4- የፈቃዱን ታላቅነት የሚያከብር ነው
“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” የሚለው ልመና የሚያስፈቅድ ልመና ነው። ይህ ለጸሎት ትልቅ ትምህርት ነው ። እግዚአብሔር ልመናችንን የሚፈጽመው እንደ ፈቃዱ ነው ። ፈቃዱ ደግሞ ለእኛ መልካም ናት ። እርሱ የምንፈልገውን ሁሉ አይሰጠንም ፥ የሚያስፈልገንን ግን ይሰጠናል ። ብዙ ጊዜ የሚያስፈልገን የዕለት እንጀራ ሳለ የምንፈልገው ግን የዓመት ቀለብ ነው ። ኪሳችንንና ቤታችንን ብንፈትሽ ለዛሬ የሚበቃ ይኖረን ይሆናል ። ስለዚህ የዛሬ ጸሎታችን ተመልሷል ማለት ነው ። ምስጋና በምናሰማበት ቀን ዝም ማለት አይገባንም ። ስለጨበጥነው ነገር ግዴለሾች ፥ ስላልጨበጥነው ነገ ስጉዎች መሆን የለብንም ። ምናልባት ከመብልና ከመጠጥ ያለፈ ጉድለት ይኖርብን ይሆናል ። አሁንም ቢሆን ከጎደለን ያለን ይበልጣል ። ምስጋና የማሰብና የመቊጠር ድምር ነው ። ስናስብ ፥ ስንቆጥር ያለን ብዙ ነው ።በመንፈሳዊ ሕይወት እየበሰልን ስንመጣ እንደ ፈቃዳችሁ ብሎ እንዳይሰጠን እንሰጋለን ። የምንፈልገው ነገር ቢመጣም ተመልሶ ጥያቄ ይሆናል ። የምንሻው ነገር ተገኝቶም እንደ ገና ፍለጋ ይጀመራል ። የዓለም ነገር ጉልላቱን ሲያወሩ መሠረቱ ይናጋል ። ስለዚህ እንደ ፈቃዱ እንዲሰጠን መለመን አለብን ። በጸሎታችን ላይ ፈቃድህ ይሁን ብለን በቃል ማሰማት ብቻ ሳይሆን በልባችንም ፈቃዱን ልንወደው ይገባል ። የእመቤታችን ጸሎት የሚያስተምረን ይህን ነው ።
5- የጌታን ርኅራኄ ታሳቢ ያደረገ ነው
እመቤታችን በመጀመሪያ ራራች ። ልጇም እንደሚራራ ታምናለች ። ስለዚህ ለእርሱ አቀረበች ። በመፈጸሙ ጥርጥር የላትም ። “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ስትለው “ያለሃቸው አንተ ነህ ፥ እወቅበት ፤ ይህን ጓዳ ማንም አይመልከተው ፥ ሸፍነህ መሥራት ልማድህ ነው” ማለቷ ነው ። ስለሌሎች ስንጸልይ ራርተን ነው ። የእኛ ርኅራኄ የጸጋ ነው ፥ የእርሱ ርኅራኄ ግን የባሕርዩ ነው ። ስለዚህ ስለሌሎች የምንጸልየው ጸሎት በፊቱ የተወደደ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል ። ልመናችን እግዚአብሔርን ለማራራት መሆን የለበትም ፥ ምክንያቱም እርሱ በባሕርዩው ሩኅሩኅ ነውና ። ውስጣችን ስለፈነቀለን ማልቀስ ፥ ማንባት እንችላለን ። እግዚአብሔርን ለማራራት ከሆነ ግን ባሕርዩን አላወቅንም ማለት ነው ። ራርተንላቸው የምንጸልይላቸው ወገኖች ብዙ ናቸው ። የእግዚአብሔርን ጠባይ ባለማወቅ ግን መልሰን እንጨነቃለን ። እኛ ከራራን እርሱ መራራቱ እርግጥ ነውና ማረፍ ይገባናል። ጌታችን ፡- “…እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?” ያለውን ማሰብ አለብን /ማቴ. 7፥11/። በዚህ ክፍል ላይ ለሚለምኑት ያለው ስለ ተሳሳቱ ወገኖች የሚማልዱትን ሰዎች ነው ።
ስለሌሎች መጸለይም ለራስ ማጉደል አይደለም ፥ መጨመር ነው ። ምልጃ ክብር ሆኖ እስከ ዛሬ ቃና ዘገሊላ የሚነገረው ለዚህ ነው ። ስለ ሌሎች የሚጸልይ ክቡር ነው ። የሚጸልይለት ወገን ያለውም ትልቅ ባለጸጋ ነው ። ስለሌሎች መማለድ ክብር ነው ብለናል ። አለመጸለይ ደግሞ ኃጢአት ነው ። እግዚአብሔር ለእኔ ፥ ለእኔ የሚል ጸሎትን አይወድምና ። ነቢዩ ሳሙኤል ፡- “ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ” ብሏል /1ሳሙ. 12፥23/ ። ከነቢዩ ሳሙኤል ንግግር ሁለት ነገሮችን እንማራለን ። የመጀመሪያው ለተሳሳቱ ሰዎች ቅኑን መንገድ ማስተማር ፥ ሁለተኛ እንቢ ካሉ መጸለይ ይገባል ። ነቢዩ ሳሙኤል እግዚአብሔር ስለናቀው ስለ ሳኦል አብዝቶ ያለቅስ ነበር /1ሳሙ. 16፥1/ ። በብሉይ ኪዳን ስለ ኃጢአተኛ ያለቅሱ ነበር ፥ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታችን የሰውን ኃጢአት ተሸክሞ ሞተ።
