የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለተቀበሉት

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ መጋቢት 19/2008 ዓ.ም.
“ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” /ዮሐ. 1፡12/፡፡
ክርስቶስን አላመኑም እንደ ገናም ሰቅለውታል በሚል አይሁዳውያንን እንወቅሳለን፡፡ በርግጥ አለማመን ባለማመን ላይ አይቆምም፡፡ አለማመን የማያምነውን ይሰቅለዋል፡፡ በክርስቶስ ባለማመን ሰው ክርስቶስን በየትኛውም ቦታና ጊዜ ይሰቅለዋል፡፡ ወንጌላዊው፡- “ዓለሙም አላወቀውም” በማለት ሁሉን ይወቅሳል፡፡ በርግጥም ስናየው በክርስቶስ የዘር ሐረግ ውስጥ አሕዛብ ስላሉ ክርስቶስ ከሕዝብና ከአሕዛብ ተወልዷል፡፡ ልደቱ መላውን ዓለም ያማከለ ነው፡፡ ስለ ክርስቶስ መወለድ በቤተ እስራኤል ብቻ ሳይሆን በቤተ አሕዛብም ተስፋ ነበረ፡፡ ለዚህም የሰብአ ሰገል መምጣት ይጠቁመናል፡፡ በክርስቶስ ሞት ውስጥም ሊቃነ ካህናቱ ሐናና ቀያፋ ብቻ ሳይሆኑ ከአሕዛብ ወገን የሆኑት ሄሮድስና ጲላጦስም አሉበት፡፡ ክርስቶስ እንዲሞት መላው ዓለም ተስማምቷል ማለት ነው፡፡ ያውም ሄሮድስና ጲላጦስ የታላቋ ሮም ሹመኞች ናቸውና መላውን ዓለም ይወክላሉ፡፡ በአገር ውስጥ ችሎት ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ችሎትም ክርስቶስ ይሙት በቃ ተፈርዶበታል፡፡ ክርስቶስን አለመቀበል ባለመቀበል አያርፍም፡፡ ይሰቅለዋል፡፡ ክርስቶስን መስቀል ማለት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡

የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊ፡- “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው የነበሩትን መልካሙንም የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና” ይላል /ዕብ. 6፡4-6/፡፡ ይህንን የሐዋርያውን ማስጠንቀቂያ ስናየው ብርሃን በርቶልን፣ ሰማያዊውን ስጦታ ቀምሰን፣ መንፈስ ቅዱስን ተካፍለን፣ መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል ሰብከን… ወደ ኋላ ማለት ሊመጣ ይችላል፡፡ ክርስትና ሁልጊዜ ብርሃንነቱን መጠበቅ አለበት፡፡ ብርሃንን ለመጠበቅ ዘይቱን መሞላት፣ የማያበራውን ክር ማነቃቃት፣ የሞተውን ክር ገለል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ኃይል ዘወትር በቃሉ፣ በጸሎትና በኅብረት መሞላት ዘይቱ ነው፡፡ የሞተውን ነገራችንን ማነቃቃት፣ እየተውናቸው ያሉትን በጎ ተግባራት እንደገና ወደ ህልውና ማምጣት ብርሃንን ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ ሙት የሆነውን ነገር ደግሞ ጨክኖ ማስወገድ፣ ክፉ ባልንጀርነትንና ኃጢአትን ማራቅ ብርሃንነትን ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ ፀሐፊው ክርስቶስ የሚሰቀለው በታሪካችን ውስጥ እንደ ሆነ ይገልጣል፡፡ ወደ ኋላ ያሉ ክርስቲያኖች የዓለም መዘባበቻ ይሆናሉ፡፡ እነርሱም አውቀዋለሁ ሰብኬዋለሁ እያሉ በሚያሳፍረው ነገር ሲኮሩ ክርስቶስን እንደ ገና ይሰቅሉታል፡፡ የተራበውንና የታረዘውን ወንድም ስናልፈው ይህም ክርስቶስን መስቀል ነው፡፡ አለማመን አለማመን ብቻ ሳይሆን ክርስቶስን እንደገና መስቀል ያስከትላል፡፡ አይሁድ አንድ ጊዜ ሰቀሉት እኛ ብዙ ጊዜ ሰቅለነዋል፡፡
