የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ሳይዳው ፊልጶስ

“ፊልጶስም ከእንድርያስና ከጴጥሮስ ከተማ ከቤተ ሳይዳ ነበረ”
ዮሐ. 1፡45
 ጌታችን ፊልጶስን ተከተለኝ አለው። ቀጣዩን ለማወቅ ቀጣዩን መኖር አያስፈልግም። ቀጣዩን የሚያውቀውን ጌታ መከተል ልብን ያሳርፋል። ተከተለኝ በሚል ድምፅ ብቻ የተከተለው ፊልጶስ ነው። ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ተደጋጋሚ ነገሮችን አይተዋል። የተቀባበለ መሣሪያ በጣት ይተኮሳል፣ የተዘጋጀ ልብም በትንሽ ቃል ይዘምታል። ጌታ ተከተለኝ ያለው ለሐዋርያነት ነው። ነቢይነት ያስወድዳል፣ ሐዋርያትን ግን ያስገድላል። ነቢያትን ስንመለከት ብዙዎቹ በክብር የኖሩ፣ ተፈርተውና ታፍረው ያለፉ ናቸው። ሐዋርያት ግን ዘመናቸውን በመከራ፣ ሕይወታቸውን በሰማዕትነት ያሳለፉ ናቸው። ነቢይነት ተስፋ የሚሰጥ፣ የወደፊቱን የሚናገር ነው። ሐዋርያነት ግን ፍጻሜን የሚናገር ነው። ነቢይነት ይሁንታን አይፈልግም። ሐዋርያነት ግን ይሁንታን ይፈልጋል። ተቀበሉ፣ እመኑ ይላል። ሰዎች ከሚኖሩበት ዛሬ የማያውቁትን ነገን ያፈቅራሉና ነቢያትን ያከብራሉ። ሐዋርያትንም ይጠላሉ። ዛሬም ወንጌልን ከጠራው ምንጭ የሚቀዱትን ስም መስጠት፣ ማሳደድ ይታያል። እናውቅልሃለን የሚሉትን ሳይጋርዱ በአደባባይ የሚጠነቁሉትን፣ እናጠምቅሃለን፣ እንፈውስሃለን፣ ስልክ ቁጥርህን፣ ትዳርህን እንነግርሃለን የሚሉትን ግን ብዙዎች ይከተላሉ። ይልቁንም የዚህ ዓለም ባለጠጎች ጠንቋይ ቤት ባይሄዱ እግዚአብሔር ቤት እንዲጠነቆልላቸው ይፈልጋሉ። ስለዚህ ለሐሰተኞች እየናኙ ወንጌላዊው ላይ ይታሠራሉ። ፊልጶስ የተጠራው ዓለም ለማይወደው ሐዋርያነት ነው።
 ዮሐንስ መጥምቅ ያለሰለሰውን ልብ ጌታችን ዘራበት። ተከተለኝ የሚለው ቃል የወደቀው ለስላሳው ልብ ላይ ነው። ጌታን ማስከተል የዓለሙ ግብር ነው። ጌታን መከተል ግን ደቀ መዝሙርነት ነው። ዮሐንስ የጀመረውን አገልግሎት ጌታ ፈጸመው። እኛ ጀምረን እኛ የማንጨርሰው አገልግሎት ብዙ ነው። ጨርሰን ከሆነ ሌሎች ጀምረውታል፣ ጀምረን ከሆነ ሌሎች ይጨርሱታል። በአገልግሎት ላይ ጀማሪና ፈጻሚ ለመሆን እንዳንከጅል ዮሐንስና ጌታችን ይነግሩናል። “ነቢያት መደመዱ፣ ሐዋርያት ገደገዱ” ይባላል። መመድመድ ቦታውን ማጥራት መሠረት ለመጣል ማዘጋጀት ነው። መገድገድ ምሰሶዎቹን ማቆም ነው። መድምደን ከሆነ የሚገደግዱ አሉ። ገድግደን ከሆነ የመደመዱ አሉ። አገልግሎት ተናባቢ ካልሆነ ክብርና ፍሬ እያጣ ይመጣል። ጌታችን የጠራቸው ቤተሰባዊ፣ ወዳጃዊ፣ ተመሳሳይ የሥራ ጠባይ፣ አብሮ አደግነት ያላቸውን ነው። ቅርበት ያላቸውን ሰዎች ለደቀ መዝሙርነት ማስተሳሰር ተገቢ ነው። ጌታ ምርጫው ውስጥ ይሁዳን የጨመረው ሁሉም ንጹሐን ከሆኑ ዓለም ሁሉ ንጹሕ ነው ብለው ሊያስቡ የመጡበትን ዓለም ሊረሱ ይችላሉ። ይሁዳ ግን የሚገጥማቸውን ዓለም ማሳያ ነበር። አጠገባችን ያሉ ዓመፀኛ ሰዎች ይህን ዓለም የማናይባቸው መስተዋት ሊሆኑ ይችላሉ።
አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል የተውጣጡ ናቸው። አሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል በሐዋርያት ብቻ ሳይሆን በሰማያዊቷ አገር ላይም ተጽፈዋል /ራእ. 21፡12/። ጌታችን ዓላማውና ፍቅሩ እስከ ሰማይ ነው። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ አሥራ ሁለቱን ነገድ የሚወክሉ መሆን ነበረባቸው። ጌታ ከኢየሩሳሌም ደቀ መዛሙርትን ያልመረጠው በዚያ የነበሩት በአብዛኛው የይሁዳና የብንያም ነገዶች ስለ ነበሩ ነው። ገሊላ ግን የሁሉም መኖሪያ ነበረች። ታዲያ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ወኪል ከሆኑ ከአሥራ ሁለቱ የነገድ አባቶች አንዱ ሮቤል የአባቱን ምንጣፍ በመድፈሩ ከበረከት ጎድሏል። ይሁዳም ጌታውን በመሸጡ ከጥሪው ጎድሏል። በይሁዳ ፋንታ ማትያስ እንደ ገባ እንዲሁም የሮቤልም ብኵርና ለዮሴፍ ልጆች ተሰጥቶአል /ዘፍ. 48፡5፤ 1ዜና. 5፡1/።
 ዛሬ ከሁሉም ወገን የተጠራ አባል በሕዝብ ተወካይነት የሚሰበሰበው ከዚህ መንፈሳዊ አሠራር ተወስዶ ነው። ለደቀ መዛሙርቱም በአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ላይ ለመፍረድ በአሥራ ሁለት ወንበር የሚቀመጡት በየወገኑ በየወኪሉ ነው /ማቴ. 19፡28/።
 ከጌታችን ደቀ መዛሙርት እስራኤልን በትግል ነጻ እናወጣለን ብለን ከሚያስቡ ከአርበኞች አባላት አንዱ የነበረው ቀነናዊ ስምዖንን እናገኛለን። ይህን ቅንዓቱን ለወንጌል እንዲያውለው ጌታ ፈልጓል።  ሰው በነፍሱ ነጻ ካልወጣ የሥጋ ነጻነት ወደ ተሟላ ኑሮ አያደርስም። ስለዚህ ጌታችን ሰውን በነፍሱ ነጻ ለማውጣት መጣ። የመገዛዛትና ሌላውን የመጨቆን ስሜት የሚመነጨው ነጻ ካልወጣች ነፍስ ነው። ነጻ የወጣች ነፍስ ሌላውን በማገልገል የምትደሰት ናት። የጌትነት ስሜትን የሚወልደው የባርነት ስሜት ነው። ጌታችን ግን በጦርነት ነጻ የማውጣት አሳብ የነበረውን ሰው ሳይነቅፍ አስከተለው። ከደቀ መዛሙርቱ የምናገኘው ሌላው ማቴዎስ ነው። ማቴዎስ ቅኝ ለያዙ ለሮማውያን ግብር የሚሰበስብ በሕዝቡ ዘንድ የተጠላ ሥራ የሚሠራ በአጭር ቃል ባንዳ እየተባለ የሚጠራ ነው። ስምዖን ቀነናዊንና ማቴዎስን ሊያገናኝ የሚችል የክርስቶስ ፍቅር ብቻ ነው። የሐዋርያት ጉባዔ አገራዊ ስሜትና ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ የነበራቸው፣ ገጠር ቀመስና ከተማ አዋቂ የነበሩ ሰዎች ስብስብ ነው። ትንሹ ያዕቆብና ይሁዳ የጌታችን አብሮ አደጎች ናቸው። የመጀመሪያውን አገልግሎቱን ተቃውመዋል /ዮሐ. 7፡4/። አብረው አድገዋልና አብሮ ማደግ አብሮ ማወቅ መሰላቸው። ጌታ ግን እስኪለወጡ ታገሠቸው። ታዲያ ለውጡማ ያዕቆብ መልእክቱን ሲጽፍ፡- “የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን” እንዲል አደረገው /ያዕ. 1፡1/። ኢየሱስ ክርስቶስን ወንድም ብሎ ቢጠቅስ ከልካይ የለውም። አብረው አድገዋልና። ነገር ግን ባሪያው ነኝ አለ። እግዚአብሔርነቱንም ተቀበለ። ይሁዳም፡- “የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ” በማለት ይጽፋል /ይሁዳ. ቊ. 1/። የያዕቆብ ወንድምነቱ ካኮራው የጌታ አብሮ አደግነቱ ይበልጥ ያኮራ ነበረ። አሁን ግን ባሪያ ነኝ አለ።
ጴጥሮስ ፈሪነት ሲታይበት የዘብዴዎስ ልጆች ዮሐንስና ያዕቆብ ግን ደፋሮች ነበሩ። ጴጥሮስ ሲፈራ እነ ዮሐንስ ሲደፍሩ እየተሳሳቡ ዘለቁ። ፈረሱ ሌጣ ከሆነ እልም ይላል። ጋሪው ግን ያበርደዋል። ፈረሱ ደግሞ ጋሪውን ሲጎትት ከጥፋት ይድናል።