ስለሌሎች መጸለይን ውለታ አድርገን የመበለቶችን ልብና ከረጢት መበርበር የለብንም ። እግዚአብሔር ተአምራትን የሚያደርገው ራርቶ መሆኑን እያሰብን ልናመሰግነው ብቻ ይገባል ። የምንጸልይላቸው ወገኖች መከራው ይርቅላቸዋል ፥ መከራው ቢመጣ እንኳ እምነታቸውን እንዳይከስሩ ይረዳቸዋል /ሉቃ. 22፥31/።
6- ስለሌሎች ማሰብ ያለበት ነው
እመቤታችን ፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለች እንጂ እኔ ይህ ነገር የለኝም አላለችም ። መንፈሳዊነት ምን አለኝ ሳይሆን ምን አላቸው ? ምን ጎደለኝ ሳይሆን ምን ጎደላቸው ? ከእኔ ይልቅ ለወገኔ ይደረግለት የሚል ነው። ራሱን ለሌሎች የሰጠ አምላክን የምናመልክ ከሆነ ለሌሎች እንኖራለን ። እመቤታችን ራሷን በሚመለከት ተአምር እንዲያደርግ ስትጠይቅ አናነብም ። ስለሌሎች ጉድለት ግን ክብሩን እንዲገልጥ ግድ ትለዋለች ። ምልጃ ወይም ስለሌሎች መጸለይ ፍቅር ነው ።
7- የጌታን ልብ ያወቀ ነው
እመቤታችን ፡- “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ባለች ጊዜ ጌታችን የሰጠው ምላሽ የሚያስደነግጥ ይመስላል ፡- “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት” በዚህ ንግግር እኛ እንደነግጥ ይሆናል ፥ እርስዋ ግን አልደነገጠችም ። ምክንያቱም ልቡን ታውቀዋለች ። በመቀጠል ፡- “እናቱም ለአገልጋዮቹ ፡- የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው” /ዮሐ. 2፥5/። ጉዳዩ ቀጠለ ። በጣም በሚዋደዱ ሰዎች መካከል መግባቢያው ቋንቋ ሳይሆን ፍቅር ነው ። በቋንቋ ምልዐት እንግባባ የሚሉ ፍቅር የጎደላቸው ናቸው ። በፍቅር መካከልም ቋንቋ የመግለጥ አቅም የለውም ። በጣም የሚወዱን ሰዎች አንድ ነገር ስንለምናቸው ውጣልኝ ሊሉን ይችላሉ ። ድምፁ ግን ግባልኝ ፥ አለሁልህ ማለት ነው ። አምላካችንንም ስንለምነው ኮስተር ያለ መልስ ሊሰጠን ይችላል ። ነገር ግን ልቡን ማወቃችን ለጸሎት በጣም ያስፈልገናል ። ያቺ ከነማዊት ሴትን እናስባት፡-
“ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ። ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች” /ማቴ. 15፥22-28/ ። ይህች ሴት ምንም ኃጢአተኛ ብትሆን የጌታን ልብ ግን አውቃለች ። በመጨረሻ በፍቅር ፥ በንስሐ ፥ በእምነት ፥ በትዕግሥት አሸነፈችው ። ፍቅሯ ኃይለ ቃል እየተናገራት አለመቀየሟ ነው ። ንስሐዋ አዎ ውሻ ነኝ ማለቷ ነው ። እምነቷ ጌታ እንደሚምር እርግጠኛ መሆኗ ነው ። ትዕግሥትዋ የለመነችውን እስክትቀበል ተስፋ አለመቊረጧ ነው ።
8- ከልመና በኋላ ተማምኖ መቀመጥ ያለበት ነው
ቅድስት ማርያም እመ ኢየሱስ ፡- “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ካለች በኋላ ተማምና ስትቀመጥ እናያታለን ። እርሱ በጽሞና እንደ ሰማን በጽሞና ደግሞ መልሱን መጠበቅ ይገባል ። በጸሎት ማልቀስ ማንባት እስኪጸልዩ ነው። ከጸለይን በኋላ በቊጥጥር ሥር የዋለ ጉዳይ ነውና ደግሞም ከእኛ አልፎ በጌታ እጅ ላይ ነውና ተረጋግተን መቀመጥ ይገባል ። አንዳንድ ጉዳዮች ከአቅማችን በላይ ሆነው ለመንግሥት ካሳወቅን በኋላ እናርፋለን ፥ እኛ ብንተወው እንኳ ጉዳዩን መንግሥት ይቀጥላል ። ዘግቻለሁ ካላልን ከርሞ ያ ጉዳይ ትኩስ ይሆናል ። እንዲሁም የምንጸልየው መንግሥት ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ነው ። ስለዚህ ማረፍ ይገባናል ። የጸለይነውን እኛ ብንረሳው እንኳ እርሱ አስታውሶ ይፈጽመዋል ። ዛሬ የምንበላው የረሳነው የጸሎት መልስ ነው ። እመቤታችን ልመናዋን ካቀረበች በኋላ በእርጋታ መጠበቅ ጀመረች ።