የተቀበሉት የተባሉት ያመኑት ናቸው፡፡ ማመን መቀበል መባሉ ትልቅ ፍቺ ነው፡፡ ማመን መስማት ብቻ አይደለም፣ ማመን መገንዘብ ብቻም አይደለም፡፡ ማመን መቀበል ነው፡፡ ማመን መቀበል ከሆነ እኛ በማድረግ ዋጋ የምናገኝበት ሳይሆን እግዚአብሔር ያደረገልንን መጀመሪያ የምንቀበልበት ነው፡፡ የምናደርገው በጎ ነገር ሁሉ ስለተቀበልነው የምናደርገው ነው፡፡ ያለ እምነት በጎ ነገር ማድረግ ኃጢአት ነው፡፡ አንድ በጎ ነገር ብቻውን ሊደረግ ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ዋጋ የሚኖረው በእውቀት፣ በእምነትና በፍቅር ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ “በእምነትም ያልሆነ ሁሉ ኃጢአት ነው” /ሮሜ. 14፡23/፡፡ ዳግመኛም፡- “በእርሱም ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ከእምነት የሚነሣ መታዘዝ እንዲገኝ ጸጋንና ሐዋርያነትን ተቀበልን” ይላል /ሮሜ. 1፡5/፡፡ ከተለያየ አስተምህሮና ዝንባሌ የተነሣ መታዘዝ ይኖራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሩቅ ምሥራቅ ያሉ የሂንዱና የቡድሃ እምነት ተከታዮች የሚያደርጓቸውን ክርስቲያኖች ላያደርጉት ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን የሚፈልገው ከእምነት የሚነሣውን መታዘዝ ነው፡፡ አንድ ሕንጻ መነሻው መሠረቱ ነው፡፡ አንድ አውሮፕላንም መነሻው ጽኑ የሆነው መንደርደሪያው ነው፡፡ እውነተኛ ምግባርም መነሻው እውነተኛ እምነት ነው፡፡ “በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና” በማለትም እምነት ምግባር፣ ምግባርም እምነት እንዲኖረው ይናገራል /ገላ. 5፡6/፡፡
“ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” /ዮሐ. 1፡12/፡፡
የሚፈስን ጸጋ የምንቀበልበት እጅ እምነት ይባላል፡፡ ለሚያንኳኳ ወዳጅ ድምፁን ሰምቶ መክፈት እምነት ይባላል፡፡ በዘላለም ኪዳን ወደ ሰው የመጣውን ክብር ልብን ከፍቶ መቀበል እምነት ይባላል፡፡ ተቀብያለሁ ማለት ሰምቻለሁ ከማለት የሚያልፍ ነው፡፡ ወታደር ሲቀበል ራሱን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፡፡ መቀበል መሥዋዕትነትን የሚከፍል ነው፡፡ መቀበል ከሌለ ማንኛውም የነገረ መለኮት ምርምር ከጠረጴዛ ጥናት አያልፍም፡፡ ዛሬ ትልቁ ጥያቄ “የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” የሚል ብቻ ሳይሆን “የምታስተውለውን ታምነዋለህን?” የሚል ነው፡፡ ሩቅ ላለው ሕዝብ ማንበብ ወሳኝ ነው፡፡ ወደ ገረገራው ለተጠጋው ወገን የሚያነበውን ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ ለሚያስተውለው ተመራማሪ ማመን ግድ ነው፡፡ መቀበል ፈቃድን የሚመለከት ነው፡፡ በልባችን ያልተቀበልነውን በራችንን አንከፍትለትም፡፡ ልብ ካልተከፈተ ሁሉም ነገር ዝግ ነው፡፡ ያልተቀበልነውን አንቀበለውም፡፡ በልቡ የተቀበለ በቤቱም በስኬቱም ይቀበለዋል፡፡ ሰዎች ላለተቀበሉት ነገር ሊያስመስሉ ይችላሉ፡፡ ሊያርፉ ግን አይችሉም፡፡ ክርስቶስ፣ ክርስቶስ ማለት ዘመናዊነት ተደርጎ ከማን አንሳለሁ በሚል ስሜት መጥራት ይቻላል፡፡ የእምነት ዋጋ ያለው እግዚአብሔር ጋ በመሆኑ የይሉኝታ አማኝ በሁለት ዓለም ይጎዳል፡፡ የምንወዳቸው ስለ ተቀበሉት ነው የተቀበልነው? ወይስ አሠሪዎቻችን ስለሰበኩልን እምቢ ማለት አስፈርቶን ነው የተቀበልነው? በእውነት ስንቀበል ወይም ስናምን ዋጋ አለ፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ልጆች መሆን ነው፡፡