 በዚህ ክፍል ላይ የምናነሣው ፊልጶስን ነው። ፊልጶስ የራሱን ጥሪ ምላሽ ከሰጠ በኋላ በመሢሑ ናፍቆት የከሳውን ናትናኤልን ለመጥራት ፈለገ። ለደረሰን ጥሪ ምላሽ ስንሰጥ ሌሎች እንዲሰጡ እናደፋፍራቸዋለን። እኛ ያልኖርንበትን እውነት ሌሎች ሊኖሩት አይችሉም። የምንናገረውን የምንኖረው ከተቃወመው አደገኛ ነገር ነው። የምንናገረውን ሌሎች ቢቃወሙት ትንሽ ነገር ነው። ሰው መልካም ምግብ ሲበላ እንኳ ጓደኛውን ያስታውሳል። ክርስቶስን የሚያህል ሠርከ ኅብስት ሲያገኙ ወዳጅን መጥራት የፍቅር መግለጫ ነው። ለወዳጅ የሚያልቀውንና ከሞት የማያድነውን ብቻ ሳይሆን የዘላለሙን አምላክ መስጠት መልካም ነው። ወዳጅነትንም ዘላለማዊ ማድረግ ነው።
 ፊልጶስን ለሁለተኛ ጊዜ የምናገኛው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስት ላይ ነው። ጌታችን አምስት ሺህ ሕዝብን በተአምራት ለመመገብ ሲል መጀመሪያ ያናገረው ፊልጶስን ነው። “ኢየሱስም ዓይኖቹን አንሥቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊልጶስን፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን? አለው” ጌታ ይህን ያለው የሚያደርገውን አውቆ ሲሆን የፊልጶስን መልስ ለመስማት ይፈልግ ነበር። ፊልጶስ ገራም፣ ለምክር የሚሆን ሰው ነው። ወዳጅነቱ ጥብቅ የነበረ ማማከርም የሚወድ ሰው ነው። አማካሪነት ውጤታማ የሚሆነው ምክር በመስጠት ብቻ ሳይሆን ምክር በመቀበልም ነው። ፊልጶስ በዚህ የተሟላ ሰው ነው። ፊልጶስና እንድርያስ የማይለያዩ ነበሩ። ፊልጶስ በተነሣበት አንቀጽ እንድርያስ ብቅ ይላል። የግልጾቹን ደቀ መዛሙርት ያተረፉ የጀርባ አጥንቶች ናቸው። እንድርያስ ጴጥሮስን፣ ፊልጶስ ናትናኤልን አትርፈዋል።
 ከግሪክ የመጡ ሰዎች ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ያሉት ለፊልጶስ ነበር /ዮሐ. 12፡21/። ፊልጶስ በቀጥታ ወደ ጌታ አላመጣቸውም። ለእንድርያስ አማከረው። የማይታወቁ ሰዎችን ወደ መምህር እየጎተቱ ማቅረብ ተገቢ አይደለም። ማብረድና የመሰናዶ ትምህርት መስጠት ተገቢ ነው። ይህን ማስተዋል የማናየው ከፊልጶስ ነው።
ፊልጶስን በአስደናቂ ጥያቄው የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ አሥራ አራት ላይ ነው። “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው”  የእርካታው ጥጉ ብዙ ነገሮች ማየት አይደለም። ዓይን ከመንከራተት፣ ልብም ከመዋተት የሚያርፉት አብን በማየት መሆኑን ፊልጶስ አምኗል። ስለዚህ ይህን ታላቅ ልመና አቀረበ። ፊልጶስ ግን የሚለምነው የተፈጸመውን ነገር ነው። አጠገቡ ያለው ጌታ በአብ ክብር የሚኖርና የሚገዛ ነው። የፀሐይን አካሏን ማየት እንደማይቻል በብርሃኗ ግን ፀሐይን መገንዘብ እንደሚቻል እንዲሁም አብን ማየት አይቻልም። በልጁ ግን እናውቀዋልን። የፀሐይ ብርሃንንም እናይበታለን እንጂ ይህን ይመስላል ብለን ልንናገረው ያስቸግረናል። የውሃንና የብርሃንን መልክ መግለጥ አስቸጋሪ ነው። እንዲሁም ክርስቶስ ሁሉን ያሳውቀናል እንጂ እርሱን በሙሉነት መገንዘብ አንችልም። ወደዚህ ዓለም የመጣው በሙሉነት እንድናውቀው ሳይሆን የአቅማችንን ያህል እንድናውቀው ነው። ፊልጶስ ገራም ሰው፣ ፍቅሩ ግን የጠበቀ ሐዋርያ ነው። እግዚአብሔር ከችሎታችን ገራምነታችንን ይፈልጋል። ችኮታ ያለ ገራምነት መሠረት የሌለው ቤት እንደማነጽ ነው። ውድ ምግብ ጣዕሙን የሚያወጣው ርካሽ በመሰለው ጨው ነው። በወጥ ውስጥ ትንሹ ዋጋ ጨው ብቻ ነው። ግን ውዱ ምግብ ጣዕሙ የሚወጣው በጨው ነው። ውድ ችሎታ ቢኖረን ጣዕሙ የሚወጣው በገራምነት ነው።
እባክህ ጌታ ሆይ ገራም አድርገን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