያሉ ቀጥሎም ያረካሉ ። የጽሞና ሰዓት በየዕለቱ በደቂቃዎች የምንለማመደው ፥ እያደገ ሲመጣ በወር ውስጥ ቀን የምንሰጠው ፥ በዓመት ውስጥ ደግሞ ሳምንታት የምንሰጠው ነው ። እነዚህ የመታደስ ጊዜዎች ለቀጣዩ ዘመን ኃይል ናቸው ።
አርምሞ በብዙ ቅዱሳን የተለመደ ነገር ሲሆን እንደ እመቤታችን ድንግል ማርያም ግን ሕይወቱ ያደረገው ማንም የለም ። ስለ መናገር ብቃት እናውቃለን ፥ ስለዝምታ ብቃት ግን አልተረዳንም ። በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ዝምታ የትልቅ አቅም ማሳያ ነው ። የእመቤታችን ሕይወቷ የአርምሞ ሕይወት ነበር ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በረጅም የተናገረችው በጸሎቷ ብቻ ነው /ሉቃ. 1፥46-55/ ። ከዚያ ውጭ የተናገረችው ውስን ንግግሮች ናቸው ። እነርሱን ለመጥቀስ ያህል ፡-
“ማርያምም መልአኩን ፡- ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው” /ሉቃ. 1፥34/።
“ማርያምም ፡- እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች” /ሉቃ. 1፥38/
“እናቱም ፡- ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው” /ሉቃ. 2፥48/
“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው” /ዮሐ. 2፥3/ ።
“እናቱም ለአገልጋዮቹ ፡- የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው” /ዮሐ. 2፥5/
እመቤታችን ድንግል ማርያም የዝምታዋ ምንጭ አለማወቅ አይደለም። የብሉይ ኪዳን ሰፊ እውቀት እንዳላት ካቀረበችው ጸሎት መረዳት እንችላለን። ዝምታዋ የእግዚአብሔርን ጊዜ መጠበቅ እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል ። ጌታችንን በድንግልና በወለደች ጊዜ እረኞች ያዩትን መጥተው በመሰከሩ ጊዜ “ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር” ይላል ።/ሉቃ. 2፥19/ ። መልአኩ የነገረኝ ይኸው ተፈጸመ አላለችም ። በልብዋ ትጠብቀው ነበር ። ልጇ በአሥራ ሁለት ዓመቱ ጠፍቶ በመቅደስ ባገኘችው ጊዜ ፡- “ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንዲገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው። ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር”ይላል /ሉቃ. 2፥51/ ። ቃሉን ብቻ ሳይሆን መታዘዙንም በልብዋ ትጠብቀው ነበር ። እግዚአብሔር በሰው መልክ ተገልጦ የሚያደርገውን ትሕትና የተረዳች እርስዋ ብቻ ነበረች ። ይህንንም በልብዋ ትጠብቀው ነበር።
የአርምሞን ሕይወት በጣም ተለማምዳ ነበር ። አርምሞዋን ለማየት ብንሞክር ፡-
በጻድቁ በዮሴፍ ፊት ፡- ጻድቁ ዮሴፍ ከለላ ሆኖ ተሹሞላት ነበር ። ይኸውም አንዲት ሴት ያለ ትዳር ፀንሳ ብትገኝ በድንጋይ ተወግራ ትሞት ነበር ። ስለዚህ መፅነሷ ራሱ መከራ የሚያመጣ ነበር ። ለዚህ ልዩ ከለላ የተደረገው ዮሴፍ ነው ። እመቤታችንም የመልአኩን ብሥራትና ድንግልናዊ ጽንሰቷን ለዮሴፍ እንኳ አልነገረችውም ። ለዮሴፍ ያስረዳው መልአኩ ነው /ማቴ. 1፥18-23/ ። ይህ የሚያሳየን አርምሞዋ ከፍ ያለ መሆኑን ነው ። አጠገቧና ዙሪያዋን እንዳትፈራ የሚያደርግ አርምሞ ነበራት ። እርስዋ ዝም ስትል የሚናገርላት ይላካል ።