የእግዚአብሔር ልጆች
“ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” /ዮሐ. 1፡12/፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ትልቁ ስጦታ ልጅነት ነው፡፡ ልጅነት ትልቅ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? ብለን ማሰብ አለብን፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ፡- “እምነት ያላየነውን ማመን ነው፣ ዋጋውም ያመነውን ማየት ነው” ብሏል፡፡ ለማመን መሠረቱ አለማየት ነው፡፡ የማመን ግቡ ደግሞ ያመነውን ማየት ነው፡፡ አሁን ካየን ኋላ እናምናለን፡፡ አሁን ካመንን ግን ኋላ እናያለን፡፡ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” ይላል፡፡ አሁን ያዩ ወደ እምነት መሄዳቸው ሊያጠራጥር ይችላል፡፡ ያመኑ ግን ማየታቸው እርግጥ ነው፡፡ የዓለም መፈክር፡- “ማየት ማመን ነው” የሚል ነው፡፡ የመንፈሳዊው ዓለም ዓርማ ግን፡- “ማመን ማየት ነው” የሚል ነው፡፡ የማይታየውን የእግዚአብሔርን ቃል ማመን እርሱ እምነት ይባላል፡፡ ብዙ ተአምራት ቢደረጉ ብዙዎች ያምናሉ ብለን እናስባለን፡፡ ማየት ግን ወደ እምነት ላያደርስ ይችላል፡፡ ተአምር ስላዩ በክርስቶስ ያመኑ የበለጠ ካሳያቸው  ሰይጣንን ይከተላሉ፡፡ ተአምር የጨው ውሃ እንደ መጠጣት ነው፡፡ በጠጡትን ቁጥር መልሶ ያስጠማል፡፡ ለዚህ ነው ተተክሎ የሚማር ሳይሆን የሚንከራተት አማኝ የበዛው፡፡
ጌታችን ዳግመኛ ሊወልደን እርሱ ሁለተኛ ተወለደ፡፡ እኛን የረቂቁ ልደት ባለርስት ሊያደርገን እርሱ የግዙፉ ልደት ባለ ርስት ሆነ፡፡ እኛን ከሰማያዊ ልደት ሊያካፍለን እርሱ ምድራዊ ልደትን ገንዘቡ አደረገ፡፡ የእኛን መንፈሳዊ ልደትና የእርሱን ሥጋዊ ልደት ወንጌላዊው አጠጋግቶ ያነሣል፡፡ ቀጥሎ፡- “ቃል ሥጋ ሆነ” ይላል፡፡ ሁለቱ ተመጋጋቢ ናቸውና፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ባይሆን ኖሮ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች አንሆንም ነበር፡፡ እኛ ግዙፋን ሳለን መንፈሳዊ ልደት ካገኘን፣ እርሱ ረቂቅ ሳለ ሥጋዊውን ልደት ገንዘብ እንዳደረገ እንማራለን፡፡ አንዱ የአንዱ ማሳያ ነው፡፡ የክርስቶስ ደኃራዊ ልደቱ ለቀዳማዊ ልደቱ ማስረጃ ነው፡፡ በደኃራዊ ልደቱ ያለ አባት መወለዱ በቀዳማዊ ልደቱ ያለ እናት ለመወለዱ ማሳያ ነው፡፡ የእኛም ዳግማዊ ልደት መሠረቱ የክርስቶስ ሰው መሆን ነው፡፡ ለዚህ ነው ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “የእግዚአብሔር ልጆች ሊያደርገን እርሱ የሰው ልጅ ሆነ” ያለው፡፡ ለዚህ ነው በወልድ ውሉድ ወይም በልጁ ልጆች ተብለናል የምንለው፡፡
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ምስጋና ላንተ ይሁን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