በኤልሳቤጥ ፊት ፡- የኤልሳቤጥን መጽነስ የነገራት መልአኩ ገብርኤል ነው ። መልአኩ የነገራትን ድርብ ደስታ ለማድነቅ ወደ ኤልሳቤጥ ቢያንስ የ400 ኪሎ ሜትሮች ጉዞ አድርጋለች ። ለዓለሙ የመዳን ጊዜ መቃረቡን የምሥራች ስለሰማች ያ የምሥራች ኃይል ሆናት ። ወደ ተራራማው ወደ ይሁዳ አገር የሄደችው በጉልበት ነው ። ኤልሳቤጥ ጋ ደርሳም የተናገረችው የለም ። ኤልሳቤጥ ግን የጌታዬ እናት አለቻት /ሉቃ. 1፥43/ ። ቅዱሳን ሳይነጋገሩ በመንፈስ ቅዱስ ይግባባሉ ። እመቤታችንም ትንቢት መናገር ጀመረች እንጂ ስለሆነው ነገር ምንም አልተናገረችም ። ወደ ኤልሳቤጥ የሄደችው የመልአኩን ቃል ለማረጋገጥ ሳይሆን ለኤልሳቤጥ በሆነላት ነገር እግዚአብሔርን ለማመስገን ነው ። የሚበልጠውን በድንግልና መጽነስ አምናለችና ።
በእረኞች ፊት ፡- እረኞች የተገለጠላቸውን ራእይ በተናገሩ ጊዜ ድንግል ማርያም ከዝምታ ውጭ መልስ አልነበራትም ። ዝምታዋ ግን እንዲሁ ሳይሆን በልብ የመጠበቅ ዝምታ ነው /ሉቃ. 2፥19/ ።
በመታዘዙ ፊት ፡- የሚላኩ ፥ የሚራዱ መላእክት ያሉት እርሱ እንጨት እየሰበረ ፥ ውኃ እየቀዳ ሲታዘዛቸው ምሥጢሩን የምታውቀው እርሷ ይህን ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር ። የአርምሞዋ ምሥጢርም ከቃላት በላይ የሆነ ነገር ሲከናወን በማየቷ ነበር ። ይህ የአርምሞ ሕይወቷ ድንግልናዊ ኑሮን ፥ የቅዱሳን መጻሕፍት ምርምርን ፥ እምነትን ፥ ትዕግሥትንና ይቅርታን ሲወልድ እናያለን።
በሔዋን ትይዩ ሆና የምትታየው ድንግል ማርያም የአርምሞ ሕይወቷ ከሔዋን ልዩ ያደርጋታል ። ሔዋን ምሥጢርን ለጠላት በመንገሯ የውድቀት ምክንያት ሆናለች ። እመቤታችን ግን በዚያ ተቃራኒ የምሥጢር ማኅደር ሆናለች ። ሔዋን ከአዳም ተገኝታ መልሳ ረዳቱ ሆናለች ። እንዲሁም ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር ተገኝታ መልሳ የእግዚአብሔር ወልድ እናት ሁናለች ። አዳም ሔዋንን ሴት በማለት ስም አውጥቶላታል ፥ ጌታችንም እናቱን አንቺ ሴት በማለት ጥንተ ተፈጥሮንና ትንቢትን ለማስታወስ በዚህ ስም ይጠራታል ። ሔዋን ከአዳም ጋር ብትኖርም ድንግል ነበረች ። እመቤታችንም ለዮሴፍ ታጨች ቢባልም ድንግል ናት ። በዘላለማዊ ድንግልናም ኑራለች ። ወደ ድንግል ሔዋን ሰይጣን ሄደ ፥ ወደ ድንግል ማርያምም መልአኩ ሄደ ። ሔዋን ዓለምን ወክላ የስህተትን ድምፅ ሰማች ፥ እመቤታችንም ዓለምን ወክላ የድኅነትን ድምፅ ሰማች ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሔዋን የጠላትን ድምፅ ሰማች ፥ ስታ አሳተች ፤ እመቤታችን የመጀመሪያዋ የወንጌል ተሰባኪ ፥ አማኒትና ሰባኪ ሆነች ። ሔዋን የእግዚአብሔርን ቃል ማመን አቃታት ፥ እመቤታችን ግን እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች ። ሔዋን የጠላትን ማግባባት መቋቋም አቃታት ፥ እመቤታችን ግን መልአኩ ሲያመሰግናት ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው ? ብላ በልብዋ አሰበች ። አዎ እመቤታችን የአርምሞ ሕይወት ነበራት ። የልጅዋ ክብር ይገለጥ ዘንድ ግን አንዲት አጭር ልመና አቀረበች ፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” /ዮሐ. 2፥3/። ልመናዋም አርምሞዋን ያሳያል ።